Saturday, 02 July 2016 11:46

አቀማመጥ አበላሽተው ከአሳላፊ ይጣላሉ

Written by 
Rate this item
(22 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ ላሟን ሊመግብ ወደ በረት ይገባል፡፡ ላሚቱ የምትበላውን ወደ ገንዳዋ እየጨመረ ሳለ በእግሯ የምግቡን እቃ መታችው፡፡ ምግቡ በሙሉ በአካባቢው ተበተነ፡፡
ገበሬው ተናደደና፤
“አንድ ብያለሁ!” አለ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ላሚቱን ለማገድ ከበረቷ ያስወጣታል፡፡ ከግቢው እየወጣች ሳለች፣ ገበሬው ሁለት ሳምንት ሙሉ ሲያጥርና ሲጠግን የከረመውን አጥር በቀንዷ ስትመታው ፈረሰና ግማሹ መሬት ላይ ወደቀ፡፡
ገበሬው ብስጭት ብሎ፤
“ሁለት ብያለሁ!” አለ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ገበሬው ላሚቱን ለማለብ ጮጮውን ይዞ ወደ እግሯ ቀረብ ብሎ፤ ወደ ጡቶቿ እጁን ሲሰድና ጥቂት ወተት እንዳለበ አሁንም በእግሯ ጮጮውን መታችው፡፡ ወተቱ በአካባቢው ላይ ተረጨ፡፡
ገበሬው ትእግስቱ አለቀና፤
“ይሄ ሶስተኛሽ ነው! አለቀ በቃ!” አለና መሣሪያውን አምጥቶ ግንባሯን ብሎ ገደላት!
ሚስቱ ተኩስ ሰምታ ተኩሱን ወደሰማችበት እየሮጠች መጣች፡፡ ስታይ ላሚቱ ወድቃለች፡፡ ገበሬው እጁ ላይ ገና አዲስ የተተኮሰ ሽጉጥ በአፈ-ሙዙ ጭስ ይተፋል፡፡
ሚስቲቱ በጣም ተበሳጭታ፣
“አሁን ምን ልሁን ብለህ ነው ይቺን ምስኪን እንስሳ በሽጉጥ የምትገላት?” ብላ አምባረቀችበት፡፡
ገበሬውም፤
“አንቺንም አንድ ብያለሁ!” አላት፡፡
***
የማስጠንቀቂያ ደወል አለማዳመጥ አንድም የጆሮ፣ አንድም የልቡና ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ የጆሮ ችግር ከሕክምና ያለፈ መፍትሄን አይሻም፡፡ የልቡና ችግር ግን የተለያዩ ግብአቶች ውጤት ነው፡፡ እንዲህ በዋዛ አይፈታም፡፡ ብዙ ናቸው የመፍትሄው አንጓዎች፡፡ የችግሮቹ አንጓዎችም እንደዚያው ሀ/ ልቡና ሊለግም ይችላል፡፡ ለ/ ልቡና አውቆ በድፍረት እምቢ ሊል፣ ሊያምፅ ይችላል፡፡ ሐ/ ልቡና ለአቅመ-መቀበል ያልደረሰ፣ ያልበሰለ ሊሆን ይችላል፡፡ መ/ ልቡና በተአብዮ የተሞላ ሊሆን ይችላል፡፡ በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ልቡና ጥያቄዎችን ላያዳምጥ ይችላል፡፡ አብሮ ግን የማስጠንቀቂያውን ደወል የደወለው ማነው? መስማት የሚጠበቅበትስ ማነው? ደወሉ ወቅታዊ ነው አይደለም? ወይንስ “የጠርሙሱ ውታፍ እንደተነቀለለት ጅኒ” ድንገት የመጣ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡
በንጉሱ ዘመን ለወሎ ረሃብ የማስጠንቀቂያ ደወል ንጉሡ ዕዝነ-ልቦናቸውን ነፈጉ፡፡ ለወታደሩ ጥያቄዎችም እንደዚሁ ዕዝነ-ልቦናቸውን ነፈጉ፡ ለተማሪዎችም ጥያቄዎች ዕዝነ-ልቦናቸውን አልቸሩም… ዋለ አደረና የሆነው ሆነ! በኃይል ለመፍታት ሞከሩ፤በኃይል ወደቁ፡፡
