Saturday, 18 June 2016 13:17

የብዕር አሟሟት

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(12 votes)

ከምሽቱ 2፡00 ሰአት ….. እንግሊዝ ኤምባሲ ፊት ለፊት …… ወደ ባልደራስ በሚያወርደው ቅያስ ጠርዝ። ቴዲ ዘለቀ ግሮሰሪ፡፡ ብራንዲ ይዤ ተሰየምኩ - ከአቶ አለሙ አጠገብ፡፡ ……. ከሰላምታ በቀር ከኔ ጋር መነጋገር አልፈለጉም፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ያደርጋቸዋል፡፡ ዝግት። ጥርቅም፡፡ ደብል ብራንዲ ደገምኩ፡፡ ሠለሥኩ፡፡… አቶ አለሙ ድንገት ወደኔ ዘወር ብለው …. <<… ሙሴ እስራኤላውያንን ከምድረ ግብፅ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ቢመራቸውም መሰሪዎቹ አይሁዶች የጎን ውጋት ሆነውበት ነበር … ባልከኝ እስማማለሁ ግን…>>
ጉድ እኮ ነው ሰዎች! ሥለ ሙሴ … እስራኤል … ግብፅ … ትንፍሽ ያልኩት ነገር የለም፡፡ … የኔን ምላሽ ሳይጠብቁ ወደ ቁዘማቸው ገቡ፡፡ … መፅሀፍ አዟሪ ወደ ግሮሰሪዋ ገባ፡፡ … ከነመፅሀፍ ድርድሩ ፊቴ ተገተረ፡፡ የመፅሀፉቱ አርዕስቶች አፈጠጡብኝ - እየተቁለጨለጩ፡፡ የሌሲሳ ግርማን “ የንፋስ ህልም ’’ በ20 ብር ገዛሁ፡፡ የሲንግል ብራንዲ ዋጋ፡፡ ብራንዲዬን ፉት እያልኩ ማንበብ ጀመርኩ፡፡
አካፔላ……
….እና እንዳልኩህ የስሜት ዜማን በተመለከተ ብቸኛ ነህ፡፡ የምታዜመውም ያለሙዚቃ መሳሪያ ያለድምጽ ለራስህ ነው ፡፡ እወቀው ቁርጥህን፡፡ እውነቱ ይኼ ነው፡፡………..
አምሽተሀል ፡፡ ቀማምሰሀል፡፡ እየጠጣህ ያለህበት ቤት፤ ጠርሙሱ እየጨመቀ ሲያቀርብልህ የነበረው ሰው አንዴም ቀና ብሎ አላየህም፡፡ የምትታይ ዓይነት አይደለህም፡፡ …..
መቼ መታየት እንዳቆምክ በግልጽ አታስታውስም። ስለማትታይ ስለማትዳሰስ ለሌላው የሚሰሩ ሕጎች ለአንተ አይሰሩም፡፡ የሌላው ሰው ሙዚቃ አይመለከትህም፡፡ የሌላው ሰው እይታ አይታይህም። ታዲያ የሌላውን ሰው መጠጥ ለምንድን ነው የምትጠጣው……..
………….መጠጡ ቢያሰክርህም እይታህን እንደ መሀረብ በአንድ እጥፋት ገልብጦታል፡፡ የሚታየው ማሰብን ለሚያዩት ትተሃል፡፡ ከእንዴት፤ ወዴት፤ መቼት….. ባሻገር ርቀሀል፡፡
………….ጥሩ ስሜትህን እንደያዝክ ወደማይታየው ቤትህ መሄድ ትፈልጋለህ፡፡ ሂሳቡን ትከፍላለህ፡፡…….
…………. መንገዱ፤ቤትህ ሊያደርስህ ሳይችል ሲቀር ትበሳጭበታለህ፡፡ ወደፊት ስትሄድ መንገዱ አብሮ ወደፊት እየሄደ፤መጀመሪያ ከተነሳህበት ቦታ ከካቻምና፤ አምና፤ ዘንድሮ፤ ሲሰልስህ እንደምንጣፍ ከስርህ ተስቦ ፈትለክ እያለ በአፍጢምህ ሊደፋህ ሲሞክር ታክሲ ለመያዝ ትወስናለህ፡፡……..
……….እቤትህ ደጃፍ ስትደርስ በሩ የውጨው ወደ ውስጥ ተገልብጦ ስለጠበቀህ፤ከደጅ እየገባሁ ወይስ ወደ ደጅ እየወጣሁ ነው ብለህ እስክትወስን ታክሲው አውርዶህ ሄዷል፡፡………..
