Saturday, 25 June 2016 12:38

‘እልፍ ሲናፈቅ’.... ‘Longing for the Eternal’

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የዚህ ዓምድ ትኩረት ሥነ-ጥበብ፡ በዋነኝነትም የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ነው። በተለይም ዘመንኛው(Contemporary) የኢትዮጵያ
ሥነ-ጥበብላይ አጽንኦት በመስጠት ወቅታዊና በመታየት ላይ ያሉ ትርዒቶችን ይዳስሳል፡ ገለጻ ያቀርባል፡ ያትታል፡ ይመረምራል፡ ሂስ
ያቀርባል። ግለሰቡን ሳይሆን ስራውን በመተቸት የሂስ ባሕልን ለማዳበር ይጥራል፡፡ የዓምደኛውን እይታ መሬት በያዙና ሚዛን በሚደፉ
አመክንዮች በማስደገፍ ግለሰብ አንባቢ ስለ ሥነ-ጥበብና ስለ ኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ግንዛቤ እንዲጨብጥ፡ የዕይታ ባሕሉ(Visual Culture)
እንዲዳብር፡ የሥነ-ጥበብ አድናቆቱ ከፍ እንዲል፡ ሥነ-ጥበብን የሕይወት ዘዬው(Life Style) አድርጎ እንዲወስደው መንገድ ለመክፈት
ይጥራል። በማኅበረሰብና በሃገር ደረጃም ልክ እንደ ኤኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊ፡ ማኅበራዊ፡ ባሕላዊና ትውፊታዊ እንዲሁም ታሪካዊ
እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሥነ-ጥበብን የሰፊው የሕይወት መር(Mainstream) አካል እንዲሆን ይተጋል።

የሥዕል ትርዒት ዳሰሳ (Exhibition Review)
የትርዒቱ ርዕስ፡
እልፍ ሲናፈቅ
ሠዓሊ፡
ደረጀ ደምሴ
የትርዒቱ አይነት፡
የግል፤ የቀለም ቅብ ስራዎች
ብዛት፡
15 የቀለም ቅብ፤ 7 የብዕር ቀለም
በወረቀት ላይ ስራዎች
የቀረበበት ቦታ፡
ጉራምዓይኔ የሥነ-ጥበብ
ማዕከል(ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ፡
ወደ አፍንጮ በር በሚወስደው
መንገድ፣ ከሰባ ደረጃ ፊት ለፊት፡
ለመጎብኘት ከማክሰኞ-እሁድ ከጠዋቱ 4:00-
ምሽቱ 12:00 ለአቅጣጫ+251911702953)፡
አዲስ አበባ
የሚታይበት ጊዜ፡
ከግንቦት 18-ሰኔ 27, 2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡
ሚፍታ ዘለቀ(የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
እልፍ ሲናፈቅ

ሠዓሊ : ደረጀ ደምሴ፡፡ ርዕስ፡ ጀምበር፡፡ የአክሬሊክ ቀለም በሸራ
ላይ፡፡ መጠን፡ 70 X 90ሳ.ሜ፡፡ 2008 ዓ.ም

የሰው ልጅ ፍጥረቱና ሕይወቱ ብቻውን እንዳልሆነ፤ ብቻውንም እንደማይቀጥል አመላካች አመክንዮዎች፣ ገዥ ስሜቶችና ሃሳቦችን መደርደር ይቻላል፡፡ ሆኖም፡ ዝንጋኤው ሲበረታ ሁሉን እየረሳ ‘ብቻውን’ አንግሶ ለመኖር ይታትራል፡፡ ‘የብቻ’ ንግስናው ባዶ መሆኑን ሲረዳ ደግሞ ‘እኔ’ ማለቱን ገሸሽ አድርጎ፣እኔነትን ለመጋራት ከመሰሎቹ የሰው ልጆች፣ የአካባቢውን፣ የተፈጥሮውን፣ የባሕሉን አውራ (aura) ለመላበስ ይማስናል፡፡ ሚዛኑን ለመጠበቅ ይሟሟታል፡ በዚያውም ይኗኗራል፡፡ እንዲህ እንዲያ እያለ እዚህ ደርሰናል፡፡
