Saturday, 18 June 2016 12:59

ከርከሮ አንዲት ፀጉር አለችው፣ እሷኑ ለማጥፋት ይተሻሻል

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አህያና አንድ ለማዳ ውሻ በአንድ ጌታ ቤት ይኖሩ ነበረ፡፡
አህያው ከጋጣ ውስጥ ብዙ አጃና ገብስ እንዲሁም ሳር ተደርጎለት እስኪጠግብ እየበላ ይተኛል፡፡ ትንሹ ቡችላ ውሻ ደግሞ ሳሎን ውስጥ ለእሱ በተዘጋጀለት ሶፋ ላይ ይቀመጣል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በጌታው ጭን ላይ ቂብ ይላል፡፡ ጌትዬው ምግብ የሚበላ ከሆነ ለውሻው ይቀነስና ይሰጠዋል፡፡ ወደ ውጪ ለራት የወጣ እንደሆነም በከረጢት ለውሻው ያመጣለታል፡፡ ውሻውም ጭራውን እየቆላ ይሮጥና ገና ከደጅ ይቀበለዋል፡፡
አህያው በጣም ብዙ ሥራ አለበት፡፡ ወፍጮ ቤት የሚፈጭ እህል ተሸክሞ ይሄዳል፡፡ ከተፈጨ በኋላም ተሸክሞ ይመለሳል፡፡ ወደ እርሻ ቦታም እየሄደ.፣ የተከመረ እህል በኩንታል እየተሞላ ይጫንበትና ወደ ቤት ይመጣል፡፡ ለአህያው፤ ሸክም የዕድሜ ልክ ሥራው ነው፡፡
አህያው በለማዳ ውሻው ምቾትና የቅንጦት ኑሮ በጣም ቅናት ገባውና፤
“እስከ መቼ ድረስ ነው፤ እኔ እዚህ ጋጣ ውስጥ ተቀርቅሬ የምኖረው? እስከ መቼሽ ነው እኔ እንደዚህ ውሻ ሳልንደላቀቅና ኑሮ ሳይደላኝ፣ አንድም ቀን ሳሎን ሳልገባ የምቀመጠው?” ሲል አሰበ፡፡
በመጨረሻም አንድ ቀን ተነስቶ፣ ጋጣውን ሰባብሮ ወጥቶ ወደ ጌታው ቤት አመራ፡፡ ጌትዬው እራት ሊበላ እንደተቀመጠ፣ አህያ ሆዬ ሳሎን ገባ፡፡ እንደ ውሻው ጭራውን እየቆላ፣ እንደ ውሻ “ው ው ው!” እያለ ይጮህ ጀመር፡፡ ይጎማለልና በማላገጥ መልክ ውሻው የሚያደርገውን በመኮረጅ፣ ለጌታው እንደ ቲያትር ያሳይ ገባ፡፡ ጠረጴዛውን በእርግጫ አለው፡፡ የጠረጴዛ ልብሱንም ገፈፈው፡፡ በዚህ ብቻ ባለመርካቱ፣ እንደ ውሻው ጌታው ጭን ላይ ለመቀመጥ ሁሉ ሞከረ፡፡ “የጌታዬ ጭን፤
ለውሻ ተፈቅዶ፣ እኔ ለምን እከለከላለሁ?” እያለ ጮኸ!
ይሄኔ አሽከሮቹ ጌታቸው አደጋ ላይ መሆኑን በመገንዘብ፣ በዱላ፣ በፍልጥና በጅራፍ ቀጥቅጠው ቀጥቅጠው፣ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው፣ አቁስለው፤ ወደ ጋጣው እየነዱ አስገቡት፡፡
አያ አህያ ቆሳስሎ፤ ተሰባብሮ፣ ጋጣው ውስጥ ተኝቶ እያቃሰተ፤
“አዬ! ምነው አርፌ ብቀመጥ? ምነው በተፈጥሮ የተሰጠኝን ማንነቴን አክብሩ ብኖር? በገዛ እጄ፣ ያለ ተፈጥሮዬ፣ ውሻን አክል፣ ውሻን እሆን ብዬ፣ ራሴ ላይ መዘዝ አመጣሁ!” አለ
*          *         *
ያልሆንነውን እንሁን ብለን የሌሎችን ህይወት ለመቀዳጀት መሞከር ቀቢፀ - ተስፋ ነው! ተፈጥሮአችን የማይፈቅደውን ነገር ለመሆን መዳከር ክፉ አባዜ ነው፡፡ በክህሎት የሌላውን ተፈጥሮ “ውስጤ ነው” ማለት ከንቱ ድካም ነው፡፡ ክህሎት ወይም ብቃት የራስን ትጋት የሚጠይቅ ቢሆንም ሰብዕናን፣ ሥነ ምግባርንና ተፈጥሮአዊ ማንነትን ማማከሉን መገንዘብ ያባት ነው፡፡ ማንም የማንንም ቦታ ለመተካት በቅንዓት፣ በምቀኝነትና “በምን - ይጎለኛል?” ሊያደርገው አይችልም፡፡