……….እና እንዳልኩህ ይኸው ነው!.... (ገጽ 167)
መጽሐፉን አጥፌ……. “ለኔው ለግሌ ሁሌም መቼም በማመሽበት በግሮሰሪ አድራሻዬ የተላከ ደብዳቤ ይመስላል…..’’ ስል ለራሴው ቀበጣጠርኩ:: ደግነቱ ማንም አላዳመጠኝም፡፡ መደመጥ ካቆምኩኝ ሰነባበትኩ …….፡፡ ቀሪዋን ብራንዲ ጨለጥኩ፡፡ ሒሳብ ዘጋሁ፡፡
ከግሮሰሪ ወጣሁ፡፡…. ማካፋት ጀመረ፡፡ዝናቡ የሚያቆም ይመስላል፣የማያቆምም፡፡ እርምጃዬን አፈጠንኩ፡፡ መንገዱ ጨቅይቷል፡፡ ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ እየጣለ ነው፡፡
የሌሊሣ የንፋስ ህልም ይሁን ንፋስ የቀላቀለው ዝናብ….ከብራንዲው ሞቅታ ጋር ተደምሮ የመፃፍ ፍላጎቴ ተነሣሣ፡፡…… ሲጋራ ለኮስኩ፡፡ ቤት እንደገባሁ ሥለምጽፈው ድርሰት ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡…….
መነሻዬ…..በቅርቡ ዝውውር በሚል የተመደብኩበት ሲኦል መሠል መ/ቤት ደምሥና ይልማ የቢሮ ተጋሪዎች ናቸው፡፡ ይልማ ወጣ ባለበት “…..ይልማ ለምንድነው ሥራ የማይሰራው” ሥል አቶ ደምስን ጠየኳቸው፡፡
”የይልማን ስራ እኔ እየሸፈንኩለት ነው……”
አዛውንቱ ደምስ፤ የወጣቱን ይልማ ሥራ ደርበው የሚሰሩበት ምክንያት እንቆቅልሽ ሆኖብኝ…….”ግን ለምን?”
”ልናገረው የማልፈልገውን ምስጢር እንድነግርህ እየገፋፋኸኝ ነው….” ለአፍታ ፀጥ ካሉ በኋላ ”ይልማ ጨርቁን ያልጣለ ወፈፌ ነው፤ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል….”
በይልማ ድንገት ዘው ብሎ መግባት ጨዋታችን ተቋረጠ፡፡……
………አቶ ደምስ ሥራ ያልገቡበት ዕለት ነበር። ተላላኪው ዳጎስ ያለ ፋይል ይልማ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ወጣ፡፡ ይልማ ፋይሉን ንክችም አላደረገውም፡፡ ’ብሰራለትስ’ በሚል ቅንነት ፋይሉን ላነሳው ስል …….
”አይመለከትህም ” ሲል ቱግ አለብኝ፡፡
”የመስራት ፍላጎቱ የለህም፤ ታዲያ ማን ሊሰራልህ ነው”
”ጋሼ ደምስ”
”አቶ ደምስ ያንተን ሥራ የሚሰሩበት ምክንያት ምንድን ነው?” ስል ጠየኩት፡፡ የይልማን ወፈፌነት ከራሱ ከምንጩ ለመስማት፡፡
”ምክንያቱማ አቶ ደምስን መርዳት ስላለብኝ”
”አልገባኝም ”
”አምና የባለቤታቸው ሁለት ወንድሞች የመኪና አደጋ ህልፈት ተከትሎ በሀዘን ብዛት ባለቤታቸው አረፉ፡፡ በእናቷ ሞት ሴት ልጃቸው ተከተለቻቸው….. በዚህ ድርብርብ ሀዘን አቶ ደምስ ለአዕምሮ መዛባት……”
”የአንተን ስራ የሚሰሩበት ምክንያት አሁንም አልገባኝም”
”ጋሼ ደምሥ የተሰጣቸውን ሥራ በፍጥነት ፉት! አድርገው ያለ ስራ ሲጨናነቁ ማየቱ ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ እናም የኔን ስራ ወደ ጠረጴዛቸው ገፋ ማድረግ ጀመርኩ፡፡ በስራ ጫና ከገቡበት የአዕምሮ ውጥረት ፋታ ማግኘታቸው ለኔ ከምንም በላይ የህሊና እርካታ ሠጥቶኛል፡፡”
ማነው ዕብዱ ደምስ ወይንስ ይልማ….?