በጃንሆይ እግር የገባው ወታደራዊ መንግሥትም ለዲሞክራሲ ጥያቄዎች፣ ለሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ልቡናውን አልከፍትም አለ፡፡ ለእኩልነት ጥያቄዎችና ለህዝባዊ ሥልጣን ጥያቄዎች ዕዝነ-ልቦናዬን አልሰጥም ሞቼ እገኛለሁ አለ፡፡ ንቀትን፣ ትምክህትን፣ ተዓብዮን “የፍየል ወጠጤን” ምላሹ አደረገ፡፡ በኃይል ኖረ በኃይል ወደቀ፡፡ ከእነዚህ ሁለት መንግሥታት ሁለት ተመሳሳይ ልምድ መማር ያለብንና ተገቢ ትኩረት መስጠት ያለብን፤ ኃይል ጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ ዘላቂ እንደማይሆን ነው፡፡ ላልተመለሱ ጥያቄዎች ዕዝነ-ልቦናን መክፈት ቢያንስ ከተለመደ የአወዳደቅ ባህል ይገላግለናል፡፡ ለዘመናት የቆዩ የተሸራረፉ ምላሾችን የማይፈልጉ፣ ሳይፈቱ ከቀጠሉ እንደገና ሌላ ችግር የሚፈለፍሉ፣ መሰረታዊ ጥያቄዎች አያሌ ናቸው፡፡ ሊዘለሉ ደግሞ ከቶ አይችሉም፡፡ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የኑሮ መሻሻል፣ የመንግሥት አስተዳደር፣ የአገር ሉአላዊነት ቱባ ቱባ ጥያቄዎች ሁሌም እንዳፈጠጡብን አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ የሊበርቲ፣ኢኳሊቲ፣ፍራተርኒቴ ልጆች ናቸው፡፡ (Liberty,equality,fraternity እንዲል መጽሐፈ ፈረንሳይ) በሽርፍርፍና በገደምዳሜ መንገድ ይነካኩ እንጂ በማያሻማ መንገድ በነቢብ - ወገቢር (Both in theory and practice)፤ ግዘፍ ነስተው አልታዩም፡፡ ህይወት አላገኙም፡፡ ነብስ አልዘሩም፡፡
“ለታላቁ ዓላማ፣ ለሰው መልካም እድል
ህይወቴ ትሞላ፣ ትሁን የትግል ድል” ---- ያለውን ማርክስን ሁሌም የሚያስታውሱ ልባም ሰዎችን አለመዘንጋት ነው፡፡ “ዕዝነ ልቡናህን ልቡና ላላቸው ክፈት” ይላል አንድ ፀሐፊ፡፡ ቢያንስ አዳምጠን ስለ መፀፀት ማሰላሰል እንችላለን፡፡ በእርግጥ ብሶቶችንና እሮሮዎችን ብናዳምጥ፣ አዳምጠንም መፍትሄ ለመስጠት ቆም ብለን ማውጠንጠን ብንችል ምን ይጐዳናል? ለማለት ያህል ለጉዳዮች ጊዜ እንስጥ፡፡ “ሁሌ እኛ ነን ልክ፣ ሌሎች ልክ አይደሉም” የሚለው ንድፈ-ሃሳብ የሚመነጨውና የሚገዝፈው የሌሎችን ጥያቄ አንድም ከመናቅና ከናካቴው ካለመስማት፣ አንድም ከማኮሰስና አድቆ ከማየት፣ አንድም ደግሞ “ይሄማ የእነ እገሌ ነው፣ ለነእገሌ መልስ አንሰጥም” ከማለት ነው፡፡  ጥያቄዎቹ ግን አድረው ብቅ ይላሉ፡፡ እንዲያውም ዘርፍ አበጅተው፡፡ መዝገብን ወደ ኋላ አገላብጦ ከወጪ ቀሪ ምን አለብኝ ማለት፣ ከዕዳ ነፃ ማድረጉን ማሰብ እጅግ ብልህነት ነው፡፡ (አራት አመት ታስሮ በነፃ የተለቀቀ አንድ ሰው፤ “መንግሥት የእኔ አራት አመት እዳ አለበት፡፡” አለ ይባላል፡፡) ዜጐች በደል ሲበዛባቸው፣ ኑሮ ሲከብዳቸው፣ አገልግሎታቸው ዋጋ ሲያጣ፣ ባለስልጣናቱን፣ ሹማምንቱን ማማረራቸው አይቀርም፡፡ “አቀማመጥ አበላሽተው ከአሳላፊ ይጣላሉ” እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ “ሌባ ሌባ” እያለች ታስራ ስትጮህ ተኝተው ለሌባው እድል የሰጡ የተሰረቁ ባለቤቶች፣ ጠዋት ውሻዋን እየደበደቡ፤“ይቺ ውሻ ናት ያሰረቀችን” ሲሉ፤ “ጮኸን ጮኸን እንዳልጮህን ሆንን” አለች አሉ ውሻ፡፡ ይሄም ያስኬደናል፡፡ ውሻ እንደ አሳላፊው መሆኗ ነዋ!!


Read 4290 times