Saturday, 03 March 2012 14:51

ቤተ-ጊዮርጊስን አየነው!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(3 votes)

ላሊበላ ከተማ ገብተን አንዱ ዋና ሥራዬ ሻወር መፈለግ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ስንነሳ ከተማውን ሊያስጎበኘን ቀጠሮ የያዝኩት ልጅ ጋ ደወልኩኝ፡፡

“ሃሎ ነቢይ፤ አውቄሃለሁ፤ አውቄሃለሁ”

“ከአዲስ አበባ የመጡ እንግዶች ይዤ ላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናቱን እያስጎበኘሁ ነኝ፡፡ ከእነሱ ስለያይ እንገናኛ” አለኝ፡፡

“ችግር የለም አሁን ግን ሻወር ፈልጌያለሁ የት አገኛለሁ?”

“አንተ ባለህበት አካባቢ ላሊበላ ሆቴል የሚባል አለ እዚያ ሂድ”

አመስግኜ ላሊበላ ሆቴል ሄድኩኝ፡፡ እንግዳ ተቀባይዋን አገኘሁዋት፡፡

“ሻወር አለ?”

“አለ”

“ስንት ነው?”

“10 ብር” አለችኝ፡፡ በዛን ቀን ሁኔታ 100 ብርም ብትለኝ ለመክፈል ዝግጁ ነበርኩ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ላሊበላን ራሱን ፈልፍዬ የሠራሁ መሰለኝ! በቅድሚያ ብሩን ከፍዬ ወደ መኝታ ክፍላችን ሄድኩኝ - ልብስ ለማምጣት፡፡ ቅርብ ነው እኛ ካረፍንበት፡፡ ሄጄ “ሻወር ተገኝቷል!” ብዬ የምሥራቹን ነገርኩ፡፡ አርኪሜደስ የተባለው ሳይንቲስት ስለዴንሲቲ ሲያጠና የሚታጠብበትን ገንዳ ውሃ ሞልቶ እግሩን ሲከት የውሃው ከፍታ ሲጨምር፤ የቮሊዩምን ሚሥጥር ባገኘ ጊዜ “ዩሬካ!” (Eureka) እያለ እንደሮጠው ነበር የሆንኩት፡፡ “አገኘሁት!” ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ “ወረፋ ያዝልን” አሉኝ፡፡ ቀድሜ ልታጠብ ሄድኩ፡፡ ሻውር ቤቷ በጣም ታስቃለች፡፡ መቆሚያ ቦታ ብቻ ነው ያላት፡፡ ገረመኝ፡ በአንድ ሰው ልክ የተሰራች ናት፡- በቁመትም በወርድም፡፡ በሩዋ ሲከፈት በቃ ሻወሩ ነው፡፡ ሆኖም እንደጠበል አክብሬያት ታጠብኩባት፡፡ ወረፋ የያዝኩላቸውም እየመጡ ታጠቡ፡፡ ውሃ መድኃኒት ነው ማለት እንዲህ ነው - ዓይነት አስተጣጠብ ታጠቡ፡፡

“ላሊበላ ቤተክርስቲያን እንሂድ!” አልን

“የለም ዛሬ ይጨናነቃል ጠዋት ብትሄዱ ነው የሚሻለው” አሉን፡፡ እንግዲያው ከተማውን ዘወር ዘወር ብለን እንይ ተባብለን ወጣን፡፡ ከተማው ባላገር ነው ለማለት የሚያስደፍር ዓይነት ነው፡፡ ያ መሆኑም ጤና ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ ተዓምራት ውቅር አብያተ- ክርስቲያናትን በቀላሉ መንፈሳቸውን ለመቀበል ከከተማ ይልቅ እዚ ባላገር አሳማኝ ነውና!