ለወሬ ሙት ነኝና ነገር ማነፍነፍኩ ጀመርኩ፡፡…..
የመዝገብ ቤት ሃላፊው አቶ ገብሬ ቢሮ አቀናሁ። የአቶ ደምስ ጎረቤት ናቸው፡፡ በወሬ በወሬ ስለ አቶ ደምስ ዘመድ አዝማዶች እልቂት አነሣሁባቸው፡፡…. አቶ ገብሬም ”አዎ ያልከው ሁሉ ደርሶባቸዋል፤ ሲያመጣው አንዴም አይደል”
“መቼም ዕልቂት ነው…..ይህ ሁሉ ውርጅብኝ የአቶ ደምስን አዕምሮ ሳያቃውሰው ይቀራል…..”
”መቼም ማዘኑ አይቀርም….የአዕምሮ መቃወስ ያልከው ግን ሲያልፍም አይነካው! የሚስቱ ወንድሞች ለቤት ውርስ አላስቆም አላቀምጥ ብለውት ነበር፤ ሙት ወቃሽ አታድርገኝና ለደምስ ግልግል በለው!”
”ሚስትና ልጃቸውስ?”
”ሚስት ተብዬዋም ብትሆን ከወንድሞቿ ጋር በማበር መላወሻ አሳጥታው ነበር፡፡ ልጅቷም ከሌላ የወለደቻቸው ዲቃላ እንጂ የደምስ ልጅ አልነበረችም።”
የዕብደት ሚዛኑ ወደ ይልማ ያደላ ይመስላል፡፡ አቶ ደምስ ፍፁም ጤነኛ…….
ጧት ቢሮ ከመግባቴ ሥራ አስኪያጁ አስጠሩኝ፡፡
“አቶ ደምስ ለወራት ፍቃድ ወጥተው የህክምና ክትትል ማድረግ አለባቸው…..”
”ህክምና የት?”
”አማኑኤል የአዕምሮ ሆስፒታል …….እናም የደምስን ስራ ደርበህ እንድትሰራ ማኔጅመንቱ ወስኗል።”
”የአቶ ደምስን ስራ ለመሸፈን ፈቃደኛ ነኝ….ግን አቶ ደምስ የይልማን ሥራ ለአመታት ደርበው ሲሰሩ ነበር!!” ስል ሀቁን ፍርጥ አደረኩት፡፡
”ጉድ ነው !እንዴት ሆኖ!” ብለው ቱግ ይላሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ በተቃራኒው ሰውየው ፊት ላይ ቅንጣት የመደነቅ ስሜት የለም፡፡ እንዲያውም በሰከነ አንደበት….
”አዎ! ማኔጅመንቱ ያውቀዋል….የአዕምሮ ህመም እንደ ጉንፋን በማንም ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡…. በእኔም….በአንተም……..”
‘አንተም’  አፈጠጥኩባቸው…..
”…….እናም ይልማ የችግሩ ሰለባ ከሆነ ሰነባበተ…ግን ሁለቱ በፈጠሩት የቅዠት ዓለም ሥራው ሳይበደል እስከቀጠለ ድረስ ማኔጅመንቱ ጣልቃ የሚገባበት ምክንያት የለም…”
‘የቅዠት ዓለም’ የሚል ቢሮክራሲያዊ ስያሜ የተሰጠውን ራዕይ ለማስቀጠል ሀላፊነት ተቀብዬ ከቢሮአቸው ወጣሁ፡፡…. የድርሰቴ ፍጻሜ ፍንትው ብሎ ታየኝ…. ለመሆኑ በትክክል ዕብዱ ማን ነው…. ይልማ፣ ደምስ፣ አለቃዬ ወይስ …እኔ…..?
መታጠፊያ ላይ ጭቃ አዳልጦ ጣለኝ… ከገባሁበት የምናብ ዓለም ወደ ገሀዱ ተመለስኩ፡፡ በአፍጢሜ ነበር ጭቃው ላይ የተደፋሁት፡፡… ከላይ እስከ ታች በጭቃ ተለውሼ ቤት ደረስኩ፡፡
ምሥሌን በቁም ሣጥኑ መስታወት አየሁ፡፡ ፊቴ ላይ የተመረገው ጭቃ ወፈፌ አስመስሎኛል፡፡ ከደቂቃዎች በፊት ራሴን የጠየኩት ጥያቄ ደግሞ አቃጨለብኝ…..
