Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 March 2012 14:57

አላምርባቸው ያሉ ነገሮች…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!

እንዲሁ ነው እንግዲህ…የላይፍ ነገር!

እኔ የምለው…ዘንድሮ አላምርባቸው ያሉ ነገሮች አልበዙባችሁም! ለምሳሌ ከቤት ውጪ የመመገብ ነገር አላምርበት ብሏል፡፡ እኔ የምለው…ፊፍቲ ምናምን ብር ከፍላችሁ ያዘዛችሁት ሥጋ ወጥ ውስጥ …”ሥጋውን” ለማግኘት ለአፋልጉኝ ማስታወቂያ ተጨማሪ ወጪ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፡፡

ሹሮ ያኔ “የድሃ ቀለብ” በነበረችበት ዘመን “ቢጠፋ፣ ቢጠፋ ሹሮዬን በልቼ እውላለሁ” እየተባለ ይፎከር ነበር፡፡ ዘንድሮ ሹሮዋም ከክትፎ እኩል ሆና ከቺስታዎች ጋር የምትቆራኘው ብቸኛዋ “ዲሽ”…አለ አይደል…”በሶ” ብቻ ልትሆን ነው፡፡

ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በየክትፎ ቤቱ “ለዚህ ክትፎ የሚሆን ሥጋ ላበረከታችሁ ኮርማዎች ሞታችሁም ለሚደርስባችሁ እንግልት ይቅር በሉን” ምናምን የሚል መፈክር ነገር ይለጠፍልንማ፡፡ ልክ ነዋ! የአንዳንዶቻችንን የአበላል “ፓሽን” ስታዩ በሬዎቹ ለምግብነት የታረዱ ሳይሆን የሆነ መስዋእትነት የከፈሉ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡

በቅቤ “ያበደው” ሹሮ ጣዕም የለው፤ ምን የለው… እንደውም ወደፊት ምን የሚል ማስታወቂያ የሚለጠፍ ይመስለኛል መሰላችሁ…”ቅቤ በነካው ማማሰያ የተማሰለ ሹሮ ወጥ ማቅረብ መጀመራችንን በደስታ እንገልጻለን፡፡” ልክ እኮ የሆነ ጨርቅ “ውል ተች” እንደሚባለው ወጡም “ቅቤ ተች” እየሆነብን ነው፡፡ እናማ የብዙ ሬስቱራንቶቻችን ነገር አላምርበት እያለ ነው፡፡

በዛ ሰሞን የሆነ ቀጠሮ ሰዓቴ እስኪደርስ ራሴን “ሀፒ” ነገር ላድርግ ብዬ እዚህ የቀለጠው ቦሌ መድኃኔዓለም መንደር የሆነ ካፌ በረንዳ ቁጭ አልኩ፡፡ ግማሽ ሻይ ጠጣሁላችሁና ቀዩዋን ሰጠሁ፤ ሀሳቤ እንግዲህ ያው ሦስት ወይም ሦስት ከምናምን መልስ ማምጣቱ አይቀርም…ያችኑ ፒፕ ሰጥቼው የዕቁብ ማሙያ ትሆንለታለች ነገር ነበር፡፡ አሳላፊው ሲመጣ ምን አለኝ መሰላችሁ… “ጋሼ ሂሳቡ አሥራ አንድ ብር ነው” ምንም የጣዕም…የምንም ነገር ለውጥ ለሌለው ግማሽ ብርጭቆ ሻይ አሥራ አንድ ብር፡፡ ሃሳብ አለን… ከመካከለኛ ክብደት ወደ ላባ ክብደት ዝቅ ላለችው ብራችን “ሜሞሪያል ዴይ” ነገር ይዘጋጅልንማ!

(እግረ መንገዴን…ስሙኝማ ቦሌም አቧራ ሆነ አይደል!...አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዢ ይሄኔ ነው፡፡ “ማን ፈርሶ ማን ይቀራል” አይነት ምቁነት ያስመስልብኝ ይሆን እንዴ? ትንሽ ቅር ያለኝ ምን መሰላችሁ…በቃ የቦዲ ሎሽንና የፋውንዴሽን ዋጋ ሰማይ ሊነካ ነው፡፡ ቻይኖቹ “የዛኛውን ጉዳይ” ዋጋ እንዳናሩብን…ቦሌዎች አምበሬ ጭቃ ሰፈር እንዳይደርሱ እግራቸውን…ይቅርታ መኪኖቻቸውን…ያዝልንማ! ከምንቀባት አምበሬ ጭቃ ቀንሰን አንድኛውን ላይምስቶኗን ሆነን ቁጭ ልንል አይደል! እኔ የምለው…ኪሏችንም፣ ብራችንም፣ ፍቅራችንም፣ “ሬታችንም” ሲቀንስ…ፀጉርና ጥፍር ብቻ የሚያድግበት እንዴት “ቢተበተብብን” ነው!)

