Saturday, 25 June 2016 12:29

ቻይና የአለማችንን እጅግ ፈጣን ኮምፒውተር ሰራች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በሰከንድ 93 ትሪሊዮን ስሌቶችን መስራት ይችላል

    ቻይና በፍጥነቱ አቻ የማይገኝለትን የአለማችን እጅግ ፈጣን ሱፐር ኮምፒውተር መስራቷንና በአለም አገራት የበርካታ ፈጣን ኮምፒውተሮች ባለቤትነት ደረጃ ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ባለፈው ሰኞ በጀርመን በተካሄደው አለማቀፍ የሱፐር ኮምፒውተሮች ጉባኤ ላይ ይፋ የተደረገውና ታይሁላይት የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ እጅግ ፈጣን ቻይና ሰራሽ ኮምፒውተር፣ በሰከንድ 93 ትሪሊዮን ያህል ውስብስብ ስሌቶችን የመስራት አቅም እንዳለው ዘገባው ገልጧል፡፡
ናሽናል ሪሰርች ሴንተር ኦፍ ፓራለል ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ኤንድ ቴክኖሎጂ የተባለው የአገሪቱ የምርምር ተቋም የፈጠራ ውጤት የሆነው ኮምፒውተሩ፣ ሙሉ ለሙሉ የተሰራው በቻይና ቁሳቁሶችና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች ሲሆን በተለያዩ የምህንድስና፣የአየር ንብረትና በሌሎች የሳይንስና የመረጃ ጥናት የምርምር ፕሮጀክቶች ውስጥ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጧል፡፡  
    ባለፈው ሰኞ በተካሄደው አለማቀፍ የሱፐር ኮምፒውተሮች ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው፣ በየመንፈቅ አመቱ ይፋ በሚደረገው የበርካታ ሱፐር ኮምፒውተሮች ባለቤት አገራት ዝርዝር ውስጥ ቻይና ቀዳሚነቱን ከአሜሪካ ተረክባለች፡፡
 የ167 ሱፐር ኮምፒውተሮች ባለቤት የሆነቺው ቻይና፤ በአለማቀፍ የበርካታ ሱፐር ኮምፒውተሮች ባለቤትነት ደረጃ ቀዳሚውን ስፍራ ስትይዝ፣ አሜሪካ በ165 ሱፐር ኮምፒውተሮች ሁለተኛ ደረጃን፣ ጃፓን ደግሞ በ28 ሱፐር ኮምፒውተሮች ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸው ተነግሯል፡፡

Read 3611 times