“ለመሆኑ ዕብዱ ማን ነው?” አልኩ፤ ሌባ ጣቴን ወደ መስታወቱ ቀስሬ፡፡… የምስሌ ነፀብራቅ ሌባ ጣቱን ወደ እኔው ጠቆመብኝ…. ‘አንተው ነህ ወፈፌው’  በሚል አይነት ……
ተጣጥቤ ፒጃማ ለወጥኩ….፤ለመጻፍ ተቀመጥኩ……
ነፀብራቅህ ከጠራው መስታወት ሀቁን አመላክቶሀል፡፡ ታሪኩ በአንተ ዕብደት ተቋጭቷል። እናም ያለቀ ታሪክ ለመፃፍ በከንቱ ባትለፋ….የሚል ኩልል ያለ ድምጽ የሰማሁ መሰለኝ፡፡
ቅስሜ ሥብር አለ….. የቢሮ ባልደረቦቼን የዕብደት ጉድ ለመጻፍ የነበረኝ መነሣሣት ከሰመ፡፡ መፃፍ ለኔ መተንፈስ እንደማለት ነው፡፡ ሥነጹሁፍ ስራዬ አይደለም - ዕጣ ፋንታዬ እንጂ፡፡ የተረገመ ዕጣ ፈንታ። አባዜ፡፡ ልክፍት፡፡
የሠው ልጅን ነቢብ ነፍሱን፣ የመንፈሱን ረቂቅነት በስነ-ፅሁፋዊ ውበት ፈልቅቆ ማውጣት… ያኔ የውበት ልዕልና…. እንኳን ይህን መሰል ጥልቅ እሳቤ፣ ተራ ሀሳብ መፃፍ አልቻልኩም፡፡
ሀሳብ በድንገት መምጣቱ አይቀርም፡፡ ከኔ የሚጠበቀው በተስፋ መቁረጥ መጠበቅ ነው፡፡ ….ድንገት የሆነ ሀሳብ እንደርችት ብልጭ! አለልኝ …. ድርግም !ከማለቱ በፊት በምናቤ ላፍ! አደረኩት፡፡
የፀሀፊነት ሀድራዬ ተለኮሰ፡፡ ውቃቢዬ እንደመራኝ ወደ አንዲት መንደር አቀናሁ፡፡… ቆሌዬን ተከትዬ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተሽሎከለኩ፡፡ እኩለ ለሊት አልፏል፡፡ ውቃቢዬ መግቢያ ቀዳዳ አጥታ ዋተተች፡፡ ግን ወዲያውኑ አኪር ወረደላት፡፡ የአንድ መደብር በር ቁልፍ ተሠብሮ በተከፈተባት ቅጽበት እንደ መጋኛ ዘው ብዬ ገባሁ፡፡… ከባንኮኒው ረብጣ ብሮች ወደ ቦርሳው በሚያጭቅ ዘራፌ ላይ የብዕሬ ዛር አረፈበት፡፡ እንደ ቀትር ልክፍትም ተጠናወትኩት፡፡ ነቢብ ነፍሴ ከገጸ-ባህሪው ጋር በማይታይ ቀጭን ክር ተሣሠረች፡፡
የማከብረው ሀያሲ ከአንደኛው የአዕምሮዬ ጓዳ ብቅ አለ፡፡ እንደ ምፅዓት ቀን ውርጅብኝ….
ሥነ-ፅሁፍ ማለት የድግምትና የጥንቆላ ቃላት የምንዘረግፍበት ቤተ-ጣዖት ነውን…ውቃቤ፣ መጋኛ፣ ልክፍት፣ አዚም፣ አኪር፣ ቆሌ……..በሚሉ ቃላት ታጭቆ የተጨማለቀ ለዛቢስ ድርታ፡፡ ፀሀፊው የእርኩስ መንፈስ አፈ ቀላጤነቱን በገሀድ ያሣየበት… የሥነ ፅሁፍ ጣዕም የራቃቸው፣ በጥንቆላ ጠረን የተነከሩ አፍዝ አደንግዝ ቃላት፡፡…. ደራሲው በእነዚህ አዚማም ቃላት እንደ ሰረገላ ተሣፍሮ በመዘረፍ ላይ ያለ መደብር ይገባል፡፡ ዘራፊው ላይ የብዕሬ ዛር ወረደበት..የሚል መያዣ መጨበጫ የሌለው…..
 በቃህ! የሚል ቀይ መብራት ሀያሲው ላይ አብርቼ ብዕሬን ከወረቀት…..