እናላችሁ…የምር “ግፍ” የሚባለው ነገር እዚህ ላይ ነው የሚሠራው፡፡ አሥራ አንድ ብር እኮ በጊዜው…አለ አይደል…የእሁድ “ፓኬጅ ዴት” ወጪ አሳምሮ ይሸፍን ነበር፡፡ ኧረ እንደውም በር ተንኳኩቶ “ሰዓት አልቋል” ሲባል “እጨምራለሁ” የሚያስብል ባይተርፍ ነው! አንድ ሳይሆን ሁለትም አዲስ ሰው ለዓለም ማበርከት ለሚያስችል “ካምፔይን” ይበቃ የነበረ አሥራ አንድ ብር ለግማሽ ብርጭቆ ሻይ! አሀ…አሁንስ እኛም እጃችንን አብረን ወደ ላይ እንዘረጋለን፡፡

እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የብር ነገር ከተነሳ…የተለጣጠፈ ብር ድሮ ባንክ ገብቶ እዛው አልነበር እንዴ የሚቀረው! ዘንድሮ ግን…ከእነ “ባንዴጁ” ወደ እኛው መመለሱ በዛ፡፡ ድሮም የወደቀ ግንድ ላይ ነው ምሳር የሚበዛበት! ግሽበት ምናምን የሚሉት አልበቃ ብሎ ብራችን የጣጤ ጉንጭና አገጭ መስሎ ይቅር! ጥያቄ አለን…”መተካካት” በብር አይሠራም እንዴ ቂ…ቂ…ቂ… (እነ እንትና…ይሄንንም “እንጀራ አብስሉበት” አሉ) ሃሳብ አለን..የተለጣጠፈ ብር ወደእኛ ሲመለስልን የመጀመሪያ እርዳታ ሳጥንም አብሮ ይሰጠን፡፡ ፌጦና ጡንጅት “ብር ማከም” ላይ አይሠራማ!

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የዘንድሮን በሬ ልብ ብላችሁ አይታችሁልኛል!...የምር እኮ “በሬ እንኳን እንዲህ ይጨምት!” ያሰኛል፡፡ ልክ ነዋ…የድሮ በሬ እኮ በስንት ዱላ፣ በስንት ገመድ ጉተታ አገር ምድሩን እየቀወጠው አልነበር የሚሄደው! ዘንድሮ ግን ልጄ…አለ አይደል…”ሂድ!” እየተባለ በአለንጋ መገረፍ የለ፣ “ና!” እየተባለ በገመድ መጐተት የለ…ምን አለፋችሁ…በራስ ተነሳሽነት ሲንጐማለል ወደ ቄራ ምናምን ሳይሆን ለሆነ ወርክሾፕ ምናምን የሚሄድ ነው የሚመስለው፡፡ (በነገራችን ላይ…የበሬ ክፋት ሲቀንስ የእኛ ለመብዛቱ ኦሾ የሚለው ነገር የለውም!)

በሬን ካነሳን አይቀር…የበግ ነገርም እኮ የ”ክላስ መለያ” አይነት ሊሆንብን ነው፡፡ ልክ ነዋ…እንደ አዝማሚያው ከሆነ እኮ የሙክት ምናምን ነገር ከሆነ… ጥያቄው “በግ ብንገዛ ይሻላል ወይስ ዶሮ!” ሳይሆን “በግ ብንገዛ ይሻላል ወይስ ያማህ ሞተር ቢስኪሌት!” እናላችሁ…እንግዲህ ከሲታ በጐችም እየበዙ አይደል…የበግ ግዢና የሙዚቃ አልበም ግዢ መስፈርቶች እየተመሳሰሉ ነው፡፡

አልበሙን “ግጥምና ዜማ እንኳን ባዶ ነው፣ ግን ድምጽ ምንም አይል” ብለን እንደምንገዛው በጉንም “ሥጋ እንኳን ባዶ ነው፣ ግን ሲጮህ ግቢ ያደምቃል!” አይነት እየሆነ ነው፡፡ እኔ የምለው…በጎቹ እንዲህ የሚቀጭጩት … የእነሱም “ኪድኒ” ምናምን ይመነተፍ ጀመር እንዴ! እናላችሁ ነገርዬው ሁሉ አላምርበት እያለ ተቸግረናል፡፡

