Saturday, 25 June 2016 12:35

አንጋፋው ደራሲ፤ ስለ አንጋፋው ሃያሲ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“በአብደላ ህልፈት ያዘንኩት ለሥነጽሁፋችን ነው”



አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ከሦስት አሰርት ዓመታት በላይ በዘለቀው የደራሲነት ዘመኑ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎችን
ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከእነሱም መካከል ”ሽበት”፣ “ሕይወትና ሞት”፣ “መቆያ”፣ “የማለዳ ስንቅ”፣ “አውጫጭኝ” (የግጥም ስብስብ)፣
“ሞያዊ ሙዳየ ቃላት”፣ “ጥሎ ማለፍ”፣ “ታሪካዊ ልቦለድ” እና በቅርቡ ደግሞ “ቅንጣት” የተሰኘው ሥራው ይጠቀሳል፡፡
ደራሲው በዚህ ቃለምልልስ የሚያወጋን ስለ ራሱና ሥራዎቹ አይደለም፡፡ ይልቁንም በቅርቡ በሞት ስላጣነው አንጋፋው ሃያሲ
አብደላ እዝራ ነው፡፡ ትውውቃቸው ከ30 ዓመታት በላይ ይሆናል፡፡ ሥነጽሁፍ ቢያስተዋውቃቸውም ግንኙነታቸውን ወደ ጓደኝነትና
ዝምድና አሳድገውታል፡፡ የአዲስ አድማሱ ደረጀ በላይነህ፤አንጋፋውን ደራሲ አበራ ለማን፣በአብደላ እዝራ ሥነጽሁፋዊ አስተዋጽኦ
ዙሪያ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

ከአብደላ ጋር የመጀመሪያ ትውውቃችሁ በየመን እንደነበር ስትናገር ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ እንዴት ነው የተገናኛችሁት?
በሕዳር 1974 ዓ.ም የመን ሰንዓ፣ በዐረብ ደራሲያን ማሕበር ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን ወክዬ ተገኝቼ ነበር፡፡ ያኔ ነው አብደላ እዝራ በቴሌቪዥን ሰምቶ ሊፈልገን የመጣው፡፡ በአረብ ደራሲያን ጉባኤ ላይ ከ23 ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች እንዳሉና ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበርም ተወካዮች መምጣታቸውን ሲሰማ፣ ሌላ መሀመድ የሚባል ጓደኛውን ይዞ ጉባኤው እሚካሄድበት ሸራተን ሆቴል ድረስ መጣ፡፡ እንግዳ መቀበያው ጋ ሄዶም፤“ኢትዮጵያዊ የጉባኤ ተወካይ መጥቷልና እባካችሁ አገናኙኝ” ይላል፡፡ ከዚያ የሆቴሉ ሠራተኞች፣ፍቃደኛነቴን   ጠየቁኝ፡፡
 እኔም፤“ኢትዮጵያዊ ብሎ የሚመጣማ!” ብዬ ያረፍኩበት ክፍል እንዲልኩት ነገርኳቸው፡፡ ሲመጡ ሁለት ወጣቶች ናቸው፡፡ ተዋወቅን፡፡ አማርኛቸውም በጣም የሚገርም ነው፡፡ ከዚያ አብደላ አባቱ የመናዊ እንደነበረና ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያርፍ፣ ቤተሰቦቹ ወደ የመን እንደመጡ ነገረኝ፡፡ መሀመድ የሚባለውም እንደሱ ግማሽ ኢትዮጵያዊና ግማሽ የመናዊ ነው፡፡