በሀገራችን ግን፤ ቅንዓትን ከመልካም አስተዳደር፣ ዕድልን ከጥሮ - ግሮ ማግኘት፣ እያምታታን ዘራፍ ማለት እየተለመደ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ ሌላውን ቦታ ከመመኘት ይልቅ ኃላፊነትን መወጣት ነው ዋናው ጉዳይ! በውስጥና በውጪ ኦዲተር የሚመጣብንን ሪፖርት በተግባር ምን ይሁን? ምን እርምጃ እንውሰድ ማለት ተገቢ ነገር ነው! ችግሮቻችን ብዙ ናቸው፡፡ የማስተር ፕላን ጣጣ፡፡ ያላግባብ መሬት መያዝ፡፡ በተሰጠን ቦታ ላይ ግንባታ አለማካሄድ፣ ለባለስልጣናት የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም “እኔ ታክስ ከፋይ ነኝ” (I am a tax - payer) ከሚለው ህዝባዊ አስተያየት ጋር አለማዋሃድ፡፡ ፍትሕ ተዛባ፣ ህጋዊነት ጠፋ … የሚልና ጩኸት የሚሰማ ጆሮ መጥፋት፡፡ የዲሞክራሲ በወገናዊነት እንደ አሸቦ ተሸብቦ መቅረት፡፡ የመልካም አስተዳደር ሽባ ሆኖ በከዘራ መሄድ፡፡ ምኑ ቅጡ፡፡ ዛሬ ደግሞ የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት ማገርሸት! የጎረቤት አገርን እብሪት ለመግታት በማቴሪያል፣ በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ የምናወጣው ወጪ ጎጂነት የትየለሌ ነው፡፡ ሲሆን ሰላምን የማስፈን የሞራል ዋጋ በከፈልን ደግ ነበር፡፡ “ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት መስጠት” ካልንም፣ ትንኮሳው ከባላንጣችን መምጣቱን አመላካች ነውና ሁሉን በወጉ መያዝ ይጠበቅብናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው!
አንድ አዛውንት ከዓመታት በፊት፣ በመጀመሪያው ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት፤ የትግራይ ሰው ሆነው በኤርትራዊ ድምፃዊ ዘፈን ሲደንሱ ታዩ፡፡
“እንዴት ጦርነቱ ሊጀመር አንድ ሃሙስ ሲቀረው፣ በኤርትራዊ ዘፋኝ እስክስታ ይወርዳሉ?” ቢባሉ፤
“አይምሰላችሁ፡፡ እዚህ ድንበር ላይ የጀርመን ግንብ እንኳ ቢገነባ፣ የሙዚቃ ካሴት መቀባበያ ትንሽ መስኮት ትኖራለች” አሉ ይባላል፡፡
የሁለቱ ህዝቦች ባህላዊ ትሥሥር ምንጊዜም ይኖራል ማለታቸው ነው፡፡ ይህን ዕውነታ ማንም አይክደውም፡፡ የጎረቤት አገር አምባገነን መሪ ምንም አቋም ይውሰድ ምንም፣ “ወረራ ውስጤ ነው፡፡ ማስወረርም ውስጤ ነው!” ቢልም እንኳን፤ የሁለቱ አገር ህዝቦችን ትሥሥር መናቁ ነውና፣ አስተሳሰቡ በማናቸውም መንገድ መሻር አለበት፡፡ ስለሆነም፤ “ከርከሮ አንዲት ፀጉር አለችው፡፡ እሷኑ ለማጥፋት ይተሻሻል” የሚለው ተረት የእሱ ይሆናል!

Read 8684 times