Saturday, 25 June 2016 11:59

የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ተማሪው ሰኔ ሠላሳ ሰርተፊኬቱን ይዞ ቤት ይመጣል፡፡
“አባዬ እንኳን ደስ ያለህ…”
“እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡ ጎረምሳው ምን ተገኝቶ ነው… አንደኛ ወጣህ እንዴ!”
“አንደኛ አልወጣሁም…”
“ታዲያ ለምንድነው እንኳን ደስ ያለህ ያልከኝ?” ብሎ ሲጠይቀው፣ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ዘንድሮም አምስተኛ ክፍል ስለደገምኩ ለአዲስ መጽሐፍት ገንዘብ አታወጣም፡፡”
ለአባቱ ‘የሚያስብ’ ልጅ ማለት እንዲህ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…
የእኛ ሙሽራ ኩሪ፣ ኩሪ
ወሰደሽ አስተማሪ
ማለት ዘንድሮ ነው፡፡ ቲቸሮች ሊሽሩ ነዋ! ልጄ…ከእንግዲህ  ‘አስተማሪ ማግባት’…አለ አይደል… “እሷማ አልፎላት አስተማሪ አግብታ ለሰላምታም ለምኑኝ ልትል ምንም አልቀራት…” ምናምን የሚባልበት ዘመን እየመጣ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በፊት ጊዜ…
“ለመሆኑ ልጃችሁ መቼ ነው የምታገባው?”
“እንግዲህ ለዳግማይ ትንሳኤ ብለናል፡፡”
“እሰይ፣ እሰይ…ለመሆኑ ባሏ ሥራው ምንድነው?”
“አስተማሪ…”
ሲባል ጠያቂዎች ፈገግ ለማለት እየሞከሩ “ጐሽ፣ ጥሩ ነው…” ይባላል፡፡ በሆዳቸው ግን ምን ሊባል ይችላል መሰላችሁ…
“አፈር በበላሁ፣ ምን አይነት ጠማማ ዕድል ነው የገጠማት!” ልክ ነዋ፡፡ “ምስኪን አስተማሪ በምኑ ሊያኖራት ነው…” የሚባለው እኮ ዝም ብሎ አይደለም፡፡
እናላችሁ…አሁን ያ ሁሉ ሊለወጥ ነው፡፡
“ለመሆኑ ልጃችሁ መቼ ነው የምታገባው?”
“ገና አልተወሰነም፣ እጮኛዋ ምን እንደሚል እየጠበቅን ነው…”
“ለመሆኑ ጮኛዋ ሥራው ምንድው?”
“አስተማሪ…”
“አስተማሪ! በሉ ጊዜው አይታመንም፣ አንዷ ጭልፊት መጥታ ሳትወስድባት ቶሎ ብላችሁ ዳሯት፡፡”
እንግዲህ ወደ ተማሪዎች ምረቃ ሰሞን እየገባን አይደል…ይቺን ስሙኝማ፡፡ ወጣቱ ከኮሌጅ ይመረቅና ምክር ፍለጋ ወደ አጎቱ ይሄዳል፡፡
“አጎቴ፡ ይኸው እንግዲህ ከኮሌጅ ተመርቄያለሁ፡፡ ሥራ ለማግኘት ምን ማድረግ ነው ያለብኝ!” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ አጎት ምን ብሎ ቢመለስ ጥሩ ነው…
“አንዷን ሥራ ያላትን ፈልግና ቶሎ ብለህ አግባ፡፡” አሪፍ አይደል!  አሀ…ሚስት ብቻ ሳትሆን ‘ኢንሹራንስ’ም ትሆናለቻ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የተማሪ አስተማሪ ነገር ከተነሳ አይቀር ልክ ያልሆኑ፣ እየታዩ እንዳልታዩ እየሆኑ ‘ቀዩን መስመር’ ያለፉ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ የሚመለከተን ሁሉ እየተበላሹ ያሉት ነገሮች እንዴት ሳይታዩን ቀሩ! ነገሩ ከተለዋወጠ በኋላ…ወይም ‘ፈረንጆቹ’ን ለመኮረጅ ያሀል…ባቡሩ ጣቢያውን ከለቀቀ በኋላ ነገር ቢገባን ምን ዋጋ አለው!
