Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 03 March 2012 14:37

ጫማ ምንም ክብር ቢኖረው ሁልጊዜ እግር ሥር ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ የታወቀ የሆሊውድ የፊልም ስክሪፕት (ፅሁፍ) ነጋዴ ለአንድ ዝነኛ የፊልም ፕሮዲዩሰር ፅሁፍ ሊሸጥለት ይፈልጋል፡፡ ፅሁፉን ከደራሲው ተቀብሏል፡፡

ደራሲው - “ፕሮዲዩሰሩን አገኘኸው ወይ?” ሲል ነጋዴውን ይጠይቀዋል፡፡

ነጋዴው - “አዎ አግኝቼው ነበር”

ደራሲው - “እሺ፤ ምን አለ?”

ነጋዴው - “አይ ስለድርሰቱ እንኳን አላነሳሁበትም”

ደራሲው - “እንዴ! ዋናው የሄድክበት ዓላማ ድርሰቱን ልትሸጥለት ነው፡፡ አግኝተኸው ስታበቃ ምን አንከረፈፈህ?”

ነጋዴው - “አልተንከረፈፍኩም እስከሚቀጥለው ቅዳሜና እሁድ ጠብቄ ወደ ሳውና (የእንፋሎት መታጠቢያው) እሄዳለሁ”

ደራሲው - “መታጠቢያው እና ድርሰቱ ምን ያገናኘዋል”

ነጋዴው - “ፕሮዲዩሰሩ ወደመታጠቢያው የሚሄደው በሳምንቱ መጨረሻ ነው”

ደራሲው - “እሺ፤ ወደ መታጠቢያው ስለሄደ ምን ይፈጠራል?”

ነጋዴው - “እዚያ ሄጄ መታጠቢያው ዘንድ አገኘዋለሁ”

ደራሲው - “እኮ ምን ጥቅም አለው?”

ነጋዴው - “ያኔ ነው ዋናው ገበያ ያለው”

ደራሲው - “እንዴት?”

ነጋዴው - “አየህ፤ ፕሮዲዩሰሩ የዋዛ ሰው አይደለም፡፡ እንዳንተ ድርሰት አይነት በቀላሉ የሚገዛው አይደለም፡፡ እሺ ብሎ እንዲገዛ እንደዛ ያለ ቦታ ሄደህ ማግኘት ይኖርብሃል”

ደራሲው - “ሌላ ቦታ እምቢ ያለውን ድርሰት መታጠቢያ ሳውና ውስጥ ምን እሺ እንዲል ያደርገዋል”

ነጋዴው - “ቁልፉ ነገር ያ ነው፡፡ ሰውዬው በየጊዜው ሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሳውና ይገባል፡፡ አሁን እድሜው ሰማኒያ ነው፡፡ አንድ አመል አለበት፡፡ ራቁቱን ሆኖ ሰው ሲያየው በጭራሽ አይወድም፡፡ ስለዚህ እኔ በቀጥታ ወደሱ እሄዳለሁ፡፡ ሄጄ ስለድርሰትህ አነሳበታለሁ፡፡ ራቁቱን ስላገኘሁት ያፍራል፡፡ ስለዚህ ያለው ምርጫ “እሺ” ብሎ ቶሎ ከእኔ መገላገል ነው፡፡

ደራሲው - “እምቢ ቢልህስ ያው መገላገሉ አይደለም እንዴ?”

ነጋዴው - “ዋናው ጥበብኮ ያ ነው፡፡ እምቢ ካለማ ልከራከረው ነው”

ደራሲው - “እስቲ ሞክር እንግዲህ”

ተለያዩ፡፡ በሳምንቱ ነጋዴው ለደራሲው “እንኳን ደስ አለህ፡፡ ድርሰትህ ተቀባይነት አግኝቷል!” ብሎ ደወለለት፡፡

***

እያንዳንዱ ሰው የየራሱ ድክመት አለው፡፡ ድክመቱን ባወቅንበት ቁጥር የምናሸንፍበትን ዘዴ ቁልፉን አገኘነው ማለት ነው፡፡ መቼም ቢሆን መቼ፤ እርቃናችን የሚያሳፍረን ነውር ካለብን ነው፡፡ ነውራችን ፖለቲካዊም፣ ማህበራዊም እንከን ሆኖ ሰው ፊት እንዳንቆም እንዳያደርገን ጉዟችንን ሁሉ ንፁህ ዱካ ያለው እናድርገው፡፡ እብሪታችንን እናስወግድ፡፡ ለሌሎች ያለንን ንቀት አሽቀንጥረን እንጣል፡፡ የእኛን ጥፋት ሌሎች ላይ አንላክክ፡፡ ትምህርታችንን ይግለጥልን እንበል እንጂ የተማረውን አናንቋሽ!!

