Saturday, 18 June 2016 12:39

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት “ብዙ ገድለናል” እያሉ ነው

Written by 
Rate this item
(77 votes)

“የኢሳያስን መንግስት ማስወገድ ያስፈልጋል”
የቀድሞ የአየር ሃይል አዛዥ ሜ.ጀ አበበ

የኢትዮጵያ መንግስት
• በከባድ ውጊያ፣ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሻለሁ
• ትንኮሳ እንዳይፈጽም ትምህርት ሰጥተነዋል
• ካለረፈ ግን፣ በተመጣጣኝ እርምጃ እንቀጣዋለን
የኤርትራ መንግስት
• ሁለት መቶ ወታደሮችን ገድያለሁ፤ አቁስያለሁ
• የአሜሪካ መንግስት ፣ እጁ አለበት፤ ጥቃት አነሳስቶብኛል
• የኢትዮጵያ ጦር ወደ ድንበር በብዛት ተሰማርቶብኛል

የኢትዮጵያ መንግስት በፆረና ግንባር ከባድ ውጊያ ተካሂዶ እንደነበር ገልፆ፣ ትንኮሳ በፈፀመው የኤርትራ ጦር ላይ ከፍተኛ የህይወት ኪሳራ አድርሻለሁ፤ እርምጃውም ለሻዕቢያ መንግስት አስተማሪ ነው ብሏል፡፡ የኤርትራ መንግስት በበኩሉ ባልታወቀ ምክንያት የኢትዮጵያ ጦር በብዛት ወደ ድንበር እንደተሰማራና የአሜሪካ እጅ እንዳለበት የተናገረ ሲሆን፤ 200 ወታደሮችን ገድያለሁ ብሏል፡፡
በኤርትራ መንግስት ላይ አስተማሪ እርምጃ መስደናል ያሉት የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፤ “ሌላ ትንኮሳ ያደርጋል ብለን አንጠብቅም፤፡፡  በድንበር አካባቢ ሌላ ግጭት የሚፈጠር ከሆነ ግን፣ የግጭቱ ብቸኛ ተጠያቂ የሚሆነው የኤርትራ መንግስት ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት፣ ትንኮሳዎችን ለማስታገስና ለመቅጣት ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የኢያሳያስን መንግስት የማውረድ ኃላፊነት ግን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአለማቀፉ ህብረተሰብም የሚመለከት ቢሆንም፣ በዋናነት የኤርትራ ህዝብ ጉዳይ ነው ብለዋል -  ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
“ተመጣጣኝ እርምጃ” የሚባለው ሃሳብ እንደማያዛልቅ የተናገሩት የቀድሞ የአየር ኃይል አዛሽ ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በበኩላቸው፤ ተመጣጣኝ እርምጃ ማለት እነሱ 200 ከገደሉ፣ እኛ 1000 በመግደል እንቀጣቸዋለን በሚል ስሌት እንደመመራት ስለሆነ አያዋጣም ብለዋል፡፡ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ሙሉ ለሙሉ መወገድ አለበት ያሉት ሜ/ጀ አበበ፣ ተመጣጣኝ እርምጃ የሚባለው ሃሳብ ትርፉ እልቂት ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት እና የአሜሪካ መንግስት፣ የድንበር ግጭቱ እንዳሳሰባቸው በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከግጭት እንዲታቀቡ መክረዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት በኢንፎርሜሽን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፣ ባልታወቀ ምክንያት ጥቃት እንደተፈፀመበት ጠቅሶ፣ ከ200 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገድያለሁ፣ 300 አቁስያለሁ ብሏል፡፡
ሃላፊነት በጎደለው ድርጊት ደም መፋሰስ እንዲከሰት የተደረገበት ምክንያት አናውቅም ያለው ይሄው መግለጫ፤ የአሜሪካ መንግስትንና አለም አቀፍ ተቋማትን ኮንኗል፡፡
ከጥቃቱ በፊትና በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግስትን እየደገፉ ነው በማለት፡፡ እነዚህ አካላት እውነታውን በመካድ ወራሪውንና ተወራሪውን እኩል ለማውገዝ ሞክረዋል ሲልም ገልጧል፡፡
በድንበር አካባቢ የኢትዮጵያ ጦር በብዛት ተሰማርቶብኛል፤ በዚህ ውስጥም የአሜሪካ መንግስት እጅ አለበት ብሏል - ትናንት የወጣው መግለጫ፡፡  
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳንዛና ድላሚኒ ዙማ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው የድንበር ግጭት እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፣ ሁለቱም አገራት ከግጭት እንዲርቁ መክረዋል፡፡ ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶችና መግለጫዎች እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን፣ ባለፈው ረቡዕ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሁለቱም አገራት ችግሩን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ አገራቱ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ከ15 ዓመታት በፊት እ.ኤአ. በ2000 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

Read 14793 times