Saturday, 25 June 2016 12:39

የዝነኞች አሰላለፍ - በእንግሊዝ ህዝበ ውሳኔ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እንግሊዝ በአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ትቀጥል ወይስ አትቀጥል የሚለው አወዛጋቢ ጉዳይ፣ከትናንት በስቲያ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ እልባት አግኝቷል - እንግሊዝ ከህብረቱ አባልነቷ ወጥታለች፡፡ የእንግሊዝ የአውሮፓ ህብረት አባልነት ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ጉዳይ፣ የአገሪቱን ብቻ ሳይሆን የሌሎች የዓለማችን አገራትን ታዋቂ ፖለቲከኞች ጭምር ለሁለት ከፍሎ ሲያሟግት ነበር የከረመው፡፡ ጉዳዩ የፖለቲከኞች ብቻም አልነበረም፡፡ በተለያዩ የሙያ መስኮች አለማቀፍ እውቅናን ያተረፉ እንግሊዛውያንና የሌሎች አገራት ዝነኞችም፣የህዝበ ውሳኔው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ትቆይ እና ትውጣ የሚል አቋማቸውን በየአጋጣሚው ሲገልጹ ነበር የሰነበቱት፡፡
ከህብረቱ ጋር ትቀጥል ባዮች
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ከ250 በላይ ታዋቂ የአገሪቱ ድምጻውያን፣ የፊልም ተዋንያን፣ ደራሲያንና ሰዓሊያን እንግሊዝ በአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ትቀጥል የሚለውን አማራጭ በመደገፍ፣ ፊርማቸውን ከማሰባሰብ አልፈው፣ እንግሊዛውያን ከጎናቸው እንዲቆሙ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ጥሪያቸውን አቅርበው ነበር፡፡ አልተሳካላቸውም እንጂ፡፡  
የጄምስ ቦንዱን ዳኔል ክሬግ ጨምሮ፣ዴቪድ ሞርሲ እና ጁሊየት ስቴቨንሰንም የዚህ አቋም ደጋፊዎች የነበሩ የእንግሊዝ ዝነኛ የፊልም አክተሮች ናቸው፡፡ ዝነኛው ድምጻዊ ኤልተን ጆንም እንግሊዝ በህብረቱ አባልነቷ እንድትቀጥል ነበር ፍላጎቱ፡፡  
እንግሊዝ በአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ትቀጥል የሚል አቋማቸውን በይፋ ከገለጹና በህዝበ ውሳኔው ላይ ድምጻቸውን ከሰጡ እንግሊዛውያን ዝነኞች መካከል ታዋቂዋ የሃሪ ፖተር ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ ተጠቃሽ ናት፡፡ እንደ እሷ ሁሉ የአገሩን በህብረቱ አባልነቷ መቀጠል የደገፈው ሌላው እንግሊዛዊ ደግሞ ታዋቂው እግር ኳስ ተጫዋች ዴቪድ ቤካም ነበር፡፡ ሞዴልና ድምጻዊት ሚስቱ ቪክቶሪያም፣ የባሏን ሃሳብ ደጋፊ ነበረች፡፡
የአርሴናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር፣ ታዋቂው እንግሊዛዊ ድምጻዊና በጎ አድራጊ ሰር ቦብ ጌልዶፍና የኤክስ ፋክተር ውድድር ዳኛው ሲሞን ኮዌልም፤ ከህብረቱ ጋር ብንቀጥል መልካም ነው ባዮች ነበሩ፡፡
ከህብረቱ ትነጠል ባዮች
ከህዝበ ውሳኔው ውጤት አስቀድሞ ለሃገሬ የሚበጃት ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ብትወጣ ነው የሚል አቋም የያዙ ዝነኞችም በርካታ ነበሩ፡፡ ታዋቂው እንግሊዛዊ የፊልም ተዋናይ ሰር ማይክል ኬን ተጠቃሽ ነው፡፡
የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰላፊ ሶል ካምቤል እና ሌላው የሙያ አጋሩ የቀድሞው የብሄራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ጄምስም፤ተመሳሳይ አቋም ከነበራቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ብትወጣ ይበጃታል ብሎ የነበረው ሌላው ዝነኛ ደግሞ ጁሊያን አሳንጄ ነው፡፡ ይኸው እንግሊዝ ከህብረቱ አባልነቷ ወጥታለች፡፡




Read 2080 times