Saturday, 25 June 2016 12:33

አዲሱ መዝገበ ቃላት

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(27 votes)

… ከዛ ደግሞ አያፍርም… ቤቴ መጥተህ ካልዋልክ ብሎ ማጅራቴን አንቆ ወሰደኝ፡፡ ሁለት መኝታ ቤት ያለው አፓርትመንት ውስጥ ነው የምኖረው ብሎኝ ነበር፡፡ አፓርትመንቱ ኮንዶሚኒየም መሆኑን ሳይ .. ይኼ ልጅ ውሸታም ነው ለካ ብዬ በቅሬታ ገላመጥኩት፡፡ ምናልባት የነገረኝ ሌሎች ነገሮችም ውሸት ሳይሆኑ አይቀሩም ብዬ ተጠራጠርኩኝ፡፡ እንደተቀየምኩት የገባው አልመሰለኝም፡፡
በቁልፍ ከፍቶ ገባ፡፡ ጣቷ ላይ ቀለበት የሌላት ሚስቱ ከጓዳ ተንደርድራ መጣች፡፡ ከእኔ አስቀድማ ወንዱን ልጄን ሳመችው፡፡ ከዚያ ከእኔ ጋር እየተዋወቀች፣ ባሏን ደረቱ ላይ በቡጢ መታችው፡፡ እሱም  ቂጧ ላይ በካልቾ አቀመሳት፡፡ ቀጥለው ተቃቀፉ፡፡ ወንድ ልጄን ይዤው ስመጣ በጣም ረጅም ማስጠንቀቂያ ሰጥቸዋለሁ፡፡ አፉን እንደለመደው እንዳይከፍት፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው ቤት ይዤው መሄድ የማልወደው፣አፉን መሰብሰብ ስለማይችል እንዳያዋርደኝ እየፈራሁ  ነው፡፡
ሁላችንም ሶፋዎቹ ላይ ተቀመጥን፡፡ ከአባወራው ጋር ማውራት ያዝን፡፡ ሚስትየዋ ደግሞ ልጁን እያጫወተችው ነው፡፡ ምንም ነገር የማያውቅ መሆኑን አምና ነው እንደ አአምሮ ዘገምተኛ ቃላቶቿን እንዳይጠባበቁ እየለያየች የምታወራለት፡፡ ከእድሜው በላይ የነቃ መሆኑ አልገባትም፡፡
“ልጆችሽን የት ነው ያስቀመጥሻቸው?” ሲላት እኔ ተሸማቀቅሁኝ፤ ባል እና ሚስቱ ሳቁ፡፡
“ገና ሆዴ ውስጥ ናቸው” አለች፤ቀለበት ያላደረገችው ሚስት፡፡
ሚስት ማግባቱን ነበር አባወራው የነገረኝ፤ሆኖም ነገረ ሥራቸው ትዳር ላይ ያሉ አልመስልህ አለኝ፡፡ ከአባወራው ጋር በአንድ ሰፈር ውስጥ እንኖር በነበረ ወቅት በአይን እንተዋወቃለን ግን አንቀራረብም፡፡ የድሮው ሰፈር ፈርሶ ሁሉም በየፊናው ከተበታተነ ከአመታት በኋላ የድሮው የአይን ትውውቃችን ሁለታችንን እንደ ዘመዳሞች አስተቃቀፈን፡፡