ከዚህ በፊት እንዳየነው፤ ላስታና ቅዱስ ላሊበላ የሚገኘው በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በመኪና ከአዲስ አበባ - ደሴ - ወልዲያ - ጋሸናን አድርጎ ቅ/ላሊበላ 700 ኪ.ሜ ወይም ወልዲያ ሲደርሱ ከወልዲያ እስከ ድልብ ተጉዘው፣ በኩል-መስክ በገነተ ማርያም ወደ ቅዱስ ላሊበላ ከተጓዙ በጋሸና ካለው መንድ 60 ኪ.ሜ ቀንሶ 640 ኪ.ሜ ያህል ተጉዘው  ነው፤ ብለናል፡፡

ላሊበላ ከተማ እኛ ወደአረፍንበት ወገን ለቱሪስቶች የሚሆኑ ትልልቅ ሆቴሎች አሉ - የውጪ ሰዎችን በዶላር የሚያስተናግዱ ጭምር፡፡ መለስተኛና ትናንሽ ቡና ቤቶች ያሉበት የከተማው ክፍልም አለ፡፡ እኔ ያንን እመርጣለሁ - ህዝቡ ያለበት ወገን ነውና!

ከፅሁፎቹ እንደምንረዳው የዛጉዌ ነገሥታት ሥርወ-መንግሥትን ማወቅ የላሊበላን ታሪክ ለመረዳት ጠቃሚ ነው፡፡ “ዛጉዌ (ዛጓ) ማለት የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆነው መራ ተክለሃይማኖት በደቡብ ወሎ በሐይቅ እስጢፋኖስ አካባቢ ከሚገኘው ደብረ እግዚአብሔር ከሚባለው ልዩ ሥፍራ፣ ከአፄ ድልነአድ ቤተመንግሥት የአፄ ድልነአድ ልጅ መሶበወርቅን አግብቶ ወደ ላስታ ቡግና ይዞ በመሄድ፣ በመሶበ ወርቅ የዘር ሀረግ ምክንያት ንግሥናውን ወደ ላስታ ቡግና ይዞ ስለኮበለለ በግዕዝ “ዘአጉየየ” ወይም “ዘአጐየ” (ያሸሸ/ያኮበለለ) ከሚለው ቃል የወጣ ነው”

“የላስታ መንግሥት (የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት) ከ10ኛው - 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ከ920-1253 ዓ.ም ግድም) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት ወይም የላስታ መንግሥት በመባል ይታወቃል”

የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት አሥር ሲሆኑ በሦስት ምድብ ተከፍለው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡-

ምድብ አንድ

ቤተ-መድኃኔዓለም

ቤተ - መስቀል

ቤተ - ማርያም

ቤተ - ደናግል

ቤተ - ሚካኤልና ቤተ - ጎልጎታ

ምድብ ሁለት

ቤተ - ገብርኤልና ቤተ - ሩፋኤል

ቤተ - መርቆሬዎስ

ቤተ - አማኑኤል

ቤተ - አባሊባኖስ

ቤተ - ጊዮርጊስ

ምድብ ሦስት

ቤተ - ጊዮርጊስ

እኛ ጉብኝት የጀመርነው ከምድብ ሶስት ነው፡፡ ነገ እምናየው ማለት ነው፡፡ ዛሬ ማታ አንድ ባህላዊ ምግብ ቤት ገብተናል፡፡ የሆኑ ጣሊያናውያን መጡ፡፡ የመካከለኛውን  ጠረጴዛ ሞሉት፡፡ አስተናጋጁ በእንግሊዝኛ ያናግራቸዋል፡፡ ምን እንደሚያዙ ግራ የተጋቡ ይመስላሉ፡፡ እኛ ፓስታ አዘናል፡፡ የእኛ ፓስት ሲመጣ ሁሉም ገልመጥ ገልመጥ እያሉ ፓስታውን ማየት ጀመሩ - ምራቃቸው ሳይመጣ አልቀረም፡፡ ባለቤቷ አንዷን ጣሊያና ጠርታ፡-

“Try this” አለቻት (ይሄን ቅመሽና ሞክሪው)