የእኛ ቺስታዎች ኮንፊደንስ እንዳይሟጠጥ ደገፍ ያደርገን የነበረው የየሆቴሉ “ሀፒ ሀወር” እንኳን አላምርበት እያለ ነው፡፡ “ሀፒ ሀወር” እኮ ኪስ ሆዬ እንደ አንዳንዶቻችን “ብሬይን” … አለ አይደል … የሚከራይ ቤት አይነት ነገር ሲሆን ከሰው ጋር እንቀላቀልበት ነበር፡፡ አሁንማ ልጄ … የሚቀማመሰው “ውሀ” ነገር የ”ሀፒ ሀወር” ዋጋ እየተሰቀለ ስቀን ገብተን ተሳቀን መውጣት ሆኗል፡፡ ሀሳብ አለንማ … ሌላ ወደ “እኛ” የሚጠጋ “ሀፒ ሀወር” ይፈጠርልንማ! ባይሆን ሰው እንዳያየን ወደ “ጓዳ ገብተን” እንጠጣለን … የዓይናችን ቀለም ደስ የማይላቸው በዝተዋላ! (ስሙኝማ … ዘንድሮ ብዙ ነገር … አለ አይደል … “ወደ ጓዳ ግቡ! የምን በአደባባይ መቀላቀል ነው!” እየተባልን አይመስላችሁም! ይሄ “ነጻ ገበያ” ምናምን … እንደ ብሉ ሌብል ውስኪ ሌላ “ብሉ ብለድ” አይነት ነገር ተፈጠረ እንዴ!)

በነገራችን ላይ … ለቁጣም “ሀፒ ሀወር” ይዘጋጅልንማ“! ልክ ነዋ … ቁጣ በጣም፤ በጣም ነው የበዛብን፡፡ እና ከቁጣ ነጻ የሆነ “ሀፒ ሀወር” በየምሽቱ በእራት ሰዓት ይመደብልንማ! እራታችን “መፈጨት የሚችል” አይነት ምግብ ከሆነ እየተሳቀቅን ጨጓራችን ሥራ እንዳያቆምብን ከቁጣ የ”ታይም አውት” ጊዜ ይሰጠንማ“!

እንደ አገር ልጅነት መታየት አላምር እያለ ነው፡፡ ልክ ነዋ … እኛ “ድንገት ጉንፋን ቢይዘኝ” ብለን አጣጥፈን የያዝናት መሀረብ “የነብር አየኝ በይ” አይነት ፍተሻ ሲካሄድባት … “ፈረንጅ” ግን ሙሉ ኪችኑን በቦርሳ ተሸክሞ ሰላምታ ተሰጥቶት የሚያልፍበት አገር ሆኗል! በዚህ ላይ ወደ እኛ “ሌቭል” ቀረብ ያሉ እንግዶች እየበዙ “እንትንም ገበያ ሆኖ እየተቀረጠላት” አይነት ነው፡፡

የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ … ዘንድሮ እዚች አገር የማይመጣ የሰው ዘር አለ እንዴ!፡፡ ልክ ነዋ … ቻይና ይመስከራ! ቂ…ቂ…ቂ የምር ግን አሁን አሁን ቻይኖች ምን ይመስሉኛል መሰላችሁ … የሆኑ “ቤተ ኢትዮጵያውያን!”  ነገሮች … ሁሉንም ነገር ተሻሙና!  ልጄ … ተወደደብን ብለን ስንቆጭበት የነበረውና የ”ጄንደር ባላንሱ” ወደ አንድ ወገን ስላጋደለ “ቀንሶ ወደ ድሮው ቦታ ይመለስልናል” ያልነው “ነገር” ሁሉ ጨመረብና! (እንትናዬ … “በደረቁ ሌሊት ታስለፈልፋለች” የተባለው “በነገር ስትጠብስ ታድራለች” ማለት አይደለም፡፡ “ንገር” የተባልኩትን ነው …)

እናላችሁ … በፊት “ስሚ … ያ አሜሪካዊ ውሽሜሽ እንዴት ነው?” ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን “ያ ቻይና ውሽሜሽ እንዴት ነው?” መባል ባይጀመር ምን አለ በሉኝ፡፡ ግሎባላይዜሽን በቴክኖሎጂ ምናምን እንደመምጣት በዚህ ይምጣብን! ኮሚክ እኮ ነው … ቁንዲፍቱ እንኳን ለኪስ እየከበደች ትምጣ! ምን አለ በሉኝ … “ትንሽ ቆይቶ የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በቻይና አናግሪያቸው” ባይባል! ወይንም ደግም “ልጃችን የቻይና ዜግነት ማግኘቷን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀነው ግብዣ ላይ …” እየተባለ በድግስ ብዛት የዕድር ድንኳኖች ኪራይ ባይጦፍ!

