Saturday, 25 June 2016 11:47

ኤርትራውያን በመንግሥታቸው ጉዳይ ለሁለት ተከፍለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(59 votes)

“የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለፍርድ የመቅረብ እድል በ UN እጅ ላይ ነው”

    የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተከሰቱ ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት እንደማይቀበሉት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቁ፡፡ ከማንም የማይወግን ነፃ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ የጠፋው ህይወትና የደረሱት ጉዳቶቹ በድጋሚ እንዲጣሩም ጠይቀዋል፡፡
መድረክ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት ከ330 በላይ ዜጎች ስለመሞታቸው መረጃ እንዳለው ጠቁሞ የኮሚሽኑ ሪፖርት የሟቾችን ቁጥር በግማሽ ያሳነሰ ነው ብሏል፡፡  በኦሮሚያ ክልል የ292 ሟቾች ስምና ሙሉ መረጃ እንዳለው የገለፀው መድረክ፤ 41 ያህል ማንነታቸው ያልተለዩትን ጨምሮ የሟቾቹ ቁጥር ከ330 በላይ ነው ብሏል፡፡ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና የፀጥታ ኃይሉም ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀሙን የሚገልፅ ሪፖርት ማውጣታቸውን የጠቀሱት ሰማያዊና መድረክ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሟቾች ቁጥር 173 ብቻ ናቸው ማለቱ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ “በተቃውሞ ወቅት በመንግስት የተወሰደው እርምጃ “አስፈላጊና ተመጣጣኝ ነው” ማለቱም የፀጥታ ኃይሉንና መንግስትን ከተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ የተወጠነ ነው” ብለዋል፤ ፓርቲዎቹ ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ፡፡
 ከኦሮሚያ በተጨማሪ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን እንዲሁም በደቡብ ክልል በኮንሶ ወረዳ፣ ዜጎች መብቶቻቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ የኃይል እርምጃ ተወስዶባቸዋል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በዚህ ሂደት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡
በየአካባቢው ተቃውሞና ግጭቱን ተከትሎ የደረሱ ጉዳቶችን ገለልተኛ አካል እንዲያጣራ በተደጋጋሚ መንግስትን ሲጠይቁ እንደነበር የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ “መንግስት ጥያቄያችንን ቸል ብሎ ራሱ መርጦ ባቋቋመው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲጣራ ማድረጉ የተቃዋሚዎችን ጥያቄና ማሳሰቢያ ወደ ጎን መግፋቱን ያመለክታል” ብለዋል፡፡ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ያልተጣራ በመሆኑም ኮሚሽኑ ያቀረበው ሪፖርት ተአማኒነትና ተቀባይነት የሌለው ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞና ጉዳዩ በድጋሚ ተጣርቶ፣ ጉዳቱ እንዲገለፅ አሳስበዋል፡፡ ተቃውሞና ግጭቶቹን ተከትሎ የታሰሩ የፓርቲ አባላት፣ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እንዲፈቱ የጠየቁት ፓርቲዎቹ፤ በማረሚያ ቤት ይደርሳሉ የሚባሉ የመብት ጥሰቶችም በአስቸኳይ እንዲቆሙ አሳስበዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅርቡ በአዲስ አበባ “ህገወጥ ግንባታ ናቸው” በሚል እየፈረሱ ያሉ ቤቶች፤ የዜጎችን መጠለያ የማግኘት መብት የሚቃረንና የሰው ህይወትም እየቀጠፈ በመሆኑ ድርጊቱን እንቃወማለን ብለዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ በርካቶችን ቤት አልባ አድርጎ፣ ለተጎሳቆለ ኑሮ እየዳረገ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ መንግሥት ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጠይቀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መንግስት ተገቢውን ካሳ በመክፈል እንዲያቋቁማቸው የጠየቁት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ፤ የልማት ተነሺዎችም በአግባቡ መብታቸው ተጠብቆ መስተናገድ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

Read 9817 times