“እነዚህ ጣሊያኖች ጉርሻ አያቁ ምን እናርጋቸው?” አልኳት፡

“ትምጣና በሹካው ትቅመሳ!?” አለችኝ ባለቤቴ፡፡ እንግዳ ተቀባይ አገር አደለን፡፡ ጣሊያኗ መጥታ በሹካው ሞከረችው፡፡ ተስማማት መሰለኝ በአዎንታ ራሷን ነቀነቀች፡፡ ባለቤቴ፤

“Try Again!” አለቻት (“አንድ ያጣላል” እንደማለት ነው በባህላዊ ቋንቋ) ጣሊያኗ ግራ እየገባት ደገመች፡፡

“ግራሴ!” ብላ ሄደች፤ ወደ ወንበሩ፡፡ ማመስገኗ ነው፡፡ እኛ እምንበላውን አዘዙ፡፡ እነዚህ ጣሊያኖች እንግዲህ ትልቁ ሆቴል አርፈው፤ ምግቡ እዚያ ስለሚወደድባቸው ረከስ ያለው ምግብ ቤት መጥተው መብላታቸው ነው፡፡ ፈረንጆቹ ይሄው ናቸው - በቁጣባ ተወልደው፣ በቁጠባ አድገው፣ በቁጠባ ይኖራሉ - በቁጠባ ይሞታሉ!

ከጣሊያኖቹ ተለይተን ላሊበላ ሆቴል ትንሽ ቢራ ጠጥተን፣ የሆድ የሆዳችንን አውርተን ወደማረፊያችን ተመለስን፡፡ መሽቷል፡፡

“ነገ ጠዋት ወደ አሸን ማርያም ለመሄድ የምትፈልጉ፤ በሌሊት ነው የምንነሳው፡፡ ሲኬድ ሁለት ሰዓት ተኩል፣ ሲመጣ ሁለት ሰዓት ተኩል፣ በጠቅላላው 5 ሰዓት የሚፈጅ ብርቱ ዳገት ነው! የማትችሉ ቅሩ!” ተባለ፡፡ ሌሊት ንጋት ላይ ክፍላችን ውስጥ የክርክር ድምፅ ሰምቼ ነው የነቃሁት፡፡ እስካሁን ያስነበብኳችሁን እየፃፍኩ ነው ክርክሩን የምሰማው፡፡

አንዲት አዲስ ልጅ መጥታለች ወደ ክፍላችን - ማታ፡፡ ይቺ ልጅ ወደ አሸተን ማርያም ትሂድ አትሂድ ነው ክርክሩ፡፡

ከፊሉ - “ኧረ ባትሄድ ይሻላታል - የአሸተን ማርያምን መንገድ አትችለውም፡፡ በእንፉቅቅ፣ በእቅፍና በዕዝል እኮ ነው የሚወጣው ባትሞክረው ይሻላል” ይላል፡፡

ከፊሉ - “ምንም አይደለም፡፡ እንኳን እሷ አሮጊቶቹ ይሄዱ የለ ወይ - መንፈሱም አለ፤ ያበረታታል” ይላል፡፡ በመጨረሻ ትሂድ በሚለው ተወሰነና ልብሷን ቀያይራ ካመጣት ልጅ - እኛ ጃፓኑ ነው የምንለው (ጃፓን ነበርኩኝ ስላለ ነው) - ከሱ ጋር ወጣች፡፡

አሁን ከንጋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ነው፡፡ የገና ዕለት 28/04/04 መሆኑ ነው፡፡ አሸተን ማርያም የሚሄዱት ሄዱ፡፡ በግ አራጁ መጥቶ ዋጋ ይደራደራል፡፡ ምግብ ለመሥራት የመጡት ልጆች እየተዘገጃጁ ነው፡፡ እሳት ያያይዛሉ፡፡ ወደ ላሊበላ ቤተክርስቲያን የሚሄዱት እየሄዱ ነው፡፡

“የላሊበላው ዋናው በዓል መቼ ነው?” ብዬ ጠየኩ፡፡

“ዋናው በዓልማ እሁድ ነው - እሁድ 29 - ታህሳስ ነው፡፡ ቅዱስ ላሊበላ የተወለደበት ቀን ነው ወረቡ የሚታየው፡፡ ቄሶቹም ተጨቃጭቀውበታል፡፡ “ዘንድሮ ገና በ28 ስለዋለ፤ የጌታችንን ልደት በገና ማክበር አለብን” በሚሉና “የለም ከቅዱስ ላሊበላ ልደት ጋር እሁድ በ29 እናክብር” በሚሉ መካከል፡፡ በመጨረሻ “አንድ ላይ እሁድ ይከበር” የሚሉት አሸነፉ አሉኝ፡፡ በኋላ ከአዲስ አበባ እንደኛ ወደ ላሊበላ የመጣ የላሊበላ ማህበር አባል እንዳጫወተኝ “እንዲያውም እኛ በ28 የገና እለት ፆመናል’ኮ፡፡ በሹሮ ነው እያደርነው” ብሎኛል፡፡

በጋችንን ሊያርድ የመጣው ልጅ፤ “ቅዳሴ ለአሥር ሩብ ጉዳይ ገብተዋል” አለን፤ ቢላዋውን እያፋጨ፡፡

እኛ ቤተ - ጊዮርጊስን ለማየት የወሰንነው ለዛሬ ነው፡፡ ቤተ - ጊዮርጊስ እኛ ካረፍንበት የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ቅርብ ስለሆነ ረፈድ አድርገን መውጣት እንችላለን ተባባልን፡፡ በጉ እየታረደ ነው፡፡ እኔ ፊቴን ወደ ገና አዙሬ ተኛሁ!!

ረፋዱ ላይ ተነስተን ወደ ቤተ - ጊዮርጊስ አመራን፡፡ አቋራጩን ቀጭን መንገድ ከመጀመራችን በፊት አንድ ድንኳን አየን፡፡ ድንኳኑ ውስጥ ያሉት ሰዎች የታረደውን በሬ የሚበልቱ፣ የሚዘለዝሉ ናቸው፡፡ ሰው አጣዳፊ ሥራ ይዞታል ማለት ነው፤ አልኩኝ በሆዴ፡፡ ቀጭኗ መንገድ እንደስሟ ቀጭን አደለችም፡፡ ዳገት፣ ቁልቁለት፣ ጠመዝማዛ የመንፈስ መንገድ ናት፡፡ የማተብ መንገድ ናት - የማትበጠስ! የዋዛ አይደለች፡፡ ከቤተክርስቲያኑ በላይ ገበያ አለ፡፡

ቤተ ጊዮርጊስ ቅዱስ ላሊበላ ካነጻቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከሁለቱ የቤተ ክርስቲያን ስብስብ ፈንጠር ብሎ (ከላይ ምድብ ሦስት ያልነው) ከመንደሮቹ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ሁለት ወንዞች ከሚገኙበት ሸንተረር አፋፍ ላይ ከዓለታማው አካባቢ ነው የሚገኘው፡፡ ቤተመቅደሱ ሙሉውን ከአናት ሲታይ የመስቀል ቅርጽ ያለው ነው፡፡ ድንቅ ነው! ቤተ ጊዮርጊስን አየነው!!

“እንዴት ለብቻው ሊታነጽ ቻለ?” አልኳቸው አንዱን አዛውንት፡፡

“ቅዱስ ላሊበላ በምድብ አንድና ሁለት የሠራቸውን አብያተ ክርስቲያናት አንፆ ሲጨርስ - ካህናቱ የገለፁትን ነው የምነግርህ - ወዲያውኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያምረው ነጭ ፈረሱ ላይ ተቀምጦ ወደላሊበላ ይመጣና በእርሱ ስም ቤተ መቅደስ እንዳልተሠራ ይነግረዋል፡፡ ቅዱስ ላሊበላም ወዲያውኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን ቃል እንደሰማ ወደዚህ ዓለታማ ቦታ በመምጣት በስሙ ይህን ህንፃ አነፀለት፡፡”

