Saturday, 25 June 2016 11:53

ኢጣሊያውያን የአድዋ ጦርነት ሽንፈታቸው ተቀበሉ ማለት ይቻላል?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት አያሌ የቅኝ ግዛት ወረራዎች ሙከራ ቢደረግባትም አያት ቅድመ አያቶቻችን ባደረጉት ተጋድሎ፣ታፍራ የተከበረች ኢትዮጵያን ተረክበናል፡፡ ከእነዚያ አኩሪ ድሎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ለአፍሪካውያን ጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ በአርአያነት የሚጠቀሰው የአድዋ ጦርነት ነው፡፡ ጣልያኖች እጅግ ዘመናዊና የሰለጠነ ጦር እየመሩ ቢመጡም በዳግማዊ ሚኒሊክ የሚመራውና ከአልደፈርም ባይነት ወኔ በቀር ዘመናዊ ሊባል የሚችል ጦር መሳሪያ ያላነገበው የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ጣልያኖችን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ ጦርነቱን በድል አጠናቋል፡፡
እንደምናውቀው ከቅኝ ግዛት ማክተም በኋላ ምዕራባውያን ሀገራት ከአፍሪካውያን ጋር ልዩ ልዩ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በመፍጠር ለሀገራቸው ገጽታ ግንባታ ጠቃሚ ነው ብለው የሚያምኑትን ተግባራት ያከናውናሉ፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና ወታደራዊ ትብብሮች ይሳተፋሉ፡፡
ዛሬ የትምህርት ትብብር ላይ እናተኩርና ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅኝ ግዛት ማክተም በኋላ ብዛት ያላቸው ኢንተርናሽናል ኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች ተከፍተዋል፡፡
የአሜሪካን አይ ሲ ኤስ፣ የእንግሊዙ ሳንድ ፎርድ፣ የፈረንሳዩ ሊሴ ገ.ማርያም፣ የጀርመኑ ጎቴ ኢንስቲትዩት እንዲሁም የጣልያን ት/ቤት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ት/ቤቶች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ባላቸው ስምምነት፣ በሀገራቸው የትምህርት ስርአት መሰረት ትምህርት የሚሰጡ ቢሆንም በሀገሪቱ ካሌንደር  የሚከበሩ ሀገራዊም ሆነ ሀይማኖታዊ በአላትን የማክበር ግዴታ ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ መሬቱ የኢትዮጵያ ነውና፡፡ አለም አቀፍ ተቋማትና የውጭ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ሀገራዊ በዓላት ማክበር ይጠበቅባቸዋል! በዚህ መሰረት አብላጫዎቹ ኤምባሲዎችና ት/ቤቶቻቸው በዓላትን ያከብራሉ! ት/ቤቶቻቸውን ይዘጋሉ፡፡ ያም ሆኖ፤ የኢጣልያን ኮሙኒቲ ት/ቤት፣ የአድዋ ድል በዓል በሚከበርበት የካቲት 23 አንድም ቀን ዘግቶ እንደማያውቅ፣ እንዲሁም ከሌላው ቀን በተለየ በዚያ እለት ከት/ቤት የቀረ ተማሪን የተለየ ቅጣት እንደሚቀጣ አንድ ልጁን እዚያ የሚያስተምር ወዳጄ ቢነግረኝ፣ጉዳዩ ከንክኖኝ ነው ይህን ትዝብት ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡
ኧረ ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ይሄንን ያውቁ ይሆን? እነዚህ ሰዎች እኮ ያንን ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሆነውን ታላቅ ድል በዘመናት ሂደት ከኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ አደብዝዞ ለማጥፋት ተግተው እየሰሩ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በቅርቡ 75ኛ ዓመት የድል በዓል አራት ኪሎ አደባባይ ላይ በተከበረበት ወቅት የኢጣልያ አምባሳደር ተገኝተው ይህንኑ ሀሳብ ሲያጠናክሩ በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ ጎበዝ … የጀግንነታችን አሻራ ያረፈበት አኩሪ የድል ቀናችንን ጣልያኖቹ ሲክዱትና ሲያናንቁት መመልከት ለማንም ኢትዮጵያዊ የማይዋጥና የሚያንገበግብ በመሆኑ፣የሚመለከተው የመንግስት አካል ጉዳዩን በቸልታ ሊያየው አይገባም እላለሁ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል ነው ነገሩ፡፡
-ከሙሉጌታ ጅኒ

Read 1893 times