Saturday, 25 June 2016 11:51

የፌስቡክ የጥላቻ መልዕክቶች ላይ የተደረገ ጥናት ምን ይላል?

Written by 
Rate this item
(18 votes)

ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፌ ስቡክ የሰመረላቸው የመንግስት ባ ለስልጣናትና ተ ቋማት ጥ ቂት ናቸው ብሏል

   ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ላይ ባደረገው የናሙና ጥናት፣ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክ በኩል የሚያስተላልፏቸው የጥላቻ መልዕክቶችና አስተያየቶች መጠን፣ ከተጠቃሚዎች ብዛት አንጻር እጅግ አነስተኛ ሆኖ እንዳገኘው አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያውያንን የፌስቡክ አጠቃቀም በተመለከተ ለሁለት አመት ያህል ያከናወነውና ሰሞኑን ይፋ ያደረገው “መቻቻል” የተሰኘ ርዕስ ያለው ይህ ጥናት፤ በናሙናነት ከተወሰዱት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አስተያየቶች መካከል ብሄርን፣ ዜግነትን፣ ሃይማኖትን ወይም ጾታን መሰረት በማድረግ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን የሚያገልሉ የጥላቻ መልዕክት ያዘሉት 0.7 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ገልጿል፡፡
በ2007 ዓ.ም ከየካቲት እስከ ሃምሌ በነበሩት ወራት ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከሰጧቸው አስተያየቶችና መልዕክቶች ውስጥ 13 ሺህ ያህሉን በናሙናነት ወስዶ የተነተነው ጥናቱ፣ አደገኛ ወይም ጠብ አጫሪ ተብለው ከተመደቡት የፌስቡክ አስተያየቶችና መልዕክቶች መካከል 21.8 በመቶ የሚሆኑት የፖለቲካ ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ እንደሆኑና ሃይማኖትና ብሄር 10 በመቶ እና 14 በመቶ ያህል ድርሻ እንዳላቸውም ገልጧል፡፡
በጥናቱ የጥላቻ አስተያየቶችንና መልዕክቶችን አስተላልፈዋል ከተባሉት ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መካከል 92 በመቶ ያህሉ፣ ትክክለኛ ማንነታቸውን ደብቀው በሃሰተኛ የፌስቡክ ስም የሚጠቀሙ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የመንግስት ተቋማት ፌስቡክን እንደ አንድ የመረጃ ማሰራጫ መንገድ ለመጠቀም ሙከራ እያደረጉ ነው ያለው ጥናቱ፤ ይሄም ሆኖ ግን ተጽዕኖ መፍጠርና ተሰሚነት ማግኘት የቻሉት በጣም አነስተኛ ናቸው ብሏል፡፡
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያከናወነው ይህ ጥናት፤ ከ2007 የካቲት እስከ ሃምሌ ባሉት ወራት፣ በ1ሺህ 55 የፌስቡክ ገጾች ላይ የተሰጡ ከ13 ሺህ በላይ አስተያየቶችና መልዕክቶችን በናሙናነት ወስዶ መተንተኑ ተገልጧል፡፡

Read 8063 times