ይህ የሠዓሊ ደረጀ ደምሴ ‘እልፍ ሲናፈቅ’ የተሰኘውን የሥዕል ትርዒት፣ መረዳት የሚያስችሉን መሰረታዊ እሳቤዎች እነሆ፡
እልፍ፡ ተቆጥሮ የማያልቅ፣ ጊዜ የማይሽረው፣የማይቆም፣ የሚሻገር፣ የማይሞት፣ የዘልዓለማዊነት ኅላዌ ያለው እሳቤ ሁሉ እልፍ ሊባል ይችላል፡፡ እልፍነት በሰው ልጅም ሆነ በተፈጥሮ ላሉ፤ የሰው ልጅ በፈጠራቸው ቁስ አካላትም ሆነ እሳቤዎች ውስጥም መገኘት ይችላል፡፡ ደረጀ እልፍነትን በተለያዩ መንገዶች በስራዎቹ ሲያስስ የኖረ ሠዓሊ ነው፡፡ የተመስጦውን ትኩረት የሰው ልጅ ከአካባቢው በተለይም ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ትስስር እንዲያጤን በመግራት፣ስራዎቹን ሲያበራይ ከአስራ አምስት አመታት በላይ ዘልቋል፡፡ ይህን እሳቤ ማብላላት ሲጀምር ቅርብ ከሆኑ ባሕላዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ ተፈጥሮአዊና ሌሎች ሁነቶችን መሰረት አድርጎ ነበር፡፡ ጸበል አንደኛው ነው፡፡
ኃይማኖታዊ መሰረቱ እንዳለ ሁሉ፣ ከተጠናወታቸው እኩይ መንፈስ ለመንጻትም ሆነ ጥሩ መንፈስ ለመላበስ ሰዎች ጸበል ይጠመቃሉ፡፡
 በውሃ የመዳን ሚስጥርን የመረዳት ብሎም የማጥናት ፍላጎቱ የሰው ‘ሰውነት’ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ተዛምዶ በጥልቀት እንዲመረምር ወገግታ ሆነው፡፡ የስራዎቹን መነሻ ወደ ኋላ ተመልሰን ለማየት ከሞከርን ደግሞ የልጅነት እድገቱንና በሥነ-ጥበብ ት/ቤት ቆይታው አማካኝነት የገጠመውን መቃኘት ይኖርብናል፡፡  
የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ጉለሌ(ፓስተር፡ ሸጎሌና) ቀራኒዮ አካባቢዎች ሲሆን የሁለተኛ አመት ተማሪ ሳለ በውሃ ቀለም መልክዓ-ምድር እንዲስሉ የቤት ስራ ይሰጣቸዋል፡፡ ደረጀ ሸጎሌን ነበር የመረጠው፡፡ ቦታው ሲደርስ ግን የሚያውቃቸው ዛፎች ተቆርጠው፤ ውሃዎች ቆሽሸው፣ ያ የሚያውቀው ቦታ ተቀይሮና ሸጎሌ ‘ጉድ’ ሆና ነበር የጠበቀችው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያቱ ደግሞ ብዛት ያላቸው ሰዎች አካባቢው ላይ በመስፈራቸው ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ተፈጥሮ፣ የሰው ልጅ አድራጐትና መልክዓ-ምድር ያላቸውን ግንኙነት እንዲፈትሽ እድል ሰጥቶታል፡፡ ይበልጡን ግን የተፈጥሮ ኃያልነት የተገለጸባቸው ቦታዎችን እንዲናፍቅ አድርጐታል፡፡
ጸበል ውሃ፣ መልክዓ-ምድር፤ መልክዓ-ምድርና የሰው ልጅ ማንነት፤ አንደኛው ሌላኛው ላይ ያላቸው በጎም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ፤ ማንነትን ከኖርንበት አካባቢና ከተፈጥሮ ጋር ማዛመድና ዝምድናውን መፈተሽ፤ኑሮና ሕይወትን ከአካባቢና ከተፈጥሮ ጋር በማያያዝ ማንነትን በመፈለግ ጉዞ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማሰስ የደረጀ ጥበባዊ አሻራ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ ይህም ሲሆን አንዳች ያልተጨበጠ፡ ነገር ግን ያለና ሕያው የሆነ እሳቤ ላይ ለመድረስ የሚያደርገውን ትግል በስራዎቹ መመልከት እንችላለን፡፡ የመስተጋብሮቹንም