Saturday, 02 July 2016 11:56

የደሞዝ፣ የኪራይ እና “የጥቃቅን ተቋማት”፣ የግብር ማሻሻያ ለፓርላማ ቀርቧል

Written by 
Rate this item
(116 votes)

ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፣ ግብር ተቀንሶላቸዋል ከኪራይ ገቢ ውስጥ፣ ግማሹ ከግብር ነፃ ይሆናል ተብሏል የተቀጣሪ ሰራተኞች የግብር ማሻሻያም ለፓርላማ ቀርቧል

    የስድስት መቶ ብር ደሞዝተኛ፣ ከ40 ብር በላይ ነበር ግብር የሚከፍለው፡፡ በአዲሱ ማሻሻያ አዋጅ፣ የግብር ክፍያው ይቀርለታል፡፡
 የጡረታ መዋጮ ከተቀነሰ በኋላ አንድ ሺ ብር የሚያገኝ ደሞዝተኛ ደግሞ፤ 62 ብር የግብር ቅናሽ ያገኛል፡፡
በተመሳሳይ ስሌት የሶስት ሺ ብር ደሞዝተኛ 208 ብር የግብር ቅናሽ ይኖረዋል፡፡ (ሰንጠረዥ ይመልከቱ)
የቤት ኪራይ ገቢ ላይ የተደረገው ለውጥ ሁለት አይነት ነው፡፡ በ1750 ብር ቤት ያከራየ ሰው፣ በድሮው አሰራር፣ ሃያ በመቶ የጥገና ወጪ ታስቦለት 1400 ብር ገቢ እንዳገኘ ነበር የሚቆጠረው፡፡ ከዚያ ልክ እንደ ወር ደሞዝተኛ ግብር ይከፍላል 160 ብር ገደማ፡፡ አዲስ በተሻሻለው አዋጅ ግን፣ ከ1750 ኪራዩ ውስጥ ሀምሳ በመቶው ወይም ግማሹ ለጥገና እንደሚያወጣ ይታሰብበታል፡፡ እናም 875 ብር ገቢ እንዳገኘ ደሞዝተኛ ይቆጠራል፡፡ ከዚህም ውስጥ 28 ብር ግብር ይከፍላል፡፡ ለምን ቢባል፣ ቤት አከራይ እንደ ደሞዝተኛ፣ በአዲስ የግብር ማስከፈያ ስሌት ቅናሽ ተደርጎለታል፡፡ ትልቁ ለውጥ ግን ሌላ ነው፡፡ ከኪራዩ ገቢ ውስጥ፣ ግማሽ ያህሉ ከግብር ነፃ እንዲሆን ተደርጓል - የጥገና ወጪ ስለሆነ፡፡ ይህም፣ አከራዮች ከሚከፍሉት ግብር፣ ሲሶ ያህል ይቀንስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ይሄ ቅናሽ የሚሰራው ለግለሰብ አከራዮች ብቻ ነው፡፡
ህንፃ ገንብተው የሚያከራዩ ድርጅቶች፣ እያንዳንዱን የጥገና ወጪ በሂሳብ መዝገብ ማወራረድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከኪራይ ገቢያቸው ላይ የጥገና ወጪ ከተቀነሰ በኋላ፣ 30 በመቶ ግብር ይከፍላሉ ይላል አዲሱ አዋጅ፡፡
ለግለሰብ የቤት አከራይና ለግለሰብ ነጋዴዎች ከደሞዝተኛ ጋር የሚመሳሰል ቅናሽ የተደረገ ቢሆንም፤ ለንግድ ድርጅቶች ግን የግብር ለውጥ አልተደረገም - እንደ ቀድሞው 30% ነው፡፡
ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትስ? እንደ ንግድ ድርጅት ግብር መክፈል ይጠበቅባቸው የነበሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በአዲሱ አዋጅ እንደ ግለሰብ ነጋዴ ወይም እንደ ደሞዝተኛ ይቆጠራሉ ተብሏል፡፡ “ጥቃቅኖች” ትርፋቸው ትልቅም ይሁን ትንሽ፤ 30% ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ የህጉ ማብራሪያ ይገልፃል፡፡
እናም የወር ትርፋቸው እንደ ደሞዝ ተቆሮ፣ በደሞዝተኛ ስሌት ግብር ይከፍላሉ ተብሏል፡፡
 በቀድሞው ስሌት በወር አምስት ሺ ብር ያተረፈ ተቋም፤ 1500 ብር ግብር መክፈል ይጠበቅበት ነበር፡፡ በአዲሱ ስሌት 750 ብር ገደማ ግብር ይከፍላል፡፡
በእርግጥ፣ ለግለሰብ ቤት አከራዮች እና ለ“ጥቃቅን” ተቋማት፣ የግብር ቅናሽ ተደርጓል ቢባልም፤ በተጨባጭ የዚያን ያህል ለውጥ ያመጣል ማለት አይደለም፡፡  ብዙዎቹ ጥቃቅን ተቋማት ግብር የመክፈል አቅም የላቸውም፤ ወይም አይከፍሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ግብር ተቀነሰላችሁ ቢባሉ፣ ብዙም ትርጉም ላይሰጣቸው ይችላል፡፡







Read 13540 times