Saturday, 25 June 2016 11:45

የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አዲስ ፓርቲ መሰረቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

     የቀድሞ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች፤ “ነፃነት ለአንድነትና ለፍትህ (ነፃነት) የተሰኘ አዲስ ፓርቲ መሰረቱ፡፡
 የአዲሱ ፓርቲ መስራች ጠቅላላ ጉባኤ ከረጅም የምስረታ ሂደት በኋላ ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም በሆቴል ዲ.አፍሪክ የተካሄደ ሲሆን በእለቱም የፓርቲው የተለያዩ መተዳደሪያ ሰነዶች በጉባኤው ከፀደቁ በኋላ የቀድሞ የአንድነት አመራር አባል ዶ/ር ንጋት አስፋው ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን በፓርቲው የመስራች አስተባባሪ ኮሚቴው ፀሐፊ፣ አቶ ደምሴ መንግስቱ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ፓርቲውን በማቋቋም ሂደቱ ከሰሞኑ ህይወታቸው ያለፈው አቶ ብሩ ብርመጅ እና አቶ ተመስገን ዘውዴ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን በእነ አቶ ብሩ የሚመራው ቡድን በሌላ በኩል ሌላ ፓርቲ እየመሰረተ ከነበረው የእነ አቶ ሽመልስ ሃብቴ ቡድን ጋር በመቀላቀል “ነፃነት” የተሰኘው ፓርቲ እንደተመሰረተ አቶ ደምሴ አብራርተዋል፡፡
አዲሱ ፓርቲ የደቡብ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ ውክልና ያላቸው አባላት እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፓርቲው ምስረታ የተሳተፉት ሁሉም አባላት በአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደምሴ፤ 2ሺህ ያህል ሰዎች ለአዲሱ ፓርቲ የድጋፍ ፊርማ ሰጥተዋል ብለዋል፡፡
ፓርቲው ከቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ህገ ደንብ በተለየ መልኩ ፕሬዚዳንት የሚመርጠው በጠቅላላ ጉባኤ ሳይሆን በብሄራዊ ምክር ቤት መሆኑም ታውቋል፡፡ ፓርቲው አመራሮቹን ስለመረጠ አሁን ከምርጫ ቦርድ የምዝገባ ሰርተፊኬት ለማግኘት ለቦርዱ የሚገቡ ሰነዶች እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡

Read 4281 times