Saturday, 25 June 2016 11:42

“ለክረምቱ ግብርና በቂ ዝግጅት አልተደረገም” አለማቀፍ ተቋማት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ከ7 ወር በኋላ ከድርቅና ተረጂነት ዜጎች ይላቀቃሉ” መንግስት

   የበልግና የክረምቱ ዝናብ በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ በድርቅ የተጎዱ ዜጎች በመጪው ጥር 2009 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ከተረጂነት ይላቀቃሉ የተባለ ሲሆን በግብርና ላይ የሚሰሩ አለማቀፍ ተቋማት በበኩላቸው፤ መንግስት ለግብርናው በቂ ዝግጅት አላደረጉም ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ የክረምቱ ዝናብ በሚፈለገው መጠን እየዘነበ መሆኑን የጠቀሰው በአፍሪካ ግብርና ላይ ትኩረቱን ያደረገው የአርካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት የተሰኘው ተቋም፤ መንግስት እርዳታ በማቅረብ ላይ ብቻ በመጠመዱ የዘር አቅርቦቱን ቸል ብሎታል ብሏል፡፡ የዘር አቅርቦቱ እጥረት እያጋጠመው ነው ያለው ተቋሙ፤ ይህም የድርቁን ችግር ሊያራዝመው ይችላል ብሏል፡፡
የብሄራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኮሚሽነር በበኩሉ፤ ከ7 ወር በኋላ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ከድርቅ ተረጂነት ትላቀቃለች ተብሎ እንደሚጠበቅና የድርቁን ወቅታዊ ችግርና የተረጅዎችን ሁኔታ የሚያጠና ቡድን ወደየአካባቢዎቹ መላኩን ጠቁመዋል፡፡
“እስካሁን የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ከ10.2 ሚሊዮን አልዘለለም” ያሉት ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ፤ የበልጉ ዝናብ ምን ያህል ተረጅዎችን ከተረጅነት አላቀቀ የሚለውን ቡድኑ ካጠና በኋላ የተረጂዎች ቁጥር አሁን ካለበት ሊቀንስ ይችላል ብለዋል፡፡ የበልግና የክረምቱን ዝናብ በአግባቡ ተጠቅሞ የሚሰራው ስራ ቀጣዩን ሁኔታ ይወስነዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ወደ 15 ሚሊዮን ያሻቅባል ተብሎ የተሰጋው ግን እስካሁን አልደረሰም ብለዋል፡፡
የመንግስት ሙሉ ትኩረት የእርዳታ ስራው ላይ መሆኑ የተገኘውን ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ክፍተት እየፈጠረ ነው ያለው የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት በበኩሉ፤ ዝናቡ ትርጉም የሚኖረው አርሶ አደሮች በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ ነው፤ ይህ ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ እየተስተዋለ አይደለም ብሏል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የክረምቱን ዝናብ ለመጠቀም “በዘር ሳይሸፈን የሚቀር መሬት መኖር የለበትም” በሚል አቋም፤ የዘር አቅርቦቱን ባለው አቅም ሁሉ እያቀረበ መሆኑን እምብዛም እጥረት ሊያጋጥም አይችልም ብሏል፡፡

Read 975 times