ሰውየው ቤቱ ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን እያየ ሳለ በሩ ይንኳኳል፡፡ ተነስቶ ሲከፍተውም በሩ ስር አንዲት ቀንድ አውጣ ነበረች፡፡ ሰውየው ይናደድና ቀንድ አውጣዋን ብድግ አድርጎ ያሽቀነጥራታል፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ አሁንም ተቀምጦ ቴሌቪዥን እያየ ሳለ በር ይንኳኳል፡፡ ሰውየው ተነስቶ ሲከፍተው ያቺ ቀንድ አውጣ ብሽቅ ብላ ቆማለች፡፡ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ቅድም ለምንድነው የወረወርከኝ!” ሦስት ዓመት ቆይቶ ነገር የሚገባን መአት ነን…ያውም ከገባን ማለት ነው፡፡
አስተማሪ እኮ ባይፈራ እንኳን ይከበር የነበረበት ዘመን ሩቅ አይደለም፡፡
“የሂሳብ ቲቸራችን መጡ፣ እንዳያዩኝ…”
“የባዮሎጂ አስተማሪያችን ሰፈሩ እዚህ ነው፣ በዚህ ሰዓት ኳስ ስጫወት ካየኝ…” ምናምን አይነት ‘ስጋቶች’ ቀርተዋል፡፡ አሀ…ስንሰለጥንስ! ደግሞ እኛ አገር በምንም ነገር ‘ስልጣኔ’ ሲገባ ደረጃ፣ በደረጃ ምናምን ብሎ ነገር ሳይሆን ‘እስከ ጥግ’ ነው፡፡ እናማ…ሁሉም ነገር ድብልቅልቁ  ሲወጣ ‘አቅመ ቢሱ’ ተማሪው ይሁን አስተማሪው ግራ ያጋባል፡፡
የአቅም ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ባልየው በሆነ ነገር ተናዶ ሚስቱን ይመታታል፣ ሚስትም በተራዋ ወንድ ልጇን ትመታዋለች፡፡ ወንድ ልጅ ሆዬ ታናሽ እህቱን ይመታል፣ ታናሽ እህትየውም የምታሸንፈውን ፈልጋ በተራዋ ምስኪኗን ድመት ትመታታለች፡፡ አቅም የሌላት ድመት ምን ብታደርግ ጥሩ ነው…ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ነጠላ ጫማዎች ላይ ተጸዳዳችባቸዋ! እናማ…ከድመቲቱ የሚገኘው ‘ትምህርት’ አቅም የላቸውም ብሎ ማጥቃት አሪፍ አለመሆኑን  ነው፡፡ ቂ…ቂ...ቂ… ማለት… ለሰው ልጅም ሊሠራ የማይችልበት ምክንያት የለም ለማለት ያህል ነው፡፡
የምር እኮ…አስተማሪና ተማሪ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፎ የሚሄድበት፣ በድራፍት ዙሪያ ተሰባስቦ የሚቀመጥበት፣ አንዳንድ አስተማሪዎች በተማሪ ‘ገርልፍሬንዶች’ እርጥባን ወር ይዳረሳሉ የሚባልባት  አገር ሆናለች እየተባለ ነው! ልጄ…ግልጥ በግልጥ መነጋገር ነዋ! ምናልባት የዘንድሮ አስተማሪዎች ብዙዎቹ በጣም ወጣቶች መሆናቸው… አለ አይደል… ለአስተማሪና ተማሪ ትከሻ ለትከሻ ‘ለመገጫጨት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ (አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች… “ተማሪው ጩጬ፣ አስተማሪው ጩጬ” እንድሚሉት ማለት ነው፡፡) አስተማሪን መፍራቱ ቀሺም ሊሆን ይችላል…ግን የሚገባቸውን ክብር ማግኘት ያለባቸው አይመስላችሁም!
ተማሪው ማሙሽን አባቱ… “ማሙሽ፣ ትምህርት ቤት ደስ የሚልህ መቼ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ማሙሽ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ሲዘጋ፡፡” አሪፍ አይደል!
ለነገሩ ችግር ያለባቸው መአት ‘ቲቸሮች’ አሉ ነው የሚባለው፡፡ አለ አይደል… ‘ትምሮው’ ላልተመቻቸው ሴት ተማሪዎች ማለፊያ ማርክ ለመስጠት ‘እነሆ በረከት’ን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያቀርቡ፣ ሲልም “ጥሩ ውጤት ማግኘት ከፈለግህ ፈረንካውን በጥስ…” ምናምን የሚሉ…አስተማሪዎች አሉ ይባላል፡፡ (ዕድሜ ለ…. የሚሉ እንትናዬ ተማሪዎችም አሉ ይባላል፡፡)
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ድሮ ‘አለቅን በሰባራ ሽጉጥ’ ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በ‘ይባላል’ ልናልቅ ነው፡፡
ወሬ በዛ! ‘ይባላል’ በዛ! የምር “እንዲህ ተባለ…” “እንደዛ ተባለ…” አይነት ነገር በዛና ብስሉን ከጥሬ መለየት አቃተን፡፡
መሄዴ ነው መልቀቄ ነው ከአገር
እንቅቡም ሰፌዱም ነካካኝ በነገር
የሚያሰኙ “…ተባለ እኮ…” ነገሮች እየበዙ የጠራ መረጃ ማግኘቱ አስቸግሯል፡፡ አይደለም እኛ ምስኪን ዜጎች መሀል… ሚዲያ ላይ የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉ እንደ ተናጋሪዎቹ ፍላጎት ገደድ፣ ወልገድ እያሉ ማን ለማተቡ፣ ማን ለባንክ ደብተሩ እንደሚሠራ ግራ እየገባን ነው፡፡
ማነው ያለው ካልኩኝ ብዙ እሰማለሁ፣
ማነው ያለው ብልስ ማንን አምናለሁ፣
ማነው ያለው አውቀዋለሁ ባይ ብዙ፣
በሞላበት ያደክማል ጓዝ መዘዙ፣
የምትለው የአብነት ግጥም አሪፍ ነች፡፡ አውቀዋለሁ ባይ በዝቶ ነው አገር አልደማማጥ ያለው፡፡
እስቲ ወጣ ብለን የአስተማሪ ወዳጅ እንፈልግማ!
የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!




Read 8384 times