Saturday, 25 June 2016 11:44

የኢትዮጵያ መንግስት የሶማሊላንድ ጋዜጠኞችን ማሰሩ ተዘገበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭት እንዲቋረጥ አድርጓል ተብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሰኞ ዋጃሌ በተባለቺው የኢትዮ-ሶማሊላንድ የድንበር ከተማ አምስት የሶማሊላንድ ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር አውሎ ማሰሩንና አራቱ ከቆይታ በኋላ ሲለቀቁ አንደኛው አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ዳስላን ሬዲዮ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞቹን ከማሰር ባለፈ፣ ሆርን ኬብል የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ ያስተላለፈው ዘገባ ተገቢ አይደለም በሚል ታይኮም ለተባለው የሳተላይት ተቋም ባቀረበው ቅሬታ፤ጣቢያው በአካባቢው ያሰራጭ የነበረው ፕሮግራም እንዲቋረጥ ማድረጉንም ሶማሊላንድ ኢንፎርመር ዘግቧል፡፡
ጋዜጠኞቹ በዋጃሌ ከተማ በተዘጋጀ ሃሰተኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙ በኋላ በመንግስት ልዩ ሃይል ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ወደ ጂግጂጋ ከተማ ተወስደው እንደታሰሩ የጠቆመው ዘገባው፣ አራቱ ሲፈቱ ሆርን ኬብል ቲቪ የተባለው የሶማሊላንድ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ባልደረባ፣ጋዜጠኛ ሙክታር ኑር ግን አሁንም በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን ያሰረበት ምክንያት ግልጽ አይደለም ያለው ዘገባው፤ሶማሊላንድና ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ረገድ ተባብረው ሲሰሩ እንደነበርና ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ የታሰሩ የአገሪቱ ጋዜጠኞች በሃርጌሳ በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁሞ ሌሎች ጋዜጠኞችም በኢትዮጵያ በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውሷል፡፡የሶማሊላንድ ጋዜጠኞች ማህበር፣ ናሽናል ዩኒየን ፎር ሶማሊ ጆርናሊስትስ እና ሶማሊ ኢንዲፔንደንት ሚዲያ ሃውስስ አሶሴሽን የተባሉት የጋዜጠኞች ማህበራት፣ድርጊቱን የፕሬስ ነጻነት ጥሰት ነው በማለት ያወገዙት ሲሆን በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ሙክታር ኑር፣ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቅ ጠይቀዋል፡፡

Read 3404 times