Saturday, 03 March 2012 14:49

ጉዞ ወደ ጐንደር - (የጉዞ ማስታወሻ - ክፍል 6)

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

የመጨረሻዋ ቀን

እርግጥ በሯ ጠባብ ናት፡፡ ከአንድ ሜትር የዘለለ ቁመት የሌላት “አስጐንባሽ” በር ናት፡፡ ይህቺን ጠባብ በር አጐንብሰን ስናልፍ የምናገኛት ክፍልም እንዲሁ ጠባብ ናት፡፡ በዚህች ጠባብ ክፍል ግድግዳ ላይ የከብት ይሁኑ የሌላ እንስሳ የማያስታውቁ ሹል ቀንዶች በመደዳ ተሰክተው ይታያሉ፡፡ እነዚህ ቀንዶች 22 ያህል ነበሩ፡፡ የተወሰኑት ከቦታቸው ተነቅለው፣ የተወሰኑት ተሸራርፈው ጥቂት ብቻ ቀርተዋል፡፡ የቀንዶቹን ሚስጥር ለማወቅ እንደጓጓሁ በሌላ ጠባብ በር ወደ ቀጣዩዋ ጠባብ ክፍል ዘለቅኩ፡፡ ጨለማ ባረበበባት (በዚህች ክፍል) መሀል ላይ ሰፊ ምድጃ ይታያል፡፡ ጣራዋ ላይ ደግሞ መክደኛ ያላቸው ስድስት መጠነኛ ቀዳዳዎች አሉ፡፡

“ምን ያለው የጉድ ዋሻ ውስጥ ገባሁ?” የሚል ስሜት በውስጤ ይመላለሳል፡፡ የቀንዶቹን ሚስጥር ሳልፈታ፣ ”ምድጃው” ሌላ እንቆቅልሽ ሆኖ ከፊት ለፊቴ አፉን ከፍቷል፡፡

የነገስታት መኖሪያ በነበረ በዚህ አፅድ ውስጥ ይህቺ “ጓዳ” ምን ትሰራለች? እያልሁ አስባለሁ፡፡ የቀንዶቹንም፣ የምድጃውንም ሚስጥር ለመፍታት አልተቻለኝም፡፡

እርግጥ የሚቻልም አልነበረም፡፡ ይህቺ ጠባብ ክፍል ከዘመናት በፊት የነበረን የአገር ስልጣኔ የምትዘክር አስገራሚ ክፍል እንደሆነች መገመት የሚቻል አልነበረም፡፡

“ስቲም ባዝ” ብሎ ነገር ወዲህ ወደ አገራችን ከመጣ በጣት የሚቆጠሩ አመታት እንደሆነው እንጂ፣ እዚህች ጠባብ ክፍለ ውስጥ ከዘመናት በፊት ይሰራበት እንደነበር የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን?

ይህቺ ጠባብ ክፍል የአፄ ፋሲል የእንፋሎት መታጠቢያ ናት፡፡ ነገስታቱ በዚህች ክፍል ውስጥ ከዘመናት በፊት በእንፋሎት ይታጠቡ ነበር፡፡

እንዴት?

እንዲህ …

ጠባቧ ክፍል መሀል ላይ ባለው የጉድጓድ ምድጃ ትልልቅ ጥቋቁር ድንጋዮች ይቀመጣሉ፡፡ ከምድጃው አንድ ጐን ላይ በሚታየው ሰፊ ቀዳዳ ደግሞ የፍልጥ እንጨቶች ይማገዳሉ፡፡ እናም እሳት ይለኮስባቸዋል፡፡ በፍልጥ እንጨቶቹ ነበልባል የሚጠበሱት ጥቋቁር ድንጋዮች ቀስ በቀስ ቀለማቸውን ለውጠው መቅላት ይጀምራሉ፡፡ ምድጃው የፍም አለሎ በሰሩ ድንጋዮች ይሞላል፡፡

ይሄኔ ጣራው ላይ የሚታዩት ስድስቱ ቀዳዳዎች ይከፈቱና ቀዝቃዛ ውሃ ቁልቁል ይፈስባቸዋል፡፡ ውሃው ወደ ምድጃው ቁልቁል ወርዶ ፍም የሰሩ ድንጋዮች ላይ ሲያርፍ አንዳች እንፋሎት ሽቅብ መትጐልጐል ይጀምራል፡፡ ቀዳዳዎቹም ጠባቧ በርም ሁሉም ስለሚዘጉ ክፍሏ በእንፋሎት ትታጠናለች፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ነገስታቱ ከላያቸው የደረቡትን ልብስ አውልቀው ከመጀመሪያዋ ክፍል ግድግዳ በተሰኩት ቀንዶች ላይ አንጠልጥለው እርቃናቸውን ወደዚህች ክፍል የሚመጡት፡፡