ስለዚህ ስለሱ የማውቀው ብዙ ነገር የለም፡፡ ስሙንም አልያዝኩትም፡፡ እሱም ስሜን የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ ግን እሱም እኔም በጣም የምንተዋወቅ መስለን ሳንተዋወቅ ያሳለፍናቸውን ጊዜያት መርሳት ስለነበረብን ወደ ኋላ ተመልሼ፤“ግን ስምህ ማን ነበር? ዘነጋሁት” ለማለት አፈርኩኝ፡፡
“ስራ እንዴት ነው?” ሲለኝ፣ “የምን ስራ?” ልለው ይገባ ነበር፡፡ ግን “ጥሩ ነው” ብዬ አቀረቀርኩኝ፡፡ “የት ነው የምትሰራው ባቢ?” አለኝ ክፍት አፉ ልጄ፡፡ ስራ አጣሁ ብዬ እናቱ ላይ ሳለቃቅስ ነው የሚያውቀኝ፡፡ ስራ የሌለው አባት፣ ስም የሌለው አባት መሆኑን በደመነፍሱ ያውቃል፡፡
“አዲስ አበባ …” ብዬ ገና ሳልጨርስ ----
“አዲስ አበባ መስተዳድር?” ሲል አባወራው አፋጠጠኝ፡፡
“አዎ … እዛ ነው” አልኩኝ፡፡ ልጄ አዲስ ማንነቴን ያወቀ መሰለ፡፡
“መስተዳድር .. የት ነው?” አለኝ፡፡ ቀስ ብዬ እጁን ይዤ እየሳቅሁ፣በሀይል መዘለግሁት፡፡ ከቤት ስንወጣ የሰጠሁት ማስጠንቀቂያ ድንገት ትዝ ቢለው ብዬ፡፡
ልጄ ስማቸውን የሚያውቃቸው መስሪያ ቤቶች፣ ባንኮችና የቢራ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ እኔ ቢራ ጠጥቼ ማታ እንደምገባም ሆነ ባንክ ውስጥ ያስቀመጥኩት ብር እንደሌለኝ አያውቅም፡፡ አያውቅም ብዬ ራሴን አፅናናለሁ፡፡ ግን እኔን ስለማወቁ በንቀቱ አማካኝነት አሳቻ ቦታ ላይ ይገልጻል፡፡
ማንም ስለ ማንም አያውቅም፡፡ ግን የሚተዋወቅ መስሎ አንድ ሳሎን ውስጥ ተሰብስቧል፡፡ ወሬውን ከእኔ የስራ ቦታ ወደ ሌላ ለማስቀየር ስል፣ ግድግዳ ላይ የተለጠፈውን አንድ ሽንጠ  ረዥም ወረቀት ማጥናት ጀመርኩኝ፡፡ መጀመሪያ ሲታይ ዋጋ ያልተፃፈበት የምግብ ዝርዝር ይመስላል፡፡ በደንብ ሳተኩርበት ሌላ ነገር እንደሆነ ተረዳሁ፡፡
“ምንድነው ይኼ ነገር?” አልኩት፤ ስሙን የማላውቀውን አባወራ፡፡
ከአባወራው ቀድማ ሚስትየዋ መለሰችልኝ፤“ይኼ እኔና ጌትሽ የምንጠቀምበት መዝገበ ቃላት ነው”
የተናገረችውን ነገር ትርጉም ሳይሆን ጌትሽ የሚለውን ስም ያዝኩኝ፡፡ የአባወራው ስም ጌትሽ ነው…ማለት ነው፡፡ ጌትሽ ያስረዳኝ ጀመር፡፡ የሚጠጣ ምን ይምጣላችሁ? ብለው አለመጠየቃቸው አስገርሞኝ፣ የሚያወራልኝን በቅጡ እያደመጥኩት አልነበረም፡፡  
“ገባህ?” ሲለኝ … ጭንቅላቴን ነቀነቅሁኝ፤ግድግዳው ላይ የተለጠፈው ወረቀት ላይ በድጋሚ እያተኮርኩ፡፡ ምንም አልገባኝም፡፡
“ዱባይ” የሚለው ቃል ጎን የይሆናል ምልክት ተደርጎ፣ “ሱቅ” የሚል ተጽፏል፡፡ በይሆናል ምልክት መሀል የተቀመጡ ሁለት ቃላት ግራና ቀኝ ተደርድረዋል፡፡ ዝርዝሩ ረጅም ነው፡፡
ምክኒያት =     ገንዘብ
መጠጣት =     መበሳጨት
እስኪሪብቶ =     ዘመናዊ ማረሻ
ልኳንዳ =     አይንን የሚያጠቃ ኮሶ
እውቀት =     እንቅልፍ
ተስፋ =     ምርቃና
እውነት =     ድንክ
ውሸት =     ረጅም/ግዙፍ
ምንም ስላልገባኝ በራሴ እውቀት ተሸማቀቅሁ፡፡ የጌትሽን የትምህርት ደረጃ የሚያሳይ ፎቶ በሳሎን ቤቱ የለም፡፡ ፎቶአቸው ራሳቸው ሰዎቹ ናቸው፡፡ እንደኔ ልማቱ ባመጣው ግራ መጋባት የተኙ ናቸው ብዬ ደመደምኩኝ፡፡
“በጣም መበሳጨት አማረኝ” አለ ጌትሽ፤ወደ ሚስቱ ዞሮ፡፡
“ለመበሳጨት ስንት ምክኒያት አለህ?” አለችው፤ወዲያው ከአፉ ተቀብላ፡፡
 ኪሱ ውስጥ ገብቶ የመቶ ብር ኖቶች አወጣና፣ ሁለቱን መዝዞ ለሚስቱ ሰጣት፡፡
“ለመበሳጨት ምክኒያት ካለህማ … ማን ይከለክልሃል፤ብስጭት በል” አለችና ከሶፋው ተነስታ በሩን ከፍታ ወጣች፡፡
አይኔን ግርግዳው ላይ ወዳለው ዝርዝር መለስኩኝ፡፡
ልብ ወለድ = ህይወት
ኢየሱስ = የሚጠበቅ ግን የማይገኝ ምኞት
የተነጠፈ አልጋ = ሜዳውም ፈረሱም ይሄው
ዱብ እዳ = ቀረጥ
“እስቲ እንደገና ቀስ ብለህ አስረዳኝ” አልኩት ጌትሽን፡፡ “እንደገና” የሚለውን ቃል ዝርዝሩ ላይ ሳየው፤“በደነቆረ ጆሮ የሚሰማ ሙዚቃ” ይላል፡፡
“… አይ እኔና ሚስቴ የምንገለገልበት የራሳችን ቋንቋ ነው፡፡ … .ለምሳሌ በእኛ ቤት ህግ “አጭር እውቀት አገኘሁ” ማለት እውነተኛ እንቅልፍ ተኛሁ እንደማለት ነው፡፡ … “መበሳጨት አማረኝ” ስል “መጠጣት አማረኝ” ማለቴ ነው፡፡”
“እኮ ለምን ዝም ብለህ መጠጣት አማረኝ አትልም?”
“ምክኒያቱም ስጠጣ ነዋ እምበሳጨው … ጠጥቼ ያልተበሳጨሁበት ጊዜ ስለሌለ… እኔና ባለቤቴ ቃሉን ለውጠን እንጠቀምበታለን”
“አስገራሚ ነው … ግን በደንብ ትግባባላችሁ? … ማለቴ … ለምሳሌ የግል ስራን፣ ታላቁ ሩጫ ብለኸዋል፡፡ ምን ማለት ፈልገህ ነው?”