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፤ ቅዱስ ላሊበላ ካነፃቸው ሁሉ በአጠራረቡና በአወቃቀሩ የተለየ ነው፡፡ ያማረና ልዩ መስህብ ያለው ነው፡፡ በአለቱ ላይ የሚታየው የፈረሰ ኮቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን ከሥራው ጋር አብሮ መኖር ያሳያል፤ የሚሉ አሉ፡፡ በመስቀል ቅርጽ የተሠራ ነው፡፡ ወለሉም የመስቀል ቅርጽ አለው፡፡ ቤተ - ጊዮርጊስ እንደ አንድ ግንብ በመስቀል ቅርጽ የወጣ ሆኖ ውስጡ ተቦርቡሮ ክፍል ያለው አይመስልም፡፡ ላሊበላን ወክሎ በየምስሉ የሚታየው ቤተ - ጊዮርጊስ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ በየበሮቹና መስኮቶቹ የታችኛው ጠርዝ ላይ ያሉ የቅርጽ አወጣጦችን ስንመለከት በአክሱም የምናያቸው ጥበቦች እዚህም ይንፀባረቃሉ፡፡

በታችኛው የቤተክርስቲያኑ ክፍል ያሉት ዘጠኙ መስኮቶች ጌጣቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ወደላይ ያሉት 12 መስኮቶች ግን በመስቀል ቅርጽ የተዋቡ ናቸው፡፡ በውስጥ ሲታዩ አራቱ አምዶች በጥበብ የተሠሩ ናቸው፡፡ ምስሎቹ ውብ ናቸው፡፡ ሦስት ማዕዘን ያለው ቅርጽ ከግድግዳው ጋር ሆኖ ለቤተክርስቲያኑ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ የ23 ዓመታት ጥረት እዚህም ተንፀባርቋል፡፡ በአንድ ጽሑፍ እንደተገለጠው፡- “ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን ለመስራት ያስፈለገበት አብይ ምክንያት በዘመኑ የነበሩ ምዕመናን እንደአሁኑ የመገናኛው መንገድ ባልበለፀገበት ዘመን፤ ከዕምነታቸው ጽናት የተነሳ ስንቃቸውን ሰንቀው፣ በእግራቸው የብዙ ወራትንና ዓመታትን አድካሚ ጉዞ አድርገው እየሩሳሌም በሚደረገው ጉዞ አቅጣጫን ካለማወቅ፣ በስንቅ ማለቅ፣ በአውሬ በመበላት፣ በፀሐይ ሀሩር፣ በውኃ ሙላት፣ በሽፍታ ወዘተ እየጠፉም መንገድ ላይ እንደወጡ የሚቀሩ ስለነበሩ ከዚህ እየሩሳሌም በሚደረገው ጉዞ ፈንታ፣ ዳግማዊት እየሩሳሌምን ኢትዮጵያ ውስጥ በመፍጠር ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ያለምንም አድካሚ ጉዞ ቅዱስ ላሊበላ ወዳነፃቸው ቅዱሳን ስፍራዎች በመሄድ በረከት እንዲያገኙ፣ የእግዚአብሔርንም ድንቅ ሥራ  እንዲመለከቱ ለማድረግ ነው፡፡”

ይህን ቦታ ስናይ መንፈስ እንደአለት ሊፀና እንደሚችል እንገነዘባለን!

የቤዛ ኩሉን ሥርዓት ነገ እስከምናይ ናፈቅን የዘጠኙ አብያተ ክርስቲያናት ቅጽር እኛኑ እየጠበቀ ነው፡፡ ወደ ነገ ፊታችንን አዙረን ለ”ቤዛ ኩሉ” እንዘጋጅ!

(ይቀጥላል)

 

 

 

Read 4749 times Last modified on Saturday, 03 March 2012 15:11