…..ከመደብሩ በቦርሣ የታጨቀ ገንዘብ ዘርፎ ወጣ።… ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ፍጥነት፡፡ ለአፍታም ዘወር አላለም፡፡ እንደ ሎጥ ሚስት የጨው አምድ ሆኖ የሚቀር ይመስል፡፡ መሰወር አለበት፡፡….ወደማይታወቅበት የምድር ጠርዝ …የዘረፈውን ብር በጥቁር ገበያ ወደ ዶላር መነዘረ፡፡….የደቡብ አፍሪካ ጉዞውን ከአዲሰ አበባ-ሞያሌ በሚል አውቶብስ ጀመረ… ቁልቁል ወደ ደቡብ …. ደብረዘይት…ሞጆ….ዝዋይ ላይ ለቁርስ አውቶብሱ ቆመ፡፡ እንትናም ለቁርስ ዝዋይ ላይ ወረደ….
እዚህ ላይ ላይ ገፀባህርዬ ሥም እንደሚያስፈልገው ትውስ አለኝ፡፡ በግዴለሽነት ”ሲሳይ” ስል ሰየምኩት። አዕምሮዬ ”አባ ሲሳይ!” ሲል አቃጨለብኝ…ነፍስ አባቴ አባ ሲሳይ ይባላሉ፡፡ በሠይጣን ላይ ክርስቲያናዊ ቀልድ በመቀለድ ይታወቃሉ፡፡ ዘራፊ ገፀ- ባህሪ እንዳደረኳቸው ከሠሙ መቀበሪያ እንደሚያሣጡኝ የሚጠበቅ ነው፡፡ እናም ሲሳይ የሚለውን ስም ሠርዤ ታደሠ በሚል ተካሁት፡፡ ብዕር የያዝኩበት ጣቶቼ ሲሸማቀቁ አንድ ነገር ትዝ አለኝ…..
አጎቴ ታደሠ ይባላል፡፡ ነገር እንደ ፀጉር በመሰነጣጠቅ ማንም የማይደርስበት ጠበቃ ነው። ነገረ ፈጅ፡፡ የፅሁፉን የመጀመሪያ መስመሮች ብቻ አንብቦ…. ”አጎትነቴን ንቀህ ዘራፊ ገፀ-ባህሪ ታደርገኝ… ከአዲሰ አበባ ሞያሌ… ደቡብ አፍሪካ … ሩቅ ሀገር የምድር ጠርዝ … “ሩቅ ሀገር” ሞት ነው …ዝዋይ ላይ ከአውቶብስ መውረዴ ወደ መቃብር የመውረዴን፣ ግብዓተ መሬት የመፈጸሙን” …በማለት ለእያንዳንዷ ቃል ቀንድና ጭራ የሚቀጥል፡፡ ከንጹህ የፍቅር ታሪክ፣ በአሸባሪነት ሊያስከስስህ የሚችል ቃል መዞ የሚያወጣ መዘዘኛ አጎት!! ድሮስ ‘አጎትና አጓት’ …የሚል አባባል አለ…. ከተባለ መባል ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም እንደ ጋብቻ ሰባት ዘር ቆጥሬ ከቤተ ዘመድ ውጭ ለገፀ- ባህሪዬ ስም የማውጣት፣ ያልተፃፈው ያልጸደቀው ያልተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ያስገድደኛል፡፡ ታደሠን ሠርዤ በደመነፍስ ሞላ የሚል ስም ጻፍኩ፡፡….ሞ እና ላ ፊደላት እንደ መንጠር አደረጋቸው ልበል…..እንደምትሀት ከመቅፅበት የሞላን ጠረንገሎ አካል ፊቴ ድቅን አደረጉት፡፡…. ሞላ ለሰፈርተኛው ውሃ በጀሪካን በአህያ ሸክም አቅራቢ ነው፡፡ የአንድ ወደል አህያ ባለንብረት ነው፡፡ የአህያው ስም እንደባለቤቱ ሞላ ሲሆን አህያው በአራት፣ ሰውየው በሁለት እግሩ ቆሞ ከመሄዱ በቀር ያን ያህል በሁለቱ መካከል የጎላ ልዩነት አይስተዋልም፡፡ ለአመታት ከአህያው ጋር የኖረው ሞላ፤ከአህያው ጋጠ-ወጥ ምግባርን ቀስሟል፡፡ አህያው በሰውየው ላይ ካሳደረው ተፅዕኖ አንዱ ባልተጠበቀ ሁኔታ መራገጥ ይጠቀሳል፡፡ ከወር በፊት ሞላ፤ ጠጅ ቤት በተነሳ አንባ ጓሮ ወልዴን ፊኛው ላይ ረግጦታል። ለወልዴ መቅሰፍት ነበር፡፡ በወደቀበት እንደ ጦሥ ዶሮ መንደፋደፉን የዓይን ዕማኞች መስክረዋል። የእርግጫውም ጦስ ወልዴን እስከ መኮላሸት አድርሶታል…ሞላን ዘራፊ ገጸ-ባህሪዬ አደረኩ ማለት የመኮላሸት ዕድሌን አሠፋሁ ማለት ነው፡፡….
