Saturday, 25 June 2016 11:49

የአዲስ አበባ ኑሮ ከአለማችን ከተሞች ጋር ሲነፃፀር!

Written by 
Rate this item
(18 votes)

     ከብራዚልና ከሜክሲኮ ዋና ከተሞች፣ ከካልታና ከኢዝላማባድ … ከሃጋሪና ከፖላንድ እንዲሁም ከዩክሬንና ከማሌዥያ ዋና ከተሞች ይልቅ፣ የአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት ይከፋል፡፡ ከካናዳ ኦታዋ እና ጊታሞና ሞንትሪያል፤ ከጀርመን ሊፕዚግ እና ኑርንበርግ ከተሞች ጋር ሊነፃፀርም፣ የኑሮ ውድነት በአዲስ አበባ ይከብዳል፡፡ ሜርሰር የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው አመታዊው የዓለማችን ከተሞች የኑሮ ውድነት ደረጃ፣ መዲናችን አዲስ አበባ 143ኛ ደረጃን መያዟን አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ለ22ኛ ጊዜ በ209 የዓለማችን አገራት ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ላይ ተመስርቶ ይፋ ያደረገው የዘንድሮ ሪፖርት እንደሚለው፣ በአለማችን ከሚገኙ ከተሞች ለመኖር ከፍተኛ ወጪን በመጠየቅ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘቺው ሆንግ ኮንግ ስትሆን የአንጎላ መዲና ሉዋንዳና የስዊዘርላንዷ ዙሪክ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ዝቅተኛ ወጪን የሚጠይቁ የዓለማችን ከተሞች ተብለው የተዘረዘሩት ደግሞ የናሚቢያዋ ዊንድሆክ፣ የደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውንና የካይሬጊስታኗ ቢሽኬክ ሲሆኑ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ ከተሞች የአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ያለባት ከተማ ናት ያለው ሪፖርቱ፤ የኮንጎዋ ኪንሻሳና የቻድ ርዕሰ ከተማ ጃሜና ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን አብራርቷል፡፡
ተቋሙ የከተሞችን የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የአልባሳትና የመሳሰሉትን ከ200 በላይ የሚሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋ እና ሌሎች ተያያዥ የፋይናንስ ሁኔታዎችን በመገምገም የየከተሞችን የኑሮ ውድነት ደረጃ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡

Read 8810 times