የበዓል ነገርም አላምርበት እያለ ነው፡፡ … በዛ ሰሞን የተረት አባትን የማናውቅ ሁሉ የገና አባት እያልን መከራችንን ስናይ ሰነበትን! “ቫለንታይን ዴይ” ጨሶ ተከበረ! “ታንክስ ጊቪንግ” ዴይ በየኤፍ.ኤም. ጣቢያው “ሰበር ዜና” አይነት ሆኖ ተሰነበተ .. ለከርሞ ደግሞ “ጁላይ ፎር” በሙሉ ቀን ቀጥታ ስርጭት ይከበርልናል፡፡ (እኔ የምለው … እንዲሁ ትዝ ብሎኝ ነው፣ የቻይና ዘመን መለወጫ እንደ እነ “ቫለንታይን ዴይ” ጨሶ የማይከበርልን የእነ ሪሀናን ዘፈን ለመምረጥ አያመችም ተብሎ ነው! አሀ … ልጅን ሲወዱ ከእነእንትቱ ነዋ! ቂ…ቂ…ቂ… “መቃብርሽ ላይ ላልቆም” ምናምን ተባብለን እስከምንቆራረጥ ምን አለበት አንዳንድ በዓሎቻቸውን “ብንኮርጅ!” አሀ … አንዲት ሳትቀር ኮርጀናቸዋል ማለት እኮ የሚያስጨበጭብበት ዘመን ነው!)

እናላችሁ … ያላማረባቸው ነገሮች እየበረከቱ ተቸግረናል፡፡ “ዘ ጉድ ኦልድ ዴይስ” ምናምን የሚባል ነገር ነበር አይደል! … ታዲያላችሁ በፊት እንደዛ ስትሉ የቅጽል አይነት ነገር ይደረድርባችሁ በር፡፡ ዘንድሮ ግን አይደለም ሀያ፣ ሠላሳ ዓመት … የዛሬ አራትና አምስት ዓመታት “ዘ ጉድ ኦልድ ዴይስ” እየሆኑብን … አላምርባቸው ያሉ ነገሮች እየበዙብን ነው!

የብዙዎቻችን ወዘናም አላምርበት እያለ ነው፡፡ (“ተግጦ ያለቀ ፍርምባ መስለሀል” ያልከኝ ወዳጄ … ጥያቄ አለኝ … ፍርምባ ምንድነው? አሀ … እኛ የሙሉ ከብቱን ስም መጥራት እየራቀን ሄዷል … አጅሬ ወደ ዝርዝር ጉዳይ መግባትህ ልክ ስላልሆነ … አለ አይደል … “አካሄድ” አስተካክል፡፡) እኔ የምለው … ወንዶች ፋውንዴሽን ምናምን መቀባት ጀመሩ እንዴ? ልክ ነዋ … በብዙ ወንዶች ገጽታ ላይ የምናየው የ”ከለር መዛነፍ” በሰዓሊዎች ላይ የመጣ እንቅፋት ነገር ይመስላል፡፡ አሀ … እኛ የለየልን “የአብስትራክቶች” መንገዱን ሞልተነው “አብስትራክት” ስዕል እንደልባቸው አይስሉማ! (እግረ መንገዴን … ያልገባን ነገር አለ፡፡ “ቦተሊካው ሲሳካ” “ቦተሊከኞች ጉንጭ” የሚያወጡበትን ሳይንስ የሚያብራራ መጽሔት ከገጠማችሁ ጠቁሙኝማ!)

እናማ … ነገሮች ሁሉ አላምርባቸው እያለ ተቸግረናል፡፡ አንዳንድ ሚስቶች እንኳን አላምርባቸው ብሏል አሉ … አንድ ወዳጄ ያለኝን ነዋ! ምን አለኝ መሰላችሁ … “ሚስቶች እንኳን ሸሚዝ ኮሌታ ላይ የከንፈር አሻራ መፈለግ ትተዋል፡፡ “እናላችሁ … ወይ ነጭ ሊፕስቲክ ተጀምራል፣ ወይም የሆነ የ”ጋራ መግባባት” ላይ ተደርሷል፡፡

(“ሥልጣን ወይም ገንዘብ ኖሮኝ ይሄን የሰው እንትናዬ መንጠቅ የሚሉትን ነገር ኤክስፒሪየንስ ባደረግሁት) ያልከኝ ወዳጄ … አንተ ሙከራህን ቀጥል፣ እኔ ደግሞ ዶሮ ማርባት እጀምራለሁ፡፡ (አሀ … ዶሮ ጠባቂ ትሆናታለህ!”)  እናላችሁ …. አላምርባቸው ያሉ ነገሮች ቁጥር የሚቀንስ ተአምር ይላክልንማ!

 

 

Read 2803 times Last modified on Monday, 05 March 2012 15:31