Saturday, 03 March 2012 14:55

አባይ እስኪደርስ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

GIZ የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ማሣየትና በዚሁ ክልል በ3 ቀበሌዎች ላይ ያስገነባቸውን በውሃ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎችን ለማስመረቅ በተያዘው ፕሮግራም ላይ እንዲገኙ ጥሪ ከተደረገላቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ሆኜ ነበር ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ላይ በድርጅቱ ዋና መ/ቤት ቅጥር ግቢ የተገኘሁት፡፡

ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ዘጠኝ ጋዜጠኞችን ያካተተው የጉዞ ቡድን የመጀመሪያ ጉብኝቱን የጀመረው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልና የኦሮሚያ ክልልን በሚያዋስናቸው በወንዶገነት ወረዳ ሶሎ 01 ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርግለትና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት የብሔረሰቦች ምክር ቤት፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ፀጥታ ቢሮዎች አጋርነት በደቡብ ክልል ሬድዮ ጣቢያ የሚተላለፈውን “ለሠላማችን እንደማመጥ” የተባለ ሣምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም በህብረተሰቡ ውስጥ ያመጣውን ለውጥና ህብረተሰቡ ስለፕሮግራሙ ያለውን አስተያየት መመልከት የመጀመሪያ ሥራችን ሆነና ወደሥፍራው አመራን፡፡

ቦታው የሁለቱ ክልሎች መዋሰኛ እንደመሆኑ መጠን በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ተከስተው የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ ሁኔታው በዚህ መልኩ መቀጠል ስለማይገባው ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ህብረተሰቡን ማስተማርና የሠላም ባህልን ማስረፅ ዋነኛው አጀንዳው አድርጐ የዛሬ ሁለት ዓመት በሁለት ወረዳዎች የተጀመረው ፕሮግራም፤ ዛሬ በ10 ወረዳዎች 14 የሚደርሱ የአድማጮች ክበባትን በማቋቋም ፕሮግራሙ በስፋት እንዲደመጥ አድርጓል፡፡

“ለሠላማችን እንደማመጥ” የሚል ነጫጭ ቲ-ሸርት የለበሱ የኮሚኒቲው አባላትና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በአንድ ዛፍ ጥላ ሥራ ተሰባስበው ፕሮግራሙን ያደምጣሉ፡፡ ጥቃቅን ግጭቶች ለከፋ የእርስ በርስ ጦርነትና መተላለቅ ምክንያትና መነሻ ሊሆኑ ስለሚችሉ ግጭቶችን ማስወገድና ከተከሰቱም በሰላማዊ መንገድ መፍታት ስለሚቻልበት ሁኔታ በስፋት ይወያያሉ፡፡ በሥፍራው ያገኘኋቸው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ጋሬ ጋንቼ፤ ሥፍራው በተለያዩ ወቅቶች በተነሱ ግጭቶች ሠላም እርቆት የቆየ መሆኑን ገልፀውልኛል፡፡ የግጭቶቹ መነሻ ምክንያቶችም የግጦሽ መሬት፣ የውሃ፣ ደንና ሌሎች ሃብቶች ባለቤትነት ዋንኞቹ ሲሆኑ በራስ ቋንቋ የመጠቀምና የመማር መብቶችም ለግጭቶቹ መነሻ ሆነው መቆየታቸውን ነግረውኛል፡፡ ከሁለቱ ብሔረሰብ አባላት በአንደኛው ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎችና የሌላኛው ብሔረሰብ አባል በአፀፋው በሚወስደው የበቀል እርምጃ የተነሳ አካባቢው ሠላም ርቆት ቆይቷል፡፡ ይህንን  ለመቀየርና የሁለቱም ብሔር አባላት ጥላቻቸውን አስወግደው በሠላምና መተሳሰብ እንዲኖሩ ለማድረግ በአካባቢው በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንና ከእነዚህ መካከልም በGIZ የሚደገፈው የሠላም ሬዲዮ ፕሮግራም ከፍተኛውን ሚና መጫወቱን የኮሚኒቲው አባላት ይናገራሉ፡፡ የሁለቱም ብሔር አባላት በአንድ ሥፍራ ተሰባስበው ስለሠላም የሚነገረውን እየሰሙ መወያየት መቻላቸው እውነትም ትልቅ ለውጥ ነው፡፡

ከGIZ ፕሮጀክት አንዱ የሆነውን ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ለመመልከት አዋሣ ዩኒቨርሲቲ ሄደንም ነበር፡፡ አራት በአንድ እየተጣመሩ የተሰሩት 54 የእንጀራ መጋገሪያ ምጣዶች ያሉበት ክፍል ስንደርስ ሠራተኞቹ በሙሉ በሥራ ላይ ናቸው፡፡ አቡኪው፣ ሊጥ አቅጣኙ፣ ማገዶ አቅራቢው፣ ጋጋሪዋ… ሁሉም በሥራ ላይ፡፡ በ2001 ዓ.ም የተቋቋመውና 100 አባላት ያሉት የምግብ ማቀነባበሪያ ማህበር፤ በቀን 24ሺህ እንጀራ እየጋገረ ለዩኒቨርሲቲው ያቀርባል፡፡ በሦስት ፈረቃዎች የተከፋፈሉት 81 ጋጋሪዎች እያንዳንዳቸው 400 እንጀራዎችን በየቀኑ ይጋግራሉ፡፡ ለዚህ ሥራቸው የሚከፈላቸው ወርሃዊ ደመወዛቸውም ብር 450 ነው፡፡ በ GIZ የተሠራው የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ማገዶውን ብቻ ሣይሆን የእነሱንም ድካም እንደቆጠበላቸውና ሥራቸውን እንዳቃለለላቸው ነግረውናል፡፡

ድርጅቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ያሰራቸውን በውሃ ኃይል የሚሰሩ ሦስት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ተቋማት በክልሉ ርዕሰ ብሔር የሚያስመርቅ በመሆኑ ቀጣይ ጉዞአችንን ወደ ሲዳማ ዞን፣ አለታ ወንዶ ወረዳ፣ አገረ ሶዲቻና ኪላ ሒቂቻ ቀበሌዎች ሆነ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ኤረርቴ፣ ጐቢቾ 2 እና አገረ ሶዲቻ የተባሉ 3 በውሃ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ተሰርተዋል፡፡ የጣቢያዎቹ ኃይል የማመንጨት አቅም ከ125 ኪሎዋት በላይ ሲሆን 22ሺህ ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ብርሃን የመስጠት አቅም አላቸው፡፡

የውሃ ግድቦቹ የተሰሩባቸውና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ የተገነቡባቸው ቦታዎች እጅግ ገደላማና አስቸጋሪ በሆኑ ሥፍራዎች ላይ ነው፡፡ በአካባቢው አግኝቼ ያነጋገርኳቸው ነዋሪዎች ለህክምና፣ ለጤና አገልግሎት፣ እህል ለማስፈጨትና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ከአራት ሰዓታት በላይ በእግራቸው መጓዝና በአለታ ወንዶ መሔድ ይጠበቅባቸው እንደነበር ገልፀው አሁን ችግሩ ስለተቃለለላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመብራት አገልግሎቱን ለማግኘት የማቴሪያል ግዥን ጨምሮ ወደ አንድ ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ መክፈል የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ይህንን ማድረግ ለእኛ ከባድ ነው ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎችን በኃላፊነት ለማስተዳደር ተቋማቱን ከ GIZ የሚረከበው የክልሉ መንግስታዊ አካል በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የነዋሪዎቹን አቅም በአገናዘበ መልኩ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ሊያመቻች ይገባዋል፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የሚነገርለት የአባይ ግድብ (ሕዳሴ ግድቡ) እስኪደርስ ድረስ እንዲህ ዓይነት አነስተኛ ግድቦች መገንባቱ የነዋሪውን ችግር ለመቅረፍ የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም፡፡

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው በክልሉ የሥራ ቋንቋ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ ፕሮጀክቶቹ ለአካባቢው ህብረተሰብ ስለሚኖራቸው ጠቀሜታ የተናገሩትን ቋንቋውን መረዳት ላልቻልነው ጋዜጠኞች በአማርኛ አጠር አድርገው እንዲነግሩን ብንጠይቃቸውም ፈቃደኛ ሣይሆኑልን ቀርተዋል፡፡ ይልቁንም በዚሁ አካባቢ በጐበኘነው አንድ ት/ቤት ቤተመፃህፍት ውስጥ በአማርኛ ተፅፎ ያገኙትን አንድ መፅሐፍ እንዴት እዚህ ቤተመፃህፍት ውስጥ ተገኘ በሚል ቁጣቸውን ሲያሰሙ ታዝበናቸዋል፡፡

ሠላምና ብርሃን ለመስጠት ወደ ደቡብ የተጓዘው የGIZ ፕሮጀክት፣ ዕቅዱ ተሣክቶለት ሁለቱንም ጉዳዮች ለየፈላጊዎቻቸው ማድረስ ችሏል፡፡ በሠርቶ ማሣያነት የተጀመረውን የዚህ ፕሮጀክት ሥራ ወደ ሌሎች ክልሎች የማስፋፋቱንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረጉን ተግባር ጠንክሮ እንደሚቀጥልበትም በGIZ የኢነርጂ ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሣምሶን ቶሎሣ ነግረውናል፡፡ የምረቃው ሥነ ስርዓት ተጠናቆ አስቸጋሪውን ገደላማ መንገድ ስንጀምር የአካባቢው ህብረተሰብ ሥጋት በሕሊናዬ መመላለሱን ቀጠለ፡፡ “ሁላችንም የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆን እንድንችል የሚደረግበት መንገድ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ፕሮጀክቱ የጥቂቶቹ መጠቀሚያ ሆኖ መቅረት የለበትም” የሚለው ጉዳይ ሥጋታቸው ነው፡፡

 

 

Read 2008 times Last modified on Saturday, 03 March 2012 14:59