ይህን ከተነጋገርን በኋላ እንዴት ልትፈልጉኝ መጣችሁ? ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ “እኔ ለሥነ ጽሑፍ ፍቅር ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ስብሀትን ታውቀዋለህ?” አለኝ፤አብደላ፡፡ “ወዳጄ ነው” አልኩት፡፡ ስለ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ስለ በዓሉ ግርማ አነሳ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ብዙ ያውቅ ነበር፤ በጥልቀትም አወራኝ፡፡ በመጨረሻ ፖስታ ሳጥን ቁጥር ተለዋውጠን ተለያየን፡፡
እዚህም ከመጣሁ በኋላ የሚፈልጋቸውን መጽሐፎች በሙሉ በፖስታ ቤት ላኩለት፡፡
የተላኩለትን መጽሐፍት አንብቦ በተለይ “ሕይወትና ሞት” የሚለውን የኔን መጽሐፍ ተንትኖ፣ ለ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላከውና ወጣለት፡፡ መጽሐፉ በድህረ አብዮት የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ ነበር፡፡ አብደላ አልአራሲ እያለ ነበር የሚፅፈው፡፡ አልአራሲ የቤተሰቡ ስም ነው፡፡ በኋላ ነው አብደላ እዝራ እያለ መጠቀም የጀመረው፡፡
በዚያው መፃፉን ቀጠለ፡፡ ከሰንዓ እያለ ሲፅፍ አንባቢ፤“ማነው?” ማለት ጀመረ፡፡ አማርኛው ረቂቅ ሆነባቸው፡፡
በጣም ታዋቂና ተወዳጅ ሆነ፡፡ እዚህ ሲመጣ ቀጥታ ወስጄ ከእነ ደበበ ሰይፉ፣ ከእነ ጋሽ አማረ ማሞ ጋር አስተዋወቅሁት፡፡ ከብዙ ደራሲያን ጋር ተዋወቀ፡፡ ለ”ዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ፣ ለ”የካቲት” መጽሔት ፅሁፍ መላክ ጀመረ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ደራሲያንና ሥነ ጽሑፍ አምባ ጠልቆ ገባ፡፡ እሱ ግን እንደ ሌላው የሥነ ጽሑፍ ሰው ዝነኛ ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም፡፡
በላቀ ደረጃ ሰርቷቸዋል ብለህ የምታስታውሳቸውን ስራዎች ልትጠቅስልኝ ትችላለህ?
“ኦሮማይ” በታተመበት ጊዜና “ጥቁር ደም” የሚለውን የአንዳርጌ መስፍን መጽሐፍ እኔ፣ መስፍን ሀብተማርያምና እሱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ጥልቅ ትንተና ሰጥተንበታል፡፡ እሱን አልረሳውም፡፡ “ጥቁር ደም” ላይ ብቻውንም የሰጠው ትንታኔ ነበር፡፡ ከሀይሉ ልመንህና ከደረጀ ጥላሁን ጋር በጥልቀት ነበር ያወራው፡፡
በአጫጭር ልቦለዶች ጎራ እነ አዳም ረታ የመሳሰሉትን አደባባይ ላይ ለማውጣት ትልቁን ድርሻ የተጫወተው አብደላ እዝራ ነበር፡፡
 ለኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ዕድገት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ በእነ ሲሳይ ንጉሱ “ሰመመን”፣ በጋሽ በዓሉና በሌሎች ላይ ብዙ ሰርቷል፡፡ ወደ ግጥሞች ከመጣን፣ እርሱ አሻራውን ያላሳረፈበት አይነ ግቡ የሆነ ግጥም የለም፡፡
ሌላው ትልቁ የአብደላ ስራ ወጣቶችን ማበረታታት ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ያኔ በደራሲያን ማሕበር ዙሪያ ይሰባሰቡ ነበር፡፡
