Saturday, 18 June 2016 12:25

7ኛው ዳይመንድ ሊግና የኢትዮጵያ አትሌቶች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

      የ2016 ዳይመንድ ሊግ ከትናንት በስቲያ በ8ኛዋ ከተማ ስዊድን ስቶክሆልም ተካሂዷል። 11 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቶች፤ 59 የዓለም ሻምፒዮኖች እንዲሁም 7 የዓመቱን ፈጣን ሰዓት እና ምርጥ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች ተሳትፈውበታል፡፡ በዳይመንድ  ሊጉ በሁለቱም ፆታዎች ከ4 በላይ የውድድር መደቦችን  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይካፈላሉ፡፡ በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር ፣ በ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች እና በ3000 ሜትር ወንዶች እንዲሁም በ5000 ሜትር  ጠንካራ ተፎካካሪም ናቸው፡፡  
ባለፈው ሐሙስ ስቶክሆልም ላይ  በ800 ሜትር ወንዶች ቤጂንግ አስተናግዳ በነበረው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ1 እስከ 5 የወጡ አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡ በተለይ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ዴቪድ ሩድሻ እና የዓለም ሻምፒዮኑ መሐመድ አማን ከ3 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መገናኘታቸው ትኩረት የሳበ ነበር፡፡
በ5ሺ ሜትር ወንዶች በ3ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የሆነው የሆነው ዮሚፍ ቀጀልቻ፤ በ2011 በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደው ኢብራሂም ጄይላንና በውድድር ዘመኑ በ5ሺ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ሙክታር ኢድሪስ ፈታኝ ውድድር አድርገዋል፡፡  ኢማና መርጋ እና የኔው አላምረውም ከተፎካካሪዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ በሴቶች ደግሞ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሶፍያ አሰፋ፤ በ1500 ዳዊት ስዩም፤ ጉድፍ ፀጋይ እና በሱ ሳዶ ተሳትፈዋል፡፡
የ2016  ዳይመንድ ሊግ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ይገኛል፡፡ በስዊድን ስቶክሆልም ጨምሮ በስምንት ከተሞች  ተካሂዷል፡፡  በኳታሯ ከተማ ዶሃ የተጀመረ ሲሆን ከዚያም በቻይና ሻንጋይ፤ በሞሮኮ ራባት፤ በጣሊያን ሮም፤ በእንግሊዝ በርሚንግሃም እና በኖርዌይ ኦስሎ ከተሞችም ተከናውኗል፡፡ ከ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ በፊት 10 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በ10 ከተሞች ይደረጋል፡፡ ከሪዮ ኦሎምፒክ በፊት ቀጣዮቹ የዳይመንድ ሊግ አዘጋጅ ከተሞች የፈረንሳይ ከተማ ሞናኮ እና የእንግሊዟ ከተማ ለንደን  ናቸው፡፡ ከሪዮ ኦሎምፒክ በኋላ በስዊዘርላንድ ሎዛን፤ በፈረንሳይ ፓሪስ መደበኛዎቹ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በስዊዘርላንድ ዙሪክ እና በቤልጄይም ብራስልስ ከተሞች ሁለቱ የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድሮች ያስተናግዳሉ፡፡
