Saturday, 18 June 2016 12:30

ሲኒማና ቲያትር ቤቶች በተመልካች ድርቅ ተመተዋል

Written by 
Rate this item
(17 votes)

“ቃና” 8 ስቱዲዮዎች ገንብቷል

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው “የቃና ቴሌቪዥን” ሥርጭትን ተከትሎ ሲኒማ ቤቶችና ቲያትር ቤቶች በተመልካች ድርቅ መመታታቸውን የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት የፊልምና ቲያትር ተመልካቾች ከግማሽ በላይ መቀነሳቸው ባለሙያዎቹን እንዳስደነገጣቸው ገልፀዋል፡፡
የቲያትር አዘጋጆችና ባለቤቶች እንደተናገሩት፤ በሣምንቱ የእረፍት ቀናት ከሚታዩ ቲያትሮች በስተቀር በስራ ቀናት ምሽት ላይ የሚቀርቡ ቲያትሮች ተመልካች አጥተዋል፡፡
በማዘጋጃ ቤት “እንግዳ” እንዲሁም በብሔራዊ ቲያትር “የፍቅር ማዕበል” የተሰኙ ቲያትሮችን የሚያሳየው አርቲስት ማንያዘዋል እንደሻው፤ ባለፉት ሶስት ወራት የቲያትር ተመልካቾች ከ30 በመቶ በላይ መቀነሳቸውን ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል በማዘጋጀ ቤት እየታየ ያለውን ቲያትር እስከ 300 ሰዎች ይመለከቱት እንደነበረ የጠቆመው አርቲስቱ፤ በአሁን ወቅት የተመልካቹ ቁጥር በመቶ እንደቀነሰ ተናግሯል፡፡ “ቃና” ቴሌቪዥን ከመጣ ወዲህ የተመልካቹ ቁጥሩ መቀነሱ የጣቢያው ተፅዕኖ የፈጠረው ነው ብሎ እንደሚያምን የገለፀው ማንያዘዋል፤ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ቲያትር ቤቶች ባዶአቸውን ሊቀሩ ይችላሉ ብሏል፡፡
ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ ሌላ የቲያትር ባለሙያ በበኩሉ፤ የተመልካች ቁጥሩ መቀነሱ ኢንዱስትሪውን በእጅጉ እየጐዳው በመምጣቱ፣ በቲያትር ስራ የመቀጠል እምብዛም ፍላጐት የለኝም ብሏል፡፡ የቲያትር ባለቤቶችም ለከፍተኛ ኪሣራ እየተዳረጉ እንደሆነ ወዳጆቹ  እንደነገሩት ጠቁሟል፡፡
የ“ታምሩ ሲኒማ ቤት” ባለቤት አርቲስት ታምሩ ብርሃኑም፤ ባለፉት ሶስት ወራት የተመልካች ቁጥር በግማሽ መቀነሱን ይናገራል፡፡ ችግሩ የተፈጠረው “ቃና” ቴሌቪዥን ከመጣ በኋላ በመሆኑ ጣቢያው የፈጠረው ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል አርቲስቱ ግምቱን ተናግሯል፡፡ “እንደ ቢዝነስ ሊጐዳኝ ቢችልም እንደ ሙያተኛ በቃና ደስተኛ ነኝ” ይላል፡፡ የተመልካች ቁጥር በትክክል የቀነሰበትን ምክንያት ለማወቅ ግን ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ነው፤ አርቲስት ታምሩ፡፡
የሴባስቶፖል ሲኒማ ባለቤትና የፊልም ባለሙያው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተመልካች ቁጥር መቀነሱን ባይክድም የ “ቃና” ተፅዕኖ ነው በሚለው ግን አይስማማም፡፡ “ከዚያ ይልቅ በየቦታው በርካታ የግል ሲኒማ ቤቶች መከፈታቸው ተመልካቹ እንዲበታተን አድርጐታል” ብሎ እንደሚያምን ቴዎድሮስ ገልጿል፡፡
የቫይን ሲኒማ ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ገዛኸኝ (ብሩስ) በበኩላቸው፤ የተመልካች ቁጥሩ ከሚገመተው በላይ መቀነሱን ይናገራሉ፡፡ “ለምን ተመልካች አይመጣም?” የሚል መጠነኛ ጥናት ለመስራት መሞከራቸውን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ አብዛኛው ተመልካች የማይመጣው ጥሩ ፊልሞች ስለማይቀርቡ እንደሆነ አረጋግጫለሁ ይላል፡፡ በ “ቃና” ቴሌቪዥን ምክንያት ከሲኒማ ቤት የቀሩም አሉ - ጥቂት ናቸው እንጂ፤ ብለዋል አቶ ብርሃኑ፡፡
የፊልም ዳይሬክተሩ ቢኒያም ወርቁ በሰጠው አስተያየት፤ ለተመልካች ቁጥር መቀነስ ዋነኛው ምክንያት “ቃና” ቴሌቪዥን ነው ብሎ እንደሚያምን የተገለፀ ሲሆን፤ ትክክለኛውን ምክንያት ለማወቅ ግን በማህበራቸው በኩል ጥናት ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል “ቃና” ቴሌቪዥን ተርጉሞ ከሚያቀርባቸው ፊልሞች በተጨማሪ ራሱ ለሚሰራቸው አገር በቀል ፊልሞችና አዳዲስ ፕሮግራሞች 8 ስቱዲዮዎች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን የጣቢያው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃይሉ ተ/ሃይማኖት ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ስርጭት በጀመረ በ3 ወር ጊዜ ውስጥም የጣቢያውን ፌስ ቡክ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች እየተከታተሉት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡    


Read 12364 times