Print this page
Saturday, 25 June 2016 11:30

የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ!

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ፈረንጆች Good News and Bad News የሚሉት አላቸው፡፡ ደግ ወሬና ክፉ ወሬ
እንደማለት ነው፡፡ ይኸንን የተንተራሰ የአንድ ሀኪምና የታካሚው ንግግር የዛሬ ተረታችን ነው፡፡
እነሆ፡-
ሐኪም - እንኳን ደህና መጣህ ወዳጄ፡፡
ታካሚ - እንኳን ደህና ቆዩኝ ሐኪም፡፡
ሐኪም - ዛሬ፤ደግም ክፉም ወሬ ይዤ ነው የጠበቅሁህ፡፡
ታካሚ - ግዴለም ሐኪም፤ከክፉው ወሬ ይጀምሩልኝ፡፡
ሐኪም - መልካም፡፡ ግን ቅር እንዳይልህ፡፡
ታካሚ - በጭራሽ ቅር አልሰኝም፡፡
ሐኪም - እንግዲያው ልንገርህ፡፡ እህትህ በጠና ታማ፣ኮማ ገብታ፣እያጣጣረች ናት፡፡
ታካሚ - ይሁን እግዜር ካመጣው ምን ይደረጋል? ሌላስ?
ሐኪም - ወንድምህ ውሃ ውስጥ ሰጥሞ፣አሁን አምቡላንስ ተልኮለት እየመጣ ነው፡፡
ታካሚ - እግዚሀር ፈርዶበት ነው እንጂ ዋና ይችላልኮ! ሌላስ የሚነግሩኝ አለ?
ሐኪም - አዎ፡፡
ታካሚ - ቶሎ ቶሎ ይንገሩኝ ሐኪም!
ሐኪም - ባለቤትህ ልፈታው ነው ብላ ነግራኛለች፡፡
ታካሚ - ይሁን እንግዲህ ካመጣው ምን ይደረጋል! ሌላ አለ የሚነግሩኝ?
ሐኪም - ዛሬ በህይወት ሆነህ አንተን ማግኘቴ ገርሞኛል፡፡ ምክንያቱም ማታ ቤትህ መቃጠሉን
ሰምቻለሁ፡፡
ታካሚ - አዎ፤ ውጪ ነው ያደርኩት፡፡ ሌላስ  ምን የሚጨምሩልኝ ክፉ ወሬ አለ?
ሐኪም - ክፉውን ወሬ ጨርሻለሁ፤የቀረኝ ደጉ ወሬ ነው፡፡
ታካሚ - (በጣም ተጣድፎ) ሐኪም፤እሱን በደምብ ይንገሩኝ!
ሐኪም - አልዛይመር የሚባል በሽታ ይዞሃል፡፡
ታካሚ - ምን ማለት ነው?
ሐኪም - የማይድን በሽታ ነው፡፡ ማስታወስ የአለመቻል በሽታ ነው!
ታካሚ - ሐኪም፤በጣም ጨካኝ ነዎት፡፡ ይሄንን ነው ደግ ወሬ ብለው የሚነግሩኝ?
ሐኪም - ለምን መሰለህ እንድታውቅ ያደረኩህ?
ታካሚ - ለምንድነው ሐኪም?
ሐኪም - ምክንያቱም አሁን ከእኔ ስትለይ ያልኩህን ሁሉ ትረሳዋለህ፡፡ ለዚህ ነው ደግ ወሬ ነው
ያልኩህ!
***
የመከራና ችግሮቻችን መብዛት መርሳትን (አልዛይመርን) እንዳንመኝ ቢያደርገን መልካም ነበር፡፡
የበሽታችንን ስር ካላወቅን ሌላ በሽታ በራችንን ማንኳኳቱ አይቀሬ ነው፡፡ በሩ ሲንኳኳ ካላደመጥን
ደሞ ሌላ በሽታ አከልንበት ማለት ነው፡፡ “ሌባ!----ሌባ!” እያልን እንጮሃለን! በአደባባይ “እናሳየዋለን” እንላለን፤አንይዘውም፡፡ የጠራራ ፀሃይ ስርቆሽ፣ “የአየር ጊዜ መግዛትና” ፖሊሱ ዞር ብሎ እንዲቆይ ማድረግ፣ ፀሃይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ሌባውም አይያዝም፤ ፖሊሱም አይጠየቅም - መርካቶ ጉያዋ ብዙ ቢሆንም አደባባይዋ ግን ይህን ያሳየናል፡፡ የሞባይል ሌብነት፣አንድ ሌባ እንዳለው፤“የሥራ ፈጠራ እኮ ነው!” እንደ አራዶች አባባል፤ “ልማታዊ ሌብነት” መሆኑ ነው፡፡ የሴት ቦርሳ ምንተፋ ተጧጡፏል! የማን ያለህ እንበል? “በኃይለስላሴ አምላክ!” ይባል የነበረው ቀረ እንጂ ትንሽ ፋታ ይሰጥ ነበር፡፡ በ”ሕግ አምላክ”፣ ዛሬ እንኳን ወጣቱ የመንግሥት ሠራተኛም አያውቀው!
“ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የተሻለ መርህ ቃል (motto) ነው:: ቀን በቀን ከባንክ ጋር ተመሳጥሮ ከሚመዘበረው ገንዘብ አንስቶ በመሬት መልክ አገር እስከ መሸጥ ያለውን “የገበያ ውጣ-ውረድ”፣ በዓለም አቀፉ የገበያ ሥርዓት ወይስ በግሎባላይዜሽን እቅፍ ውስጥ እንደመድበው?
የታላላቅ ባለስልጣናት ወገናዊነት፣ እስከ ሰባት ቤት የኢ-ፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል፣ የህዝብ ሀብት
ምዝበራ እንጂ የልማት ቀፎ ውስጥ የሚቀፈቀፍ የማር እንጀራ ሊባል ነው እንዴ?
ማ ባለስልጣን የማ ንግድ ድርጅት “ሼር ሆልደር” እንደሆነ ሳናውቅ ነው እንዴ ስለ ሙስና የምናወራው? የጦር አበጋዝ የንግድ ተቋራጭ የሚሆንበት አገር፣እዚሁ አኛ ዘንድ ካልሆነ የሮማ ነገስታትን ታሪክ አናመጣ?ስንቱን እንርሳ? በስንቱ “አልዛይመር” ይያዘን? ወይስ በተቋም ደረጃ የሚያም “አልዛይመር” ይኑረን?
ነገረ ስራችን ሁሉ ጥሩ ታቅዶ ነበር፡፡ ጥሩ ሥራ አመራር ተመድቦ ነበር - ታዲያ ምን ያደርጋል?
“የአፈፃፀም ችግር አለ” ይባላል፡፡ እስከ መቼ? “የአፃፀም ችግርን የሚያይ አገር አቀፍ ኮሚሽን”
ይቋቋም እንዴ? የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኮሌጅነት እስከ ዩኒቨርሲቲነት በሸፍጥ እስከመሰየም
ድረስ ከፍተኛ ሙስና ውስጥ ሲዘፈቅ ስናይ፣ እንዲህ በይፋ ምንም ሳያሟላ የተመረቀ ተማሪ ማስረጃ
አቅርብ ሲባል፤ እስከ መፋጠጥ ሲደርስ፣ ያስተማረው ዩኒቨርሲቲ እንዴት እንደተቀበለው ግራ  እስከመጋባት ሲደርስ ስናስተውል፤ “እዚህ አገር ስንቱን እንርሳ?” “በስንቱ አልዛይመር ይያዘን?”
ያሰኛል፡፡
በእውነት አገራችን እድገት ካላት፣የእድገቷ ታማሚ ናት ወይም ምርኮኛ ናት!
የቤቶች አስተዳደር ጣጣ ችግር ዛሬም ችግር ነው፡፡ ገቢዎችና ተገልጋዩ ነጋዴ ህብረተሰብ ዛሬም እንዳልተማመኑ፣ዛሬም እንዳልተዋደዱ ናቸው፡፡ የአደጉ አገሮችን የገቢዎች አስተዳደር ሥርዓት እንመኛለን፡፡ ግን በምን አንጀት? በማን ትከሻ? በምን እምነት?
የሰብዓዊ መብት ችግርና የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ይተሳሰር ዘንድ መከራችንን ስናይ ሰንብተናል፡፡ ግጭትን ባልተመጣጠነ ኃይል መፍታት የመልካም አስተዳደር የሁሉ-የሁሌ-ፍቱን  መድሐኒት (Panacea) አድርገን መውሰዱ በውል መጤን አለበት፡፡ ፍርድ ቤቶች ከሹማዊና ወገናዊ ሥርዓት መፅዳት አለባቸው፡፡ ስህተታችንን ስንሰማ አለመደናገር ቁልፍ ነገር ነው፡፡ በርትቶ ማረም ነው መድሐኒቱ! ችግሮቻችን አያሌ ናቸው፡፡ አልዛይመርም ቢይዘን አንረሳቸውም፡፡ ከሁሉም የሚልቀው “ችግር የለብንም፡፡ ይሄን ያህል ፐርሰንት አድገናል! የዓለም ባንክ ይሄን ይሄን ብሎናል፡፡” የሚለው ነገር ነው፡፡ “ይሄን አውጀናል፤ይሄን በጀት በጅተናል፤በሚቀጥሉት ይሄን ያህል አመታት ጉድ እናያለን” የሚለው ምኞትና ተስፋም፣ ዜጐች ብዙ ፍሬ እንድንጠብቅ ልባችንን ያንጠለጥለናል፡፡ “መሬት የያዘው የቱ ነው?” ማለታችን ግን አይቀርም፡፡ “የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ” የምንለው ያኔ ነው!

Read 8506 times
Administrator

Latest from Administrator