እዚያ የሚመጡትን ወጣቶች ለማወያየትና ለማበረታታት ጊዜውን ይሰጥ ነበር፡፡ እኔ ህዝብ ማመላለሻ በምሰራበት ወቅት ከስራ ውጭ የነበረው ጊዜ ሁሉ የእነርሱ ነበር፡፡ የእረፍት ሰዓት ሳይቀር ለወጣቶች የተሰጠ ነው፡፡ እነ “ፍካት”ን የመሳሰሉትን ማህበራት እየተረዳዳን እናሰለጥን ነበር፤ያልተሞከረ ነገር አልነበረም፡፡
ከአንጋፋዎቹስ ጋር እንዴት----ነበር?-
ከእነ ደበበ ሰይፉ ጋር ውይይት ማድረግ ይወድ ነበር፡፡ አብደላ ደስ የሚለው ዘር አይመርጥም፣ ፆታ አይመርጥም፣ ሃይማኖት አይመርጥም፡፡ ለሁሉም ቅን ሆኖ ስራዎቻቸውን የሚታደግ ሰው ነበር፡፡ ለሁሉም ራሱን ዘግኖ ሲሰጥ የኖረ ሰው ነው፡፡ እንደ ሰብዓዊ ፍጡርም ብዙዎችን ይረዳ ነበር፡፡ ወጣቶችን የሚያግዝ፣ የኢኮኖሚ ችግር የነበረባቸውን እንደ ጋሽ ስብሀት ገብረ እግዚአብሔር ያሉ ሰዎችን የሚታደግ ሰው ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ወዳጆቹን ከነቤተሰቦቻቸው ሲደግፍ ነው የኖረው፡፡  
የእኔን ልጆች ስም ያውጣውም እርሱ ነው፣ የመጀመሪያ ልጄ “መቅድም”፣ ሁለተኛዋ “ምስጢር” ነበር ስማቸው፡፡ ሁለቱንም ቀይሮ ሶስና እና ፌቨን ብሎ አወጣላቸው፡፡ ሁለቱንም ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ እስከ አሁንም የሚጠሩት እሱ ባወጣላቸው ስም ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም ተንከባክቦ ያሳደጋቸው እርሱ ነው፡፡ እንደ አጎት በፍቅር ነው ያሳደጋቸው፡፡
እንዳልከው አብደላ፣በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበረው ሰው ነው፡፡ የእሱ አለመኖር ትልቅ ክፍተት አይፈጥርም ?
ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ አብደላ ባህር የሆነ ክፍተት ነው የሚፈጥረው፡፡ ምክንያቱም የእርሱ ሂሳዊ ንባብ አካሄድ ለየት ያለ ነው፡፡ “ቼሆቪያን አይ” (Chekovian eye) ይሉታል ፈረንጆቹ፡፡ ቼሆቭ የአጭር ልቦለድ ደራሲ ነው፡፡
የሚያነሳቸው ጭብጮችና ጉዳዮችም ሌሎች ሰዎች የማያዩትን ነው፡፡ አብደላ የቼሆቭን አይነት ምልከታ፣ ራዕይ ያለው ሰው ነው፡፡
ሕይወትን ነቅሶ ሲያወጣ፣ ከተደበቀችበት ጎልጉሎ አውጥቶ ፀሐይ ላይ ሲያሰጣት አቻ የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ አምባ እንደዚህ አይነቱን ሰው ማጣት በጣም ት-ል-ቅ ት-ል-ቅ  ጉዳት ነው፤ያንን ክፍተት እንዴት በዘመናት ውስጥ እንደምንሞላው አላውቅም፡፡
 በተለይ ግጥምና አጫጭር ልቦለድን ደፍሮ የሚያሄስ ሰው የለም፡፡ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ እርሱ ደግሞ ከጥቂቶቹም ላቅ ያለውን ቦታ የያዘ ነበር፡፡
አዲስ አድማስ ላይ “ተናዳፊ ግጥም” በሚል አንዳንድ ዘለላ ግጥሞች እየመረጠ ሲያቀርባቸው የነበሩ ትንተናዎችን ስንመለከት፣አዲስ መንገድ ነው ያሳየን፡፡ በመጨረሻ ያነበብኩት በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ግጥም ላይ የሰራውን ትንተና ነበር፡፡ እና አንድ አብደላን ብቻ አይደለም ያጣነው፡፡ ብዙ ዓይነቱን አብደላ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አብደላ ምስጢር የሆነ ሰው ነው፡፡ ገና ተገልጦ ያላለቀ ቅኔ፡፡ እርሱ ስለ ሌሎች ሲጨነቅ ውጫዊ ማንነቱን እንጂ ውስጡን አናውቅም፡፡ ውስጡን ጠልቀህ ማወቅ አትችልም፡፡ አብደላ ረቂቅ ሰው ነው፡፡ በአንድ በኩል የፊዚክስ፣ በሌላ በኩል የሂሳብ፣ ጥሩ የቴክኖሎጂ እንዲሁም የባዮሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው ነበር፡፡ ስለ ሃይማኖት ብታወራው፣ጥልቅ ትንታኔ ሊሰጥ የሚችል ሰፊ ገበታ ነው፡፡ ግን ባልጠበቅነው ሰዓት ሞት ድንገት ከእጃችን ነጠቀን፡፡ ያዘንኩት ገና ማደግ ላለበት ሥነ ጽሑፋችን ነው፡፡ ብዙ ትሁት ሃያሲያን በሌሏት፣ አንዱን ገድሎ፣አንዱን አድኖ ማኄስ በተለመደባት ሀገር ላይ፣እንደ አብደላ ዓይነት ከቡድን አስተሳሰብ ነፃ የሆነ ሰው ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ሚዛናዊ ሰው ማጣት በእጅጉ ይጐዳል፡፡
ይሄን ታላቅ የጥበብ ሃያሲ ለማሰብና ለመዘከር ምን መደረግ አለበት ትላለህ?
አሁን ይህን ሰው አንመልሰውም፡፡ ይልቅ የእርሱን ብሄራዊ ተዋፅኦ፣ የእርሱን የሀገር ፍቅርና የሥነ ጽሑፍ ፍቅር ለማስታወስ፣ ለእርሱ መታሰቢያ የሚሆኑ ነገሮች መስራት ይኖርብናል፡፡ ከነዚህም አንዱ ስራዎቹን ሰብስቦ ማሳተም ነው፡፡ በደበበ ሰይፉ ስራዎች ላይ ጥናታዊ ዳሰሳ እየሰራ እንደነበር ነግሮኛል፡፡ እሱን አጠቃልሎት ከሆነ ማየት፣ካላለቀ ደግሞ የሚቋጭበትን መንገድ ---- ኮሚቴም ቢሆን አቋቁሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
አንዲት ሴት ልጅ ናት ያለችው፡፡ ገና ጨቅላ ስለሆነች ምን እናግዝሽ? እያልን በእሷ አስተባባሪነት የምንሰራውን ነገር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ለእርሷና ለቤተሰቧ ድጋፍ በመሆን፣ አብደላን ከመቃብር በላይ ለማዋል መሞከር ይኖርብናል፡፡ በየመን መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ብዙ የመፃህፍት ስብስቦች አሉት፡፡ መጻህፍቱ መጥተው ለእርሱ መታሰቢያ የሚሆን ነገር የሚበጅበትን ሁኔታ መፍጠርና በስሙ መሰየም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
 ይህን ዓይነቱን ስራ  እኔና አንተን ጨምሮ ሌሎችም በመሆን ከዳር ማድረስ ይጠበቅብናል ብዬ አምናለሁ፡፡  ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ወርክሾፖችና ሲምፖዚየሞች በስሙ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
ለእንዲህ ያለ ጉዳይ የኢትዮጵያ ደራሲያን በሙሉ ቅኖች ናቸው፡፡ ለብዙ ሰዎች ሲያደርጉት ስለነበር ለአብደላም የማያደርጉት ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ይህን ሰው ማሰብ ማለት፣ የራሳችንን ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ስለሆነ፣ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡




Read 2243 times