የ2016 ዳይመንድ ሊግ  በሪዮ ኦሎምፒክ ዓመት መካሄዱ ለየት ያደርገዋል፡፡ በኦሎምፒክ በመካከለኛና በረጅም ርቀት የአትሌቲከስ ውድድሮችና የሜዳ ላይ ስፖርቶች የሚያሰልፏቸውን ምርጥ ኦሎምፒያኖች ለመለየት የሚያግዝ  ነው፡፡ ዘንድሮ በተለይ በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች የኢትዮጵያ አትሌቶች በዳይመንድ ሊጉ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም በሪዮ ኦሎምፒክ ለሚኖር የሜዳልያዎች ስኬት ከፍተኛ ተስፋ ሊፈጥር ይችላል፡፡
በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍ የሚዘጋጀው ዳይመንድ ሊግ  ዘንድሮ በ7ኛ የውድድር ዘመኑ ላይ ይገኛል። አስቀድሞ ይካሄድ የነበረውን ጎልደን ሊግን በተሻለ ደረጃ የተካ ዓመታዊ የአትሌቲክስ መድረክ ሆኖ በስኬት የቀጠለው ዳይመንድ ሊግ በየዓመቱ በ32 የውድድር መደቦች (16 የወንድ 16 የሴት) የሚካሄደ ሲሆን በርካታ ምርጥ አትሌቶች የሚሳተፉበትና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበትም ሆኗል፡፡ በ4 አህጉራት ፤  በ11 የተለያዩ አገራትና 15 ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች የብሔራዊ፣ የዓለምና፣ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆኑ ብዛት ያላቸው አትሌቶችን ማሳተፉ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በከፍተኛ የውድድር ደረጃው ሪከርዶች እና የውድድር ዘመኑ ፈጣን ሰዓቶች የሚመዘገቡበት መድረክም ነው፡፡በሻምፒዮንሺፕ ደረጃ ባይሆንም በርካታ ምርጥ አትሌቶችን በከፍተኛ የፉክክር ደረጃ የሚያሳትፍ የአትሌቲክስ ታላቅ መድረክ እየሆነ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን
በ7ኛው ዳይመንድ ሊግ ላይ
ዳይመንድ ሊጉ በ8ኛዋ ከተማ ስቶክሆልም ከቀጠለ በኋላ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች  በሁለት ተከታታይ ውድድሮች ተከታትለው በመግባት ፍፁም የበላይነት በማሳየት ላይ ናቸው፡፡  ከሳምንታት በፊት አትሌት ሐጎስ ገብረህይወት፣ ሙክታር እድሪስ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት ተከታትለው ገብተዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ደግሞ በስዊድን ስቶክሆልም ኢብራሂም ጄይላን፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ እንዲሁም ሙክታር ኢድርስ ሆነው ከ1 እስከ 3 ደረጃ አግኝተዋል። በ5ሺ ሜትር ወንዶች ሙክታር ኢድሪስ በ4 ውድድሮች 30 ነጥብ አስመዝግቦ 1ኛ ሲሆን፤ ሃጎስ ገብረህይወት በ2 ውድድሮች 12 ነጥብ አስመዝግቦ 2ኛ፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ በ3 ውድድሮች 11 ነጥብ አስመዝግቦ 3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ኢብራሂም ጄይላን በስዊድን ስቶክሆልም ካሸነፈ በኋላ በ10  ነጥብ 4ኛደረጃ ሲይዝ ይገረም ደመላሽና አባዲ አምባዬ በእኩል 3 ነጥብ ዘጠነኛ፤ እንዲሁም ደጀን ገብረመስቀል በ1 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች ደግሞ በሞሮኮ ራባት እና በጣሊያን ሮም ያሸነፈችው አልማዝ አያና ለዓለም ሪከርድ እጅግ የቀረበ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የበላይነቷን እያሳየች ነው፡፡ አምና በ6ኛው ዳይመንድ ሊግ በ5ሺ ሜትር ያሸነፈችው ገንዘቤ ዲባባ ስትሆን ዘንድሮ ግን አልማዝ አያናን የሚቀናቀን ያለ አይመስልም። በ3 ውድድሮች በማሸነፍ በ30 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ የኬንያዎቹ ሜርሲ ቼሮኖ በ18 እንዲሁም ቪቪያን ቼሮይት በ13 ነጥብ ይከተላሉ፡፡ ሌሎቹ አትሌቶች ሰንበሬ ተፈሪ በ7 ነጥብ 6ኛ፤ ገለቴ ቡርቃ በ4 ነጥብ 7ኛ፤ ሃፍታምነሽ ተስፋዬ በ3 ነጥብ 9ኛ፤ እቴነሽ ዲሮ እና አባቤል የሱፍ በእኩል 2 ነጥብ 9ኛ እንዲሁም አለሚቱ ሃሮዬ በ1 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሶፊያ አሰፋ በ3 ውድድሮች 12 ነጥብ አስመዝግባ በ3ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ በሴቶች 3ሺ መሰናክል ላይ ሶፊያ አሰፋ በዳይመንድ ሊግ በ35 ውድድሮች በመሳተፍ በዳይመንድ ሊጉ የተሳትፎ ልምድ አራተኛ ደረጃ ያላት ሲሆን፤ በ22 ደውድድሮች ከ1 እስከ 3 ባሉ ደረጃ በመጨረስ ውጤቷ በ10ኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው፡፡ እቴነሽ ዲሮ በበኩሏ በ1 ውድድር 4 ነጥብ አስመዝግባ 4ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ በ800 ሜትር ወንዶች መሃመድ አማን በ4 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲሆን  በ1500 ሜትር ወንዶች አማን ወቴ በ3 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡በ800 ሜትር ሴቶች ሃብታም አለሙ በ3 ውድድሮች 8 ነጥብ አስመዝግባ 5ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፤ በ1500 ሴቶች ዳዊት ስዩምና ጉድፍ ፀጋይ በ2 ውድድሮች 10 ነጥብ በማስመዝገብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲሆኑ በ6 ነጥብ በሱ ሳዶ 8ኛ ነች፡፡
ስለ ዳይመንድ ሊጉ
ባለፉት ስድስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናር ኤስያ፤ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካን ያካለለው ውድድሩ ዘንድሮ ደግሞ  በአፍሪካ መካሄድ ጀምሯል፡፡ በአሜሪካዋ ኒውዮርክ የሚዘጋጀውን ግራንድ ፕሪ በመተካት በአፍሪካ የዳይመንድ ሊግ አዘጋጅ ሆና የተመረጠችው የሞሮኮዋ ከተማ ራባት ስትሆን ውድድሩን በመሀመድ አምስተኛ ስታድዬም በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በቅታለች፡፡ በሌላ በኩል ተግባራዊ የሆነ የዳይመንድ ሊግ አዲስ አሰራር የነጥብ አሰጣጡ ነው፡፡ ባለፉት 6 የውድድር ዘመናት ከ1 እሰከ 3 ለሚወጡ አትሌቶች ብቻ  ነጥብ ይሰጥ በር፡፡ ዘነድሮ ከ1 እሰከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች ነጥቦች ይሰጣሉ፡፡  በዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመን አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከሚያገኙት የገንዘብ ሽልማት እና የዳይመንድ ዋንጫ በተጨማሪ በቀጣይ የውድድር ዘመን በቀጥታ ተሳታፊ በመሆናቸው ከፍተኛውን ነጥብ ለማስመዝገብ ፉክክሩ ከባድ ነው፡፡ በዳይመንድ ሊግ በየውድድር አይነቱ በሚሰጥ ነጥብ መሰረት ዳይመንድ ሬስ ተብሎ ደረጃ ይሰጣል፡፡  በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከፍተኛውን ነጥብ ያስመዘገቡ አትሌቶች በአልማዝ ማእድን የተሰራ ልዩ ዋንጫ እና 40ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ፡፡ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫው ተቀማጭነቱ በዙሪክ የሆነው፤ ከ18ኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በመስራት ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው ቤዬር የተባለ ተቋም ይሰራዋል። በዳይመንድ ሬስ ፉክክር ለመግባት አትሌቶች ውድድሮቹ ከሚደረጉባቸው 14 ከተሞች በ7ቱ የግድ መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡
በዳይመንድ ሊጉ አዲስ የነጥብ አሰጣጥ መሰረት በአንደኝነት የሚያሸንፍ አትሌት በመደበኛ ውድድሮች 10 ነጥብ በፍፃሜ 30 ነጥብ፤ 2ኛ ደረጃ የሚያገኝ በመደበኛ 6 ነጥብ በፍፃሜ 12 ነጥብ ፤ 3ኛ ደረጃ የሚያገኝ አትሌት በመደበኛ 4 ነጥብ በፍፃሜ 8 ነጥብ፤ 4ኛ ደረጃ የሚያገኝ አትሌት በመደበኛ 3 ነጥብ በፍፃሜ 6 ነጥብ፤ 5ኛ ደረጃ የሚያገኝ አትሌት በመደበኛ 2 ነጥብ በፍፃሜ 4 ነጥብ እንዲሁም 6ኛ ደረጃ የሚያገኝ በመደበኛ 1 ነጥብ በፍፃሜ 2 ነጥብ ይሰጣቸዋል፡፡ በዳይመንድ ሊጉ ማጠቃለያ አትሌቶች በየውድድር መደቡ በእኩል ነጥብ የሚጨርሱ ከሆነ ባሸነፉት የውድድር ብዛት፤ ይህም አቻ የሚያደርጋቸው ከሆነ በተሻለ ሰዓት እና ውጤት መሰረት አሸናፊዎቹ የሚለዩ ይሆናል፡፡
በዳይመንድ ሊጉ በእያንዳንዱ ከተማ በሚደረግ ውድድር  እሰከ 8ኛ ደረጃ ላገኙ አትሌቶች የሚበረከተው የሽልማት ገንዘብ ዝርዝር እንደሚከተለው ሲሆን ለ1ኛ 10ሺ ዶላር፤ ለ2ኛ 6ሺ ዶላር፤ ለ3ኛ 4ሺ ዶላር፤ ለ4ኛ 3ሺ ዶላር፤ ለአምስተኛ 2500 ዶላር፤ ለስድስተኛ 2ሺ ዶላር፤ ለ7ኛ 1500 ዶላር እንዲሁም ለ8ኛ 1000 ዶላር ይሆናል፡፡
የምንግዜም ውጤት ደረጃ
ባለፉት 6 የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት 48 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች ያስመዘገበችው አሜሪካ አንደኛ ደረጃ ሲኖራት፤ ኬንያ በ30 ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ጃማይካ በ14 የዳይመንድ ሊግ ድሎች ሶስተኛ ደረጃ ስትይዝ፤ ኢትዮጵያ በ2012 እኤአ ላይ አበባ አረጋዊ በ1500 ሜትር ዜግነቷን ሳትቀይር ያስመዘገበችውን ድል ጨምሮ በ10 የዳይመንድ ሊግ ድሎች አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ 10 የዳይመንድ ሊግ ድሎች በአምስት አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በ800 ሜትር መሃመድ አማን በ2012 እና በ2013 እኤአ አሸንፏል። በ5ሺ ሜትር ወንዶች ካላፉት አምስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመኖች አራቱን ሁለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል፡፡ በ2010 እና 2011 እኤአ ኢማና መርጋ እንዲሁም በ2013 እኤአ የኔው አላምረው ናቸው፡፡ አበባ አረጋዊ ዜግነቷን ሳትለውጥ በፊት በ1500 ሜትር በ2012 እኤአ ላይ አሸናፊ ነበረች፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትር መሰረት ደፋር በ2013 እኤአ ያሸነፈች ሲሆን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞ 2014 እኤአ ላይ ህይወት አያሌው ድል አድርጋለች፡፡ በ2015 ደግሞ ዳይመንድ ሊጉን በ5ሺ ሜትር ለማሸነፍ የበቃችው ገንዘቤ ዲባባ ነበረች፡፡
ባለፉት ስድስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖችን የሚከተሉት ናቸው፡፡
በ3ሺ ሜትር የኔው አላምረው በኳታር ዶሃ በ2011 እኤአ ላይ በ7፡27.26
በ5ሺ ሜትር ደጀን ገብረመስቀል በፈረንሳይ ፓሪስ በ2012 እኤአ 12፡46.81
በሴቶች 1500 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ በፈረንሳይ ሞናኮ በ2015 እኤአ ላይ 3፡50.07
በሴቶች 5ሺ ሜትር አልማዝ አያና በሮም ጣሊያን 14፡12.59

Read 2724 times