Saturday, 11 June 2016 13:56

ከእሾህ አጥር የሰው አጥር ይጠነክራል

Written by 
Rate this item
(28 votes)

ሦስት አህዮች በጠፍ ጨረቃ ሣር ሊግጡ ወደ ሜዳ ተሰማርተዋል፡፡ ጅቦች ደግሞ ርቧቸው ሲዞሩ አምሽተው፣ በመጨረሻ አህዮቹ ሣር ወደሚግጡበት አካባቢ ይመጣሉ፡፡
“በዚህ ሌሊት፣ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት እንዲህ ፍንድቅድቅ ያሉት ማንን ተማምነው ነው? ከመብላታችን በፊት እንጠይቃቸው” አሉና ጅቦቹ አህዮቹን ተራ በተራ ለፍርድ እንዲቀርቡ አደረጉ፡፡
የጅብ መሀል ዳኛ የመጀመሪያዋን አህያ አስቀርቦ፤
“ወ/ሮ አህያ፣ በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት መጥተሽ ሣር የምትግጪው ማንን ተማምነሽ ነው?” ሲል ጠየቃት፡፡
ወ/ሮ አህያም፤
“አምላኬን ተማምኜ ነው፡፡ ማንም ጥቃት ቢያደርስብኝ አምላክ ይበቀልልኛል ብዬ ነው” ስትል መለሰች፡፡
ሁለተኛዋን አህያ አስጠሩና ዳኛው ጅብ፤
“አንቺስ በጠፍ ጨረቃ በእኛ ግዛት ሣር የምትግጪው ማንን ተማምነሽ ነው” ሲሉ ጠየቋት።
ሁለተኛዋ ተከሳሽ አህያም፤
“እኔ ጌታዬን ተማምኜ ነው የወጣሁት፡፡ ማንም ጥቃት ቢያደርስብኝ፤ ጌታዬ ተከታትሎ ይበቀልልኛል” አለች፡፡
ሦስተኛዋ ተከሳሽ አህያ ቀረበች፡፡
“ማንን ተማምነሽ ነው በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት ሣር የምትግጪው?” ሲሉ ጠየቋት፡፡
አህይትም፤ “እናንተን ተማምኜ፣ እናንተን አምኜ ነው ከቤቴ የወጣሁት” ስትል መለሰች፡፡
ሶስቱ ጅቦች ዳኞች,ኧ ሶስቱን ተከሳሽ አህዮች ወደ ጥግ እንዲቆሙ አድርገው ይመካከሩ ጀመር፡፡
“የመጀመሪያዋን አህያ ብንበላት፤ እንዳለችው አምላክ ሊበቀለን ይችላል፡፡ ለእኛ ለይቶ ባይልከውም ነጐድጓድ ሊያወርድብን፣ መብረቅ ሊልክብን፣ ድርቅ ሊያመጣብን ይችላል”
“ሁለተኛዋን ብንበላትስ?” አለ ግራ ዳኛው ጅብ፡፡
“የእሷም ጌታዋ ሊበቀለን ይችላል፡፡ አሁንም ፍለጋ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እሷንም ብንተዋት ይሻላል፡፡ ይልቅ እቺን እኛን የተማመነችውን ብንበላት ማናባቱ ይጠይቀናል?” አሉና ሁለቱን አሰናብተው ሶስተኛዋ ላይ ወረዱባት፡፡
*   *   *
በርትቶ ራስን ማዳን ነው እንጂ “እናንተን ተማምኜ” ማለት አብዛኛውን ጊዜ አያዋጣ። ምንጊዜም በራስ መተማመንን የመሰለ ነገር የለም፡፡ በራስ ለመተማመን የራስን ብቃት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የራስን ብቃት ለማረጋገጥ ራስን በመሠረታዊ ዕውቀት መገንባት፣ ሁሌ መትጋት፣ ሁሌ መማር ያሻል፡፡ ትምህርት ከመሠረቱ ካልተስተካከለ የተጣመመ ግንድ ለማቃናት እንደመሞከር ይሆናል፡፡ ዛሬ ትምህርት በእጅጉ ቁልቁል እየወረደ ነው፡፡ ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን፤ “ቁልቁል ማደግ” እንደሚለው ነው፡፡