“በቃ … ሮጠህ ምንም የማታተርፍበት ድካም ነው ለማለት ነበር … ግን አሁን በቅርቡ በግሌ ሮጬ ደህና ገቢ ማግኘት ስለቻልኩ ምናልባት … በህይወቴ አንዴ ከሆነ የሚሳካልኝ ወይ “ኩፍኝ” እለዋለሁ፡፡ ካልሆነም “ፍቅር” ልለው አስቤያለሁ፡፡ …. ረግቶ የሚቆይ ትርጉም ያለው ቃል የለም፡፡ በምግብ ሜኑ ላይ የአንዱ ምግብ ዋጋ ባለበት እንደማይቆየው .. ለእኛ ቤት ደግሞ ቃላትም እንደዛ ናቸው፡፡” አለኝ፡፡
 ያው ልማቱ ያመጣው፣ ውጣ ውረድ የፈጠረው ችግር ነው ብዬ ዝም አልኩኝ፡፡ ሚስቱ ቢራውን ይዛ እስክትመጣ ጓጓሁኝ፡፡ ጉጉቴ የአካል ቅርፄን ለውጦ፣የባዶ ቢራ ጠርሙስ ያደረገኝ እስኪመስለኝ ድረስ፡፡
“እሺ ጌትሽ … እንዴት ነህ በተረፈ .. የድሮ ሰፈር ልጆችን ታገኛለህ?” አልኩትና በሌላ ቋንቋ ተናግሬ እንዳይሆን በሚል፣ግድግዳው ላይ ያለውን የቃላት ዝርዝር አሰስኩኝ፡፡
በሞት መለየት = እፎይታ
“ስሜ እኮ ጌትሽ አይደለም … ዛሬ ገንዘብ ስላለኝ ነው ሚስቴ ጌትሽ ያለችኝ … እውነተኛ ስሜ እንደ አለሁበት ሁኔታ የሚለዋወጥ ነው … ኪሴ ሲሞላ ጌትሽ፣ መጠነኛ ገንዘብ ሲኖረኝ “ምትኩ” እሆናለሁ … ገንዘብ እየጎደለ ሲመጣና አቅም ሲያንሰኝ “ዝግ - ያለው” … እባላለሁ … ድሮ የምታውቀውማ ቋሚ ስሜ ከቋሚ ማንነቴ ጋር ተሰረዘ ..” አለኝ፡፡
ሚስትየዋ መጣች፤ቢራ በፌስታል ሞልታ እያንኳኳች፡፡ ከቆርኪ መክፈቻ ጋር አንድ አንድ አውጥታ ሰጠችን፡፡ በዝምታ እንጎነጭ ጀመር፡፡ ክፍታፉ ልጄ፣ የሴት የወር አበባ መቀበያ ከቦርሳዋ መዞ “የማን ዳይፐር ነው ይሄ?” አለ፡፡
ሚስት ከተቀመጠችበት ተነስታ በግድግዳው ላይ ያለው ወረቀት ላይ፤ “ሞዴስ = የኮረዶች ዳይፐር” ብላ ፃፈች፡፡
“ጥሩ ትርጉም አይደለም…የኮረዶች ሳይሆን የሄዋኖች…ብትይው ይሻላል” ሲል ባሏ ቢያርማትም አልተስማማችም፡፡ ብዙ ተጨቃጨቁበት፡፡ የልጄን ጆሮ ሳያዩኝ እንዴ እንደምመዘልግ አስቤ ተቁነጠነጥኩኝ፡፡ ልጄ ነው እያልኩ አስተዋውቀዋለሁ እንጂ እኔን እንደማይመስል ሁሉ ነገሩ ያሳብቅበታል፡፡ እኔ የእሱን እናት ባገባ፣የእንጀራ አባቱ የመሆኔ ጉዳይ ነው የዘወትር ቅዠቴ፡፡
ባልና ሚስቱ ሲጨቃጨቁ ቆዩና ጌትሽ መፃፊያውን ነጥቆ፣እሷ ከፃፈችው ስር ሌላ አዲስ ቃል ከይሆናል ምልክቱ ጋር አሰፈረ፡፡
አቅመ ሄዋን = ጨቅጫቃነት
“ግን ቲና ቢራ አትጠጣ አላለችህም …?” አለኝ፤ልጄ ቢሆን ራሴን ከፎቅ ላይ እወረውርለት የነበረው የአራት አመት ፍጡር፡፡
“እንዳልመታህ አንተ” አልኩት፤ወደ ጆሮው ተጠግቼ፡፡
“እናገራለሁ…ትላንት ከሷ ቦርሳ የሰረቅከውንም ብር እናገርልሀለሁ” አለኝ ጮክ ብሎ፡፡ እንግድነቴ ድንገት አከተመ፡፡ በኩርኩም ደህና አድርጌ ደነቆልኩት፡፡ ገና ምቴ ሳያርፍበት ተዘጋጅቶ የመጣበትን ለቅሶውን ለቀቀው፡፡ አባወራውና ሚስቱ ሲያባብሉት እየተፈራገጠ የቢራ ጠርሙስ ሰበረ፡፡
“አሁን በጣም መበሳጨት ፈለግሁ” አልኩት ለጌትሽ፤በራሱ ቋንቋ፡፡ ምናልባት ከቢራ ወደ አልኮል ሊያሻግረኝ ይችል ይሆናል በሚል ግምት ፍላጎቴን መግለጼ ነበር፡፡
“ለመበሳጨት ምን ምክኒያት አለህ?” አለኝ፡፡ ለመጠጣት የሚሆን ገንዘብ ይዘሀል ወይ? ማለቱ ነው፡፡ አሁን ሙሉ ለሙሉ በእነሱ ቤት መዝገበ ቃላት በመጠቀም ላይ ነኝ፡፡ መዝገበ ቃላቱ ከስኳር መናር ጋር ለአጠቃቀም እየቀለለ እንደሚመጣ ገባኝ፡፡ የጌትሽ ቤት ቋንቋ የብስጭት ቋንቋ ነው፡፡ ከመጠጥ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይስማማል፡፡ “ምንም ምክኒያት የለኝም … ምክኒያት ማግኛዎቼ ቤተሰቦቼ ነበሩ ሞተዋል” “ለራስህ አጭር ልብወለድማ ምክኒያቱ ራስህ መሆን አለብህ … በእኔ ምክኒያት አንተ ልትበሳጭማ አትችልም፡፡ በሚስትህ ምክኒያት መበሳጨቱ አያዋጣህም!” አለኝ፡፡
ተዋረድኩኝ፡፡ በዛ ላይ እርቦኛል፡፡ ምሳ ይጋብዘኛል ብዬ ልጁና እናቱ የበሉትን ገንፎ አልተጋራሁም፤ከራሴ መኖሪያ ከመውጣቴ በፊት፡፡ አሁን ሞረሞረኝ፡፡ በግድግዳ ላይ ባለው መዝገበ ቃላት ላይ የራሴን አስተዋፅኦ ማድረግ አማረኝ፡፡
ለጠራችሁት እንግዳ = ምሳ አቅርቡለት
ማለት ፈለግሁኝ፡፡ ባልና ሚስቱ መሀል ልጄ ተወሽቆ በጥላቻ ያየኛል፡፡ የእነሱ ልጅ ነው የሚመስለው፡፡ ግን ምንም አልተናገርኩም፡፡
በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ = በአንድ ወር ሁለቱን ወላጆቹን እና መኖሪያ ቤቱን ያጣ ልጅ … እንበለው እያሉ ሲወያዩ ድንገት ንዴቴ ገነፈለ፡፡
በረሀቤ ምክንያት ይሁን በሌላ ብቻ የእውነተኛውን ብስጭት ተበሳጨሁ … እኔን ለመንካት ነው፡፡ ወላጆቼ በአንድ ወር ውስጥ ነው ተከታትለው የሞቱት … ተነስቼ በግድግዳ ላይ የሰቀሉትን የቃላት ዝርዝር ቦጫጨኩት፡፡ የልጄን እጅ አንጠልጥዬ ወጣሁ፡፡ ባልና ሚስቱ  ትክዝ ብለው ከማየት በስተቀር ምንም አላደረጉም፡፡ በእኔ ድርጊት አማካኝነት ለብስጭት አዲስ የመዝገበ ቃላት ትርጉም ያገኙለት ይመስል እርስ በራሳቸው ፈገግታ ተለዋወጡ፡፡  


Read 4604 times