Saturday, 03 March 2012 14:46

መከልከል መፍቀድ ነው!

Written by  ሶፎንያስ አቢስ
Rate this item
(0 votes)

ሀገራችን የመከልከል አዚም የተጠናወታት ሀገር ነች፡ ኑሮአችን ወይም ህይወታችን በክልከላ የተሞላ ነው፡፡ ፓርላማችን እራሱ የህዝብ እና የሀገር ጥቅም ለማስጠበቅ ሳይሆን የክልከላ ናዳ እንደ ህግ ለማዝነብ የተቋቋመ ነው፡፡ ወይም ይመስላል፡፡ ወይም…

ልጆቻችን የሚያድጉት በክልከላ ታጥረው ነው፡፡ ወይም ቢያንስ እኛ የትላንቶቹ ልጆች ያደግነው በክልከላ ታጥረን ነው፡፡ ወላጆቻችን ከማሳየት ይልቅ መከልከል ይቀናቸዋል፡፡

የክልከላው ህግ ብዙ ነው፡፡

አንድ - ልጅ ከአዋቂ ጋር አይበላም…

ሁለት - ልጅ ከአዋቂ ጋር አያወራም…

ሶስት - ድስትና ልጅ ወደ ጓዳ…

አራት - ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም…

ያደግነው ስንከለከል ነው፡፡ አትንካው፣ አትያዘው፣ ልቀቀው፣ ዞር በል፣ ወዘተ…

የክልከላ ልጆች ነን፡፡ መሪዎቻችንም የክልከላ ልጆች ስለሆኑ ነው፣ የከልካይ ህጐች አባቶች የሆኑት፡፡ አዙሪት ነው፡፡ ክልከላ እንደጦስ ዶሮ አናታችን ላይ አዙረን ካልጣልነው የሚለቀን አይደለም፡፡ ወይም አይመስልም፡፡ ወይም…

ከተፈቀደልን ውጪ የሆነ ነገር ለማድረግ ስንሞክር ሙከራችን የግድያ ሙከራ ተደርጐ ይቆጠርብናል፡፡ ይቆጠርብንና ቅጣትና ማዕቀብ ያስጥልብናል፡፡

ጉያችን መሀል እጅ ይገባና በጣቶች መሀል ስጋችን ይያዝና “የሚጣፍጥ” ቁንጥጫ እየቀመስን መመሪያ እንቀበላለን፡፡

“ሁለተኛ ይለመድሀል?”

“አይለመደኝም”

“ሁለተኛ እንደዚህ ታደርግና ወየውልህ…”

“ግን ቆይ ለምን?”

“ክልክል ነው!”

“ለምን?!”

“በቃ! ክልክል ነው!!”

“በቃ” ማሰሪያ ናት፡፡ በቃ ከተባለ በቃ ነው፡፡ በቃ፤ አራት ነጥብ፡፡ ማድረግ የሌለብን ብቻ ሲነገረን ነው ከህፃንነት ወደ ወጣትነት የተሻገርነው፡፡ ማድረግ ያለብን ነገር የሚነገረን ጊዜ ካለ ጥቂት ነው፡፡ በልማቱ ሳይሆን በጥፋቱ፣ በነፃነቱ ሳይሆን በገደቡ፣ በመልካሙ ባህሪ ሳይሆን በመጥፎው ባህሪያችን ላይ አተኩረው ነው ያሳደጉን፡፡

ነገር ግን ተፈጥሮአችን የተገላቢጦሽ ነው፡፡

የተገለጠውን ነገር ከማስተዋል ይልቅ የተሸፈነውን ነገር ለማየት የሚተጉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ በተፈጥሯችን ከግልፁ ይልቅ ሽፍኑ ያጓጓናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ እርቃኗን የምትቆም ሴት ውበት ውበትነቱ ብዙም አይታይም፡፡ የውበት ውበትነቱ ማጓጓቱ ነው፡፡ የውበት ውበትነቱ ዓይን አፋርነቱ ላይ ነው፡፡ ወጣትዋ ሙሉ እርቃን ከመሆንዋ ይልቅ ዋናዎቹን የአካልዋን ክፍሎች ሸፍና በስሱ ብትገልጣቸውና ከፊል እርቃን ብትሆን ግን ምራቄን መዋጤና መጉዋጉዋቴ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሰው ነኝ፡፡ ከሰውም ወንድ!

ድብቅ ነገር ያጓጓል፡፡ ሰው ስለሆንን የተፈቀደውን ከማድረግ ይልቅ የተከለከለውን ለማድረግ እንፈጥናለን፡፡

ይህን ከላይ የፃፍኩትን ያሰብኩት ከወዳጄ ናኦድ ጋር ካወራሁ በኋላ እንደሆነ መናዘዝ አለብኝ፡፡ ናኦድ ብስል ወጣት ነው፡፡ መጻሕፍት ላይ ተጥዶ እና ራሱን ያበሰለ ሰው ነው፡፡

አንድ ቀን ሻይ እየጠጣን ስንጨዋወት:-

“መከልከል መፍቀድ ነው!” አለኝ፡፡ ጨዋታችን ስለ ክልከላ መብዛት ነበር፡፡ አባባሉ ገረመኝና

“እንዴት?” አልኩ፡፡

“አንድን ሰው የሆነ ነገር እንዳያደርግ መከልከል እንዲያደርገው መገፋፋት ነው”

“እንዴት”

“አንደኛ ስለዛ ነገር ያላሰበውን ነገር እንዲያስብ ታደርጋለህ፤ ለምሳሌ ያን ነገር እስከነመፈጠሩ ረስቶት ሊሆን ይችላል፡፡ ስትከለክለው መኖሩን ታስታውሰዋለህ፡፡ ነገርዬው መኖሩን አስታወሰ፡፡ ይቀጥልና መከልከሉን ያስባል፡ መከልከሉ ለምን ተከለከልኩ የሚል ጥያቄ ይፈጥርበታል፡ ጥያቄው በማድረግ ውስጥ የሚገኝ አንዳች ስውር እርካታ እንዳለ ይነግረዋል፡፡ ነገሩ የሚያረካ መሆኑን ማሰቡ እንዳለ ሆኖ፣ ሰዎች አለማወቃቸውና አለማድረጋቸው ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ እርካታ ይሰጠዋል፡፡ ጀብደኝነትም ይሰማዋል፡፡ ይኼ ጀብዱ የመስራት ጥማት ነው ሰውን ወደተከለከለው የሚስበው ሌላው ነገር፡፡

እንደምሳሌ አዳምንና ሄዋንን አቀረበ፡፡ “የተፈቀዱላቸው ብዙ ዛፎች ነበሩ፤ እነሱ ግን የተፈቀዱላቸውን ዛፎች ሁሉ አላዳረሱም፤ ከተፈቀደላቸው በርካታ ይልቅ የተከለከሉት አንድ አጓጓቸው፡፡

ምናልባትም “ይህን እንዳትነኩ” ባይባሉ ኖሮ ትዝም ላይላቸው ይችል ነበር፡፡ ያቺን ዛፍ ፍሬም ላይቀምሱ ይችሉ ነበር፡፡ መከልከላቸው ግን ከየትኛውም ዛፍ ይልቅ ይቺ ዛፍ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አደረጋቸው፡፡ ሰው የሆነ ነገር ተጠቁሞ እንዳያደርግ ሲታዘዝ የማይችለው አንድ ነገር ቢኖር ያንን ትዕዛዝ መፈፀም ነው፡፡ መከልከሉ በራሱ ወደ ማድረግ የሚመራ ነው፡፡ ለዚህ ነው የመከልከል ውስጠ ወይራ ትርጉሙ መፍቀድ ነው የምልህ፡፡ እውነቴን ነው፤ መከልከል መፍቀድ ነው፡፡”

ሲጨርስ በመደነቅ አየሁት፡፡ እያየሁት የበዕውቀቱ ግጥም ትውስ አለኝ፡፡ ከናኦድ ሀሳብ ጋር አንድ ባይሆንም በክልከላ የመማረር ስሜት አለው፡፡

 

ክልክል ነው

ማጨስ ክልክል ነው!

ማፍዋጨት ክልክል ነው!

መሽናት ክልክል ነው!

ግድግዳው በሙሉ ተሰርቶ በክልክል

የቱ ነው ትክክል?

ትንሽ ግድግዳና ትንሽ ሃይል ባደለኝ

“መከልከል ክልክል ነው”፤ የሚል ትዕዛዝ አለኝ፡፡

ግጥሙን በቃሌ ወጣሁለት፡፡ ናኦድ ፈገግ አለ፡፡ “የሚያዝናና ግጥም ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር መታወቅ አለበት፡፡”

“ምን?”

“ሀሳቤ ሁሉም ነገር መልካም ነው የሚል አይደለም፡፡ የሚጠቅሙ ነገሮች አሉ፡፡ የማይጠቅሙ ነገሮች አሉ፡፡ የሚጐዱ ነገሮችም አሉ፡፡ መልካሙን ከማሳየት ይልቅ መጥፎ የሚባለውን ወይም መልካም ያልሆነውን መከልከል ላይ ማዘንበል ችግር ነው፡፡ የጨለማን መጥፎነትና ክፋት ከማላዘን ይልቅ የብርሀንን መልካምነት መስበክ መልካም ነው፡፡ ብርሀኑ ሲነግስ ጨለማው ይረሳል፡፡ ብርሃኑ ሲያሸንፍ ጨለማው ይረታል፡፡”

“የሚገርም ነው!” ብዬ አዳነቅኩ፡፡

“ምኑ?” አለኝ

“አስተሳሰብህ!”

“የሚገርመው አስተሳሰቤ ሳይሆን አኗኗሯችን ነው፡፡”

“እንዴት?” አልኩት፡፡

“በጐ ከሆነው ይልቅ በጐ ያልሆነው ላይ የሚያነጣጥር ዓይን ነው ያለን፡፡ ከደማቁ ፈዛዛው ጐልቶ ይታየናል፡፡ ከጠንካራው ጥንካሬ የደካማው ድክመት ጠልቆ ይሰማናል፡፡ ቀና ያለውን ቀና ብለሃል ከማለት ይልቅ ትንሽ አጐንብሰሃል ማለት ይቀለናል፡፡

የተፈቀደውን ሰፊ ጐዳና ችላ ብለን የተከለከለውን ጥቂት መንገድ ክላከላውን በማጥበቅ ብዙ እናደርገዋለን፡፡ ክልከላ ከየአቅጣጫው እንደ አሸን ይፈላል፡፡ መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ይከለክላል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለየ ሀሳብ ያለው ሰው ሀሳቡን እንዳይገልፅ ይከለክላሉ፡፡ ልዩነት በአግባቡ ከማስተናገድ፣ የተለየ ሀሳብ ያለውን ማገድ ይስተዋላል፡፡ ሁሉ ነገር ክልክል ነው፡፡ … እና የሚገርመው አኗኗራችን ነው፡፡”

ዝም አልኩ፡፡ ያለውን እያብሰለሰልኩ ዝም አልኩ፡፡

 

 

Read 2659 times Last modified on Saturday, 03 March 2012 14:49