ሚስጥራዊነት ያመላክተናል፡፡ ይህንንም የሚከውነው የመስተጋብሩን የእልፍነትና የዘላለማዊነት ክብደት በብርቱ  የሚወክሉ  በተፈጥሮ የሚገኙ ቅርጾችን በመጠቀም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለምሳሌ ከቅርጹ፡ ከአገነባቡ ጀምሮ ለአርባ አመታት አገልግሎ ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ የሚፈርሰው የዶርዜ ባሕላዊ የቤት አሰራርን የሰው ልጅ ራሱ የፈጠራቸውና ከተፈጥሮ ጋር በሚዛንና በስምምነት ለመኖር ለሚያደርገው ጥረት እንደ አንድ ማሳያ አድርጎ በማጥናት የስራዎቹ አካል ያደርጋቸዋል፡፡ ስራዎቹ እልፍ የሆነው የሰው ልጅ ፍላጎት፣አካባቢውንና ተፈጥሮን ለመቆጣጠርም ሆነ ተስማምቶ ለመኖር የሚያደርገውን ሙከራ ያስቃኘናል፡፡ የተፈጥሮና የሰው ልጅ መስተጋብር እልፍነትን ለአመታት ሲያጠናና ሲዳስስ ቢኖርም፣ የሁለቱ ኅላዌ ሌላ እልፍ አእላፍ ተመስጦና አድማስ ይከፍትለት እንጂ መቋጫ አበጅቶለት፣አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ይሆናል የሚል አይነት ድምዳሜ አያስቀምጥም፡፡ ምናልባት ሂደቱና ዑደቱ ላይ የደረሰባቸውን መገለጦች እያበረከትልን ይሆናል እንጂ! በዚሁ ግን የተፈጥሮና የሰው ልጅ መስተጋብር ኅላዌ በእልፍ አእላፍ፡ ዘላለማዊ፡ የጊዜ ገደብ በሌለው፡ ጊዜ በማይሽረው ፍስሰት መታጀቡን ያስታውሰናል፡፡የሰው ልጅ ፍጥረትና ሕይወት ብቻውን እንዳልሆነ አበክሮ ያሳስበናል፡፡ ከየትኛውም ቦታ በሚታዩ ተራሮች በታጠረችውና በማያቋርጥ ግንባታ አበሳዋን እየበላች ባለችው አዲስ አበባ መሐል ቢኖርም፣ በልጅነት ያሳለፈባቸው ከከተማው ዳር የሚገኙት አካባቢዎች በዕዝነ ልቦናው መቆየታቸው፣ ተፈጥሮን በቅርበት እንዲያስታውስ ምክንያት እንደሚሆነው ማገናዘብ፣ ስራዎቹ በዚህ እሳቤ እንዲቆዩ አጋዥ አመክንዮ ነው፡፡  
የዚህ ትርዒት ዋነኛ ትኩረት ደግሞ ይህ እልፍ የሆነው የተፈጥሮና የሰው ልጅ መስተጋብር፣ በዘመንኛዊ የኑሮና የሕይወት ጅረት ውስጥ መስተጋብሩ እየሳሳ፡ እየቀጠነ፡ እየላላና እየደበዘዘ የመጣበትን ሂደት የሚያመላክቱ አዲስ መልክ ያላቸው ስራዎቹንና ከጀርባቸው ያሉ ምክንያቶችን መዳሰስ ነው፡፡
ዘመንኛዊው አኗኗራችን ከደረስንበት የስልጣኔ ምጥቀት ተቃራኒ በሆነ መልኩ ከተፈጥሮ ጋር ያለንን ዝምድና ይበልጥ ከማቅረብ ይልቅ እያራቀው፡ እየገፋውና እየሸሸው ይገኛል፡፡ እልፍ የሆነው ቁርኝት፣ እልፍ ወደሆነ ተጓዳኝነት እየተለወጠ ይመስላል፡፡ ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ እሳቤዎች በእያንዳንዷ የዘመንኛዊ ኑሮአችን ጠብታ ውስጥ በጉልህ ይስተዋላሉ፡፡ ለዘመንኛዊ ኑሮ ወሳኝ አድርገን ከምንቆጥረውና ከምንደክምለት መሃከል ቁስ ዋንኛው ነው፡፡ በኑሮ ሂደት ውስጥ ያለቁስ መኖር የማይቻል በመሆኑ፣ የቁስ ሃብት መሰረታዊና አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ትኩረታችን ወደዚህኛው ሚዛን እየደፋ፣ሌሎች እኩል ወይም በላጭ ዋጋ ላላቸው እሴቶች የምንሰጠው ቦታ እዚህ ግባ የማይባል እየሆነ ከመምጣቱም ባሻገር፣በሚታይና በማይታይ መልኩ ጉዳት እያስከተለብን ይገኛል፡፡ እንገነባለን፡ ነገር ግን ግንባታችን እስከ ምን እንደሆነ አይታሰበንም፡፡ በተለይ በሃገራችን ዓውድ፣ቁስ ለመሰብሰብም ሆነ ለመገንባት ያለን ጥማት ሌሎች ነገሮችን ለማሰብ እድል ሳይሰጠን፣የዕውር ድንብራችንን እየዳከርን እንገኛለን፡፡ በዚህም እልፍ የሆነው የተፈጥሮና የሰው ልጅ ቁርኝት፣ እየላላና እየደከመ ብቻ ሳይሆን አቅጣጫውን እየሳተ፣ ጉዳቱ እየበረታ መምጣቱን ይጠቁማል፡፡
አዳዲሶቹና የቅርብ ጊዜ የደረጀ ስራዎች፣ይህን እውነት እንደ ተረት ተረት አይተርኩልንም፡ እንደ መረጃም አያባንኑንም፡፡ ይልቅስ ከዚህ በፊት እንደሚሰራው ሁሉ በቅርጽ ደረጃ አንድም ነገር ሳያጓድሉ፣የተፈጥሮና የሰው ልጅ ቁርኝትን ከሚወክሉ ሃሳባዊ፣ ስሜታዊ፣ ባሕላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ትውፊታዊ፣ ሃገራዊና ተፈጥሮአዊ እሳቤዎች ጋር እያሰናኘ፣ የስራዎቹን የለውጥ መንፈስ እንድናጤንና እንድንመረምር ይጋብዘናል፡፡ እራሳችንን ስራዎቹ ውስጥ እንድንከት መስህብ ያላቸው የድርሰት አወቃቀሮችን፡ ውሳኔውን እንድንረዳ የሚያግዙና የቁርኝቱን እልፍ አእላፍነት አመላካች የሆኑ መስመሮችን እየዘረጋልን፡ ግዘፍ የሚነሱ ተፈጥሮአዊ ቅርጾችን እያተወልን፤እነዚህን ሁሉ የተፈጥሮና የሰው ልጅን መስተጋብር የሚያትቱ ውህዶች በዘመንኛዊ አኗኗራችን እየሳሱ፡ እየሰለሉና እየበነኑ መምጣታቸውን ደግሞ በተቆጠቡ ቀለማቶቹ ይጠቁመናል፡፡ የመስተጋብሩን ሚስጥራዊነት፤ የሚስጥራዊነቱን ጥልቀትና ርቅቀትም ሹክ ይሉናል፡፡
ናፍቆት የሰው ልጅን ስሜት፣ ሃሳብ፣ ነብስ፣ ስጋ፣ መንፈስና ባጠቃላይ ሕልውናውን የሚያዳክምና የሚያዝል ኃይል አለው፡፡
በሌላ ጎኑ፡ ናፍቆት የብርታት፣ የጽናትና ማንነትን የማስታወስ ልዩ ብቃትም አለው፡፡
የወደፊቱንም እንድናስብ፡ እንድንቀምር፡ እንድንናፍቅ ያነሳሳናል፡፡
 ናፍቆት የተቃርኖ ውጤት ነው፤ አንድም ካለንበት እውነታ ባሻገር እንድናይ፡ አንድም ባለንበት እውነታ ብቻ ሳንወሰን፣ አስፈላጊ የሆነውን ግን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች  ልናገኘው ባለመቻላችን እንድንናፍቅ፣እንድንፈልገው እንድናስበውና እንድንጓጓለት የሚያደርግ፡ ናፍቆታችንን እንድናረካ፣ በሰላ አእምሮ እንድናስብና አስፈላጊውን መስዋዕት እንድንከፍል የሚያጸና ኃይል አለው፡፡
ናፍቆት የሰው ልጅ ፍጥረቱና ሕይወቱ ‘ብቻውን’ እንዳልሆነ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ጉዞው ጤነኛ እንዲሆን ሊያካትተው የሚገባቸውን መስተጋብሮች ልብ እንድንል፡ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ያስታውሰናል፡፡ ደረጀ በተለይ በዘመንኛዊ አኗኗራችን ውስጥ እልፍ የሆነውን የተፈጥሮና የሰው ልጅን ዑደት ሲያሰላስል፣ ከአኗኗራችን የጎደለ ነገር እንዳለ፡ መጓደሉ እንደታወቀውና እንደተሰማው ብቻ ሳይሆን፣ ያ እልፍ ዑደት እንደናፈቀው ከአዳዲሶቹ ስራዎቹ መረዳት እንችላለን፡፡
 እልፍ ናፍቆት፡ እልፍ እንድናስብ የሚኮረኩሩ ስራዎች አቅርቦልናል፡፡
 እልፍ ሲናፈቅ ምን እንደሚመስል ማየት፣ መረዳትና ማጤን የኛ ድርሻ ነው፤ልብ ያለው ልብ ይላል!
ቸር እንሰንብት!









Read 1196 times