በስም ስያሜ ጊዜዬን በከንቱ አባከንኩት…ለገዛ ዕጣ ፈንታ አሳልፌ የሠጠሁት ገፀ ባህርዬ ሞያሌ ደርሶ ስንቱን መንደር … ሀገር አቆራርጦ ደቡብ አፍሪካ ገባ፡፡…በዚች ቅጽበትም ዚኖፎቢያ (የባዕድ ፍራቻ) አለብን ባዮች ወጠምሻ ጠብደል ደቡብ አፍሪካውያን እንዳይሞት እንዳይሽር አድርገው ደበደቡት፡፡ ዘረፉትም፡፡ በፅኑ ቆስሎ፣ ሆስፒታል ገባ…..
የአስታማሚነት ጭንብል አጥልቄ ገፀ-ባህርዬ ተሽሎት እስኪወጣ መጠባበቂያ ክፍል እየጠበኩት ነው…. እላችኋለሁ፡፡ በተቀመጥኩበት ሸለብ አደረገኝ… ቅኔያዊ ህልም መሰል ሰመመን ……
ሀያሲው ሸለብ እንዳደረገኝ ስላወቀ የአዕምሮዬን በር ሣያንኳኳ በድንገት ዘው ብሎ ገባ፡-
……የተዝረከረከ አጨራረስ - አጀማመሩስ እንዳትለኝ -አልደረስኩበትም፡፡…..ዝዋይ ላይ ለቁርስ የወረደውን ሰውዬ እንደ ዳማ ጠጠር አንስተህ ደቡብ አፍሪካ ላይ ጉብ አደረከው -በብርሃን ፍጥነት፡፡…..የገፀ-ባህሪህን ተሸሎት መውጣት እየጠበክ ነው - ሰመመን ውስጥ ገብተህ….ተሸሎት ሲወጣ ምን ልታደርገው አሰብክ?… በምዳራዊ ህይወቱ ተማሮ ማርስ ውስጥ በሚገኝ ዋሻ የምንኩስና ህይወቱን ሲገፋ…..ከማርሳዊቷ እመቤት ጋር በዝሙት በመውደቁ ምንኩስናውን አፍርሶ - ቆቡን ጨረቃ ላይ ወርውሮ… ጁፒተር ቀለበት ላይ ራሱን በሲባጎ ሲያንጠለጥል እያለምክ ይሆን? ምክንያቱም ቅኔያዊ ህልም መሰል ሰመመን ውስጥ ነህ! ሀቁ ግን የፀሀፊነት ተሠጥዖህ ሙጥጥ ብሎ መንጠፉን እመን! እናም መፃፍ ቢቀርብህ…. በቃህ!... “በህይወት እያለሁ እንዴት ብዕሬን ወደ ሰገባው እመልሳለሁ…” ማለትህ አይቀርም፡፡ ሀቁ ግን የብዕር አሟሟት በአፀደ ስጋ ከመኖርና ከህልፈት ጋር አይገናኝም፤ ሌላ ጉዳይ ነው….ሌላ…..
የብዕር አሟሟት ሌላ……….
ሲፈስ የብሌኑ ኬላ…………
የፊደል መቅረዝ አሟሟት….
ከውስጥ ነው እንደጋን መብራት
በቁም ነው እንደቁም ፍትሀት… እንዲል
ሎሬት ፀጋዬ …….
የብዕር አሟሟት እንዲህ ነው….በቁም ነው….. የቁም ሞት ግነዛ ነው…….የሰብዕና ክሽፈት ነው- በቁም መምከን…. በድን ሥነ -ፅሁፋዊ ፅንስ ውርዴን ያስከትላል -የብዕር አሟሟት……….
ለሀያሲ አብደላ ዕዝራ፤ ሰኔ 05 ቀን 2008 ዓ.ም




Read 3687 times