Saturday, 02 July 2016 11:49

ስለ ክፍሉ ታደሰ አዲሱ መጽሐፍ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(4 votes)

አዲሱ መጽሐፍ ያልኩት የክፍሉ ታደሰን “ኢትዮጵያ ሆይ …” ነው፡፡ አግኝቼ አነበብኩት፡፡ 416 ገፅ ከነፎቶግራፉ፤ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ምንጊዜም ለኢህአፓ (እሱ ለኖረበት ወቅት) በሚቆረቆረው “በአመራሩ ውስጥ ባገለገልኩባቸው ጊዜዎች ሁሉ ለተላለፉት ማናቸውም ውሳኔዎች እንደ ሌሎቹ ሁሉ ሙሉ ኃላፊነትን እንደምወስድ አረጋግጣለሁ በሚለው ህፀፁን ከማረም ጋር፤ እንደገናም የልጅነት ዕድል ቢሰጠው ኢህአፓ ከመሆን ምኞት ባልተላቀቀው በክፍሉ ታደሰ፤ (ለመሆኑም በበኩሌ አልፈረድኩበትም) የተፃፈ ነው፡፡
ክፍሉ ታደሰ፤
የያ - ትውልድ፣ ቅፅ 1፣ 1983 ዓ.ም
ያ - ትውልድ፣ ቅፅ 2፣ 1983 ዓ.ም
ያ - ትውልድ፣ ቅፅ 3፣ 1983 ዓ.ም
የ1997 ዓ.ም ምርጫ፣ ግንቦት 7፣2006 ዓ.ም
 መፃህፍት ደራሲ ነው፡፡ እኒህን ስለመድረሱ እግዜር ይስጠው፡፡
አሁን ያነበብኩት “ኢትዮጵያ ሆይ--” የሚለው መፅሀፉ ቅፅ 1 ነው፡፡ ቅፅ 2 እንዳለው አመላከተን ማለት ነው፡፡
መታሰቢያነቱ - ለጄ/ተፈሪ በንቴ፣ ኮ/ል አስራት ደስታ፣ ኮ/ል ኅሩይ ኃ/ሥላሴ፣ ሻምበል ሞገስ ወ/ሚካኤል፣ ሻ/ዓለማየሁ ኃይሉና አብረዋቸው ለወደቁት ነው፤ ይላል፤ አልገረመኝም፡፡ አንድምታው ገብቶኛልና!
የመፅሀፉ የበለስ ፍሬ ነገር፤
ኢህአፓን በተመለከተ መፅሐፍ ላወጡ ሰዎች ምላሽ መስጠት፤ (ጊዜ ለሰጣቸውም ላልሰጣቸውም ፀሐፊዎች ማለት ይሻላል)
ስለ ኢህአፓ ውዥንብር ፈጥረዋል ባላቸው የአሁኑ ትውልድም ሆነ የዱሮው ትውልድ ጭብጥ ማብራሪያ ማቀበል
የኢህአፓን ነገረ ሥራ በዝርዝር ማሳየት ይመስለኛል፡፡
ደራሲው እንዳለው በአደባባይ ስለ ኢህኢፓ በተነሱ ጉዳዮች ዘንድ፤ ይጣቀሳሉ ያላቸውን፣ ፍሬ ነገሮች፤
ሀ) ብርሃነ መስቀል ረዳ (የኢህአፓ፣ አመራር) በእስር ቤት ሆኖ የፃፈውን ሰነድ
ለ) የደርግ አባሉ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ” ሲል የፃፈው መፅሐፍ
ሐ) የደርግ አባሉ ኮ/ል ፍስሀ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” ያሉት መፅሐፍ
መ) ከመኢሶን ዋንኛ መሪዎች በተለይም የፕሮፓጋንዳና የቅስቀሳ ኮሚቴ መሪ በሆነው በነገደ ጎበዜ በተፃፈው “ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት” የተባለው መፅሐፉ፤
 ሠ) የደርግ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ የልዩ አቃቤ ህግ (በ1980 መጀመሪያ ላይ) ያዘጋጃቸውን ሰነዶች
ረ) በ1971 ዓ.ም የመኢሶኑ መሪ ኃይሉ ፊዳ በእስር ቤት ለደርግ የሰጠው ደጎስ ያለ ሰነድ
ሰ) በ1971 ዓ.ም እነቲቶ ህሩይ በሚል ስም በርከት ያሉ የኢህአፓ አባላት የሰጡት ቃል --የተባሉ ሰነዶችን በዋቤነት በመጠቀም፣ እኒህ ሰነዶች ከኢህአፓ ጋር ባላቸው ተያያዥነትና ተፃርሮ ላይ ተመርኩዞ፣ ጉዳያቸውን መዳሰስ ላይ መፅሐፉ ያጠነጥናል፡፡ ስለ ትግሉ የራሱን የግሉን አስተያየትም ያክላል፡፡ ስለ ኢህአፓ ልቦለዳዊ ትርክት ስለ ፃፉ ሰዎችም አስተያየቶችና ትዝብቶቹን በክብር አስፍሯል፡፡ ዋናው ጉዳዩም ውዥንብሩን ማጥራት ነው!
ዞሮ ዞሮ ክፍሉ ታደሰ ከተረፉት ሁለት አመራሮች አንዱ ነውና፤ ስለ ያ ትውልድ ይሟገታል! ለኢህአፓ ይሟገታል! ስለ ኢህአፓ ስምና ያለቁ አባላት አልተዘመሬነት እንደቱሉ ፎርሳ፤ “ይቺ ማህበር እኔ ቆሜ አትፈርስም!” ይላል፡፡ ህዝብ ውስጥ ያለው የኢህአፓ መንፈስ ያቸንፋል፤ ይላል፡፡ የሚችለውን ያህል በማስረጃ ያፀኸየዋል! ነባር አይጥፋ!
ዛሬም፤
“የትግሉ ነው ህይወቴ
ልጓዝ በድል ጎዳና
በወደቁት ጀግኖች ፋና!”
--- ማለት አላዳገተውም! በማስረጃ አስደግፎ “በላ ልበልሃ!” ይላል፡፡በበኩሌ ቅፅ ሁለትን ሳላነብ በቅፅ አንድ ብቻ አስተያየት ልስጥ አልስጥ በማለት ከራሴ ጋር ተሟግቻለሁ፡፡ የተስፋዬ ደበሳይ ልጅ ሀምራዊት፤ስለ አባቷ አባትነት ስለተሰማት ስሜት “እንኳን ከሌላ ሰው ከራሴ ጋርም ላልነጋገርበት ወሰንኩ” እንዳለችው ሳይሆን፤“ስላነበብኩት የተሰማኝንማ ማንም አይነጥቀኝም!” ብዬ ከራሴ ጋር ወስኜ ነው የተነሳሁት! “የታሪክ ሽሚያው እንደ ጉድ ፈልቷሏ!) ግዴለም በቅፅ አንዱ ላዝግም፡፡ የክፍሉን የመጨረሻ ድምዳሜ ሳልሻማ በራሴው መንፈስ ልፃፍ አልኩ! የቀጣዮቹ እትሞች ሰው ይበለን!!”

Read 3951 times