“በጠቅል ጊዜ ያልተማረ
ማዘኑ አይቀርም እያደረ
ዐይናችን ታሞ ታውረን
ኃይለሥላሴ አዳኑን”
ለማለት እንኳ አቅም የለም፡፡ ለመማር አቅም የሌላት አገር የበለፀገ ትውልድ ለማፍራት አትችልም፡፡ የተልፈሰፈሰና የተቆለመመ ህብረተሰብ ነው የምትፈጥረው፡፡ እንዲያ ያለ ህብረተሰብ ደግሞ ነገው የተጭለመለመ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ “መማር፣ መማር፣ መማር” የሚለው የዱሮ መፈክር፤ የሸረሪት ድርም አድርቶበት ከሆነ ተጠራርጐ ጐላ ብሎ ቢታይ በጐ ነው፡፡
ቻይናዎች፤
“ዕቅድህ ለዓመት ከሆነ ሩዝ ዝራ፡፡
ዕቅድህ ለአምስት ዓመት ከሆነ ባህር ዛፍ ትከል፡፡
ዕቅድህ ለዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር” ይላሉ፡፡
(“If your plan is for a year, plant rice;
If your plan is for five years, plant a eucalyptus tree;
If your plan is for ever educate your child.)  
ይህንን አስተምህሮ ሶስት ወገኖች በቅጡ ሊጨብጡት ይገባል፡- አንደኛ ወላጆች፡፡ ሁለተኛ መምህራን፡፡ ሶስተኛ መንግሥት፡፡ ይህ የሶስትዮሽ ትሥሥር (Network) ብቻ ነው የኋሊት እየተንደረደርን ካለንበት አዝቅት ታኮ ሆኖ ሊያቆመን የሚችለው፡፡ ኩረጃን እንደ ባህል እንዳንይዝ በግሮ የሚከላከልልን ይኼው የሶስትዮሽ አጥር ነው፡፡ ታሪካዊ ምፀቱ ቢያስገርምም እዚህ ተጠቃሽ ቢሆን አግባብ ነው የምንለው ነገር አለ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር “ከሌሎች አገሮች የዕድገት አካሄድ ቢያንስ በአግባቡ መኮረጅ እንቻል”፡፡ ያን ያሉት ለትምህርት ቤት ፈተና ኩረጃ አልነበረም! ያ የበለጠ ለመሥራት፣ የበለጠ ለመትጋት፣ የበለጠ ለመነሳሳት ነበረ። አሁን የሚታየው ግን ሥንፈተ - ትምህርት ነው! ይህ አደጋ ነው፡፡ ትልቅ ሥጋት፣ ትልቅ ጥንቃቄ፣ ትልቅ ቆራጥነት ይጠይቃል፡፡ በገጣሚ መንግሥቱ አገላለጽ፣ “መርፌ ትሠራለህ?” ከሚል ማህበረሰብ ተነስተን “መኮረጅ ትችላለህ?” ወደሚል ትውልድ ማቆልቆላችን አሳዛኝ ነው፡፡ ከቶማስ ኤዲሰን 128 የውድቀት ልምድ ባንማር፣ እንደቅዱስ ያሬድ ስምንቴ ከወደቀችው ትል መማር አቅቶናል፡፡
ጥንካሬያችን በሰው ኃይል ጥራት የተገነባ ይሆን ዘንድ የትምህርትን መሠረታዊ ጉዘት እናጢን፡፡ የመምህራኖቻችንን ሙያዊ ብቃትና ስብዕና እንፈትሽ፡፡ የመንግስትን፤ የትምህርት ላይ ትኩረት፤ ከልብ እንመርምር! “ከእሾህ አጥር የሰው አጥር ይጠነክራል” የሚለው ተረት በቅጡ የሚባን ያኔ ነው!!



Read 6711 times