እርቃናችንን አይደለንም፡፡ ታሪክ አለን፡፡ ቅርስ አለን፡፡ ፊደል አለን፡፡ ባህል አለን፡፡ መቼም ይሁን መቼም፣ ማንም አይፈልገው ማንም፤ ማንነታችን በጉልህ መሰረት ላይ የተፃፈ፣ የተደነገገ ነው፡፡ ዘመን በተቆጠረ፣ ትውልድ በተሸጋገረ ቁጥር፤ ማንነታችን ይጠነክራል እንጂ እንደሚታሰበው መንምኖ፣ ተንኖ አይጠፋም! ይልቁንም ህይወት በተራመደ ቁጥር እኛነታችንን ከትላንት ሽበት ውስጥ ለቅመን፣ አጥርተን ማውጣት አለብን! አድዋን ስናስታውስ የሚሰማን ያ ነው! የማንነታችን መገለጫ፣ የአፍሪካዊ አሻራችን መጐልበቻ ነው፡፡ “ተስፋ ርቀቱ ምን ያህል ነው?” ቢለው፤ የእድሜህን ያህል ርቀት ነው፡፡ “ወርዱስ ምን ያህል ነው?” ቢለው የአስተሳሰብህን ወርድ ያህል ነው” አለው አሉ፡፡ የእኛም ነገር ይሄው ነው፡፡ እድሜያችንና አስተሳሰባችን የድርጊታችን መለኪያ ነው፡፡

ታሪካችን እርቃኑን ቢቆም እንኳ አያሳፍርም፡፡ የሌለብንን እንከን በራሳችን ውስጥ እየፈለግን በመብሰክሰክ የትላንትን ታሪክ በማናናቅ፣ ዛሬ የተሻልን ነን ለማለት ባንቃጣ መልካም ነው፡፡ ሀገራዊ ቀናዒነትም ሆነ አህጉራዊ ቀናዒነት ሊኖረን ይገባል፡፡ በእርግጥ የውጪውን ዓለም በአግባቡ ጣዕሙን ካልለየን የቅኝ ገዢዎች ፍልስፍና ነገረ-ሥራው አይገባንም፡፡ ማንነታችንን የመዳጥ ተልእኳቸው አይነበብልንም፡፡ የቅኝ-አገዛዝም፣ ሆነ የእጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ መላውን ለመረዳት፤ ጅላጅል ቢመስልም፣ ማንነትን መረዳት ዋና ነገር ነው፡፡ ትላንት በፀረ-ነገሥታት፣ ከፀረ-ፊውዶ-ቡርዧ አቋም ታግለን የነበርን የጥፋተኝነት ስሜት የማይሰማን፤ ያም የማንነታችን አካል በመሆኑ ነው፡፡

ጉዟችን “የቋመጡትን ሲያጡ፣ የጠሉትን ይቀላውጡ” መሆን የለበትም፡፡ ትላንት አገራችንን ለመውረር ላይ ታች ያሉትም ሃያላን፤ ዛሬ በግሎባላይዜሽንም፣ በዓለም ባንክም፣ በዓለም ገበያም ሊጠፍሩን የሚያስቡት ሃያላንም ያው ናቸው! አድዋን ስናስብ በአድዋ ድል የመታናቸውን አንረሳቸውም! ዞሮ ዞሮ የሀገራችንን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካም ሆነ ባህል ኮድኩደው ለማሰር የማይተኙት፤ እነዚያው የትላንት ባላንጦቻችን ናቸው፡፡ በሀገራዊም፣ በአህጉራዊም መንፈስ ከአዕምሮአችን አይወጡም፡፡

እኛም እነሱም መርሳት የሌለባቸው አንድ ተረት፤ በመሪም በህዝብም ደረጃ ልብ የሚባል አንድዬ ተረት፤

“ጫማ ምንም ክብር ቢኖረው ሁልጊዜ እግር ሥር ነው!” የሚለው ነው፡፡

አድዋም የሚያስታውሰን ይሄንን ነው፡፡

 

 

Read 4532 times Last modified on Saturday, 03 March 2012 14:43

Latest from