ከምድጃው ራቅ ብለው በዱካ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠውም በእንፋሎት መታጠን፣ በላቦት መወርዛት ይቀጥላሉ፡፡

እኛም መጐብኘታችንን እንቀጥላለን …

ይሄ … “ፈረስ ባልደራስ በር”ን ከበስተጀርባው፣ ሙያተኛ ተብለው የተመሰከረላቸው ሴቶች ጥበባቸውን የሚያሳዩበትን “የወይዛዝርቶች ቀጭን ፈታዮች ግንብ” ደግሞ ከፊት ለፊቱ አድርጐ ከመካከል የሚታየን ህንፃ ደግሞ የብርሃን ሰገድ ቋረኛ ኢያሱ ቤተ-መንግስት ነው፡፡ ከእሱ አለፍ ስንል 55 ሜትር በ6 ሜትር ስፋት ያለው የአፄ በካፋ ቤተመንግስት የግብር አዳራሽ ይጠብቀናል፡፡ አፄ በካፋ ሴት ከወንድ ሳይለዩ ሁሉን በአንድ ነበር ግብር የሚያበሉት፡፡

ከግብር አዳራሹ ፊት ለፊት ዘጠኝ በሮች በመደዳ ተደርድረው ይታያሉ፡፡ ለግብር የሚመጡ መኳንንቶችና ሹማምንት ፈረስና በቅሎዎቻቸውን እነዚህ በሮች ላይ ነበር በስርአት አሰልፈው የሚያቆሟቸው፡፡

እነዚህን በሮች እየተመለከትኩ “ስቲም ባዝ” ብቻ ሳይሆን “ፓርኪንግ”ም እዚህ ግቢ ውስጥ ከዘመናት በፊት ነው የተጀመረው” አልኩ በጥናት ሳይሆን በግርምት በመነሳሳት፡፡

የአፄ አዕላፍ ሰገድ ፃድቁ ዮሃንስ፣ የአፄ ዳዊት ሳልሳዊ፣ የእቴጌ ምንትዋብ … የሁሉንም አብያተ - መንግስታት ጥንታዊ ህንፃዎች እየተዘዋወርኩ እቃኛለሁ፡፡

የአንበሶች ማደሪያ የነበረውን “አንበሳ ጓዳ”፣ የወቅቱ ሰአሊያንና ፀሐፍት የብራና ፅሁፍ ያዘጋጁበት የነበረውን “ቤተ-መዛግብት”፣ የአፄ ፋሲል አበጋዝ ወደ ግቢው የሚገቡ ሰዎችን ይቆጣጠርበት የነበረውን የማማ ፍርስራሽ፣ “የወረቀት ግንብ”ን … ሁሉንም አንድ በአንድ እጐበኛለሁ፡፡

እዚህ ግቢ ውስጥ ብዙ ነገር አለ፡፡ የጐንደር ጥንታዊ ስልጣኔና ታሪክ የሚዘክሩ ብዙ ቅርሶችና መስህቦች በዚህ አፅድ ውስጥ አሉ፡፡

ከአፄ ፋሲል ግቢ ወጣ ቢሉም የሚያዩት ነገር አያጡም፡፡ አይተው የሚደነቁባቸው፣ ታሪክ ተናጋሪ ስልጣኔን ዘካሪ የቱሪስት መስህቦች ሞልተው የተረፉባት ከተማ ናት - ጐንደር፡፡

እቴጌ ምንትዋብ ያሳነጿት ደብር ፀሐይ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን እነ አለቃ ገብረሃና የመፅሐፍት ትርጓሜ ያስተምሩባት እንደነበር ይነገራል፡፡ የአፄ ብርሐን ሰገድ ኢያሱና የእቴጌ ምንትዋብ አፅም የሚገኝባት ይህቺ ተራራ ላይ የምትገኝ ቤተ-ክርስቲያን በውስጧም ሆነ በዙሪያዋ በሚገኙ ጥንታዊ ህንፃዎች ብዙ ጥንታዊ መፅሐፍትና ቅርሶች ይዛለች፡፡

ውቅያኖስ ተሻግሮ የመጣው እንግሊዛዊው ታሪክ ፀሐፊ ጀምስ ብሩስ ከእነዚህ ጥንታዊ ቤቶች በአንደኛው አርፎ ስለ ጐንደር ብዙ እንደፃፈም ይነገራል፡፡

ወዲህ ደግሞ ሌላዋ የጐንደር መስህብ አለች - ደብረብርሐን ስላሴ፡፡ በአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተሰራችው ውቧ ደብረብርሐን ስላሌ፣ ጐንደር በደርቡሾች እሳት በጋየችበት ጊዜ እንኳን ነበልባሉ ሳይበግራት፣ እሳቱ ሳይፈታተናት፣ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባት ከእነ ሙሉ ውበቷ ዘመን ተሻግራ ዛሬም የጐንደር መስህብ ሆና አለች፡፡ እየመሸ ቢሆንም የጐንደርን ጐዳናዎች ተከትለን መጓዛችንን ቀጥለናል፡፡ ትናንቷን ከዛሬዋ ጋር እያሰናሰልን እንጐበኛታለን፡፡

እድሜና እርጅና ቢጫጫኗትም ጐንደር ሙሉ ሽበት አልወረሳትም፡፡ ከጥንታዊ ህንፃዎቿ ውስጥ አዳዲስ ፎቆች ይበቅሉ ጀምረዋል፡፡

“አረጀሽ እያሉ ሰዎቹ ሲያሙሽ

ሙሽራ ነሽ ጐንደር ይሰፋል ልብስሽ” እያሉ የሚያቀነቅኑላት ጐንደር እርግጥም ሙሽራ መስላለች፡፡ በተራራ መቀነት ስር ከ5ሺህ 560 ሄክታር በላይ በሆነ ምድር ላይ የተንጣለለችው ጐንደር ከ300 ሺህ በላይ ህዝብ ይኖርባታል፡፡

ጐንደር ከፈረንሳዩዋ ቬንሰነስ፣ ከአሜሪካዊ ኮርቫሊስ፣ ከእስራኤሏ ሬሽንፅዬን ከተሞች ጋር የእህትማማችነት ስምምነት ፈጥራለች፡፡ ከስፔንና ጀርመን ከተሞች እህት የሚሆናትን ለመምረጥም እየተሰናዳች ትገኛለች፡፡

ባለፈው አመትም አዋሳና ጐንደር “እህቴ”፣ “እህቴ” ተባብለው ተዛምደዋል፡፡ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው ጐንደር እንግዶቿን በአግባቡ ተቀብላ የምታስተናግድባቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ያላቸው 103 ያህል ሆቴሎች አሏት፡፡ 22 ፔንሲዮኖችና 63 የሚደርሱ ደረጃቸውን የጠበቁ ሬስቶራንቶች የሚገኙባት ጐንደር፣ ተጨማሪ 45 ሆቴሎችና ሎጆችን እየገነባች ትገኛለች፡፡

እየመሸ ነው …

ጐንደር የሙዚየሞቿን በሮች ዘጋግታ የምሽት ቤቶቿን በሮች መከፋፈት ጀምራለች፡፡ እንዲህ ሲመሻሽ እነ “ብርቧክስ”፣ እነ “ኮራው በባህሌ”፣ እነ “ባላገሩ” … ሌሎች የባህል ምሽት ቤቶች ታዳሚዎቻቸውን ለመቀበል ተፍ ተፍ ማለት ይጀምራሉ፡፡

በወጉ እንዲነባ ፀሐይ ላይ ተሰጥቶ የዋለው አታሞ ድምድምታውን ይጀምራል፡፡ የጐንደር አዝማሪ የመሰንቆውን ጭራ በእጣን ሳስሎ ብድግ ይላል፡፡

“አንቺ ጐንደሬ

እንዳገርሽ እንዳገሬ” ብሎ ያዜምላታል አዝማሪው፡፡

“አንተ ጐንደሬ

እንዳገርህ እንዳገሬ” ስትል ትቀበለዋለች - ሴቲቱ፡፡ እየተቀባበሉ ያቀነቅናሉ፡፡ ጐንደር ስትዘፍን ታመሻለች፡፡ ከሩቅ የመጣው ቱሪስትም አብሯት እስክስታ ሲመታ ያድራል፡፡ (አበቃ)

 

 

 

Read 1909 times Last modified on Saturday, 03 March 2012 14:53