Saturday, 11 June 2016 12:38

“…ከጅብ የምታስጥል ሁን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(14 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
‘ሚስት ተብዬ’ የተባለችው ለአቶ ባል የሰጠችው ምላሽ ነው ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡
ለሚመለከተው ሁሉ፡፡
(ለነገሩ በማይመለከታችሁ ነው የገባችሁት፡፡ ግን ይሁን…ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ የራሱን ጉዳይ ትቶ የሰው ጉዳይ ውስጥ ጥልቅ ማለት ለምዶበታል፡፡)
የባልሽ አቤቱታ ብላችሁ የሰጣችሁኝን አነበብኩት። ባል ነኝ በሚለው ሰው አላዝንም። እናንተ ግን ይህን ቁም ነገር ብላችሁ ለእኔ በማሳየታችሁ አፈርኩባችሁ። ሆኖም ካነበብኩት አይቀር እኔም የበኩሌን እላለሁ፡፡
በራሱ አንደበት ደጅ ጠኝቼ፣ ተለማምኜ ነው ያገባኋት ብሎ የለ… እቅጩን አይናገርም እንዴ! የምን ማለባበስ ነው፡፡ እምቢ ብዬው ከጭንቅላቱ የቡሎን መአት ወልቆበት ‘ራሴን አጠፋለሁ’ ብሎ ጠበል ለጠበል ሲያዞሩት ከርሞ አይደል እንዴ የዳነው! ይህንን ለምን ደበቀ! ድሮም ወንዶች የሚፈልጉትን እስኪያገኙ መሬት ይስማሉ፡ ካገኙ በኋላ ደግሞ ይታበዩና ሰማይን ካልነካን ይላሉ፡፡ የእኔው ባል ለዚህ ምስክር ነዋ!
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
“አሁን አንተም እንደ ወንዶቹ ባል ነኝ ትል ይሆናል…” አለችኝ ላለው አዎ እንክት አድርጌ ብየዋለሁ፡ እንደውም ያልኩት ለጽሁፍ አይመችም ብዬ ነው እንጂ ከሚንጠለጠል ነገር ጋር አያይዤ ነው የተናገርኩት። እንደውም ትቼው ልሄድ አስቤ ልጆቼን ብዬ ነው የከረመኩት፡፡ እሱ ራሱ ከርቀት እያየ አይደል እንዴ ሰውዬው መቀመጫዬን ቸብ ያደረገው! ታዲያ እንዲህ ሲሆን ከጅብ አያስጥልም የሚባለው አህያ እንኳን ደሙ አይፈላም! የእኔ ባል እንኳን ደሙ ሊፈላ “ተዪው ባለጊዜ ስለሆነ ነው…” አለኛ፡፡ ባለጊዜ የሚኮነው የእኔን መቀመጫ ቸብ በማድረግ ነው እንዴ! ለምንድነው ይሄንን ያልተናገረው! እንደውም ከዛ በኋላ ሰውየውን መንገድ ላይ ሲያገኘው በሁለት እጁ አጎንብሶ አይደል እንዴ የሚጨብጠው! አሁን ይሄን “ባል ነኝ ትል ይሆናል…”  ብለው ምን ይገርማል!  
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
ደግሞ ትንሽ አያፍርም፣ ቀማምሼ ስመጣ ይላል! እኔ እሱ እየመጣ መሆኑን የማውቀው ገና አምስት መቶ ሜትር ሲቀረው ነው፡፡ እኔ ምኑን ከምን እንደሚቀላቅለው የሰማዩ ጌታ ይወቀው እንጂ ሽታው ለሦስት ቀን ከቤታችን አይጠፋም። በዚህ ላይ የቤቱ ብርጭቆና ሳህን ያለቀው እሱ ከግድግዳ ግድግዳ ሲላጋ ነው፡፡ ደግሞ ሞራሌን ትነካዋለች ይላል! መጀመሪያ ነገር ሞራል የሚባለው ነገር አይደለም አሁን፣ ያገባሁት ጊዜም አልነበረውም፡፡ ሞራል ያለው ሰው “ካላገባሽኝ ራሴን አጠፋለሁ!” ይላል! እኔ የሌለውን ነገር ምን አድርጌ ነው የምነካበት!
ሲኖትራክ ገብቷል ትላቸዋለች ላለው…እኔ ልጆቹ እንዳይሳቀቁ ብዬ ነው እንጂ ሌላም ባልኩት። እሱ ጠጥቶ ሲመጣ ቤታችንን ብታዩት፣ አፍራሽ ግብረ ሀይል ከውስጥ በኩል ማፍረስ የጀመረ ነው የሚመስለው፡፡ እኔ እንደውም ሲኖትራከ ብቻ ሳይሆን ‘በአፈር የተሠራ’ የሚመስል ብሎኬት የጫነ ሲኖትራክ ነው የሚመስለኝ።
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
ደግሞ አርባ ሁለት ኢንች ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን ካልገዛን ትላለች የሚለው…ብልስ! እኛ ቤት ያለው ቴሌቪዥን እኮ ከርቀት ሲያዩት የትሬንታ ኳትሮ ሞተር ነው የሚመስለው፡፡ በዚህ ላይ ሰዉን ስናይ፤ የቱ ነጭ፣ የቱ ጥቁር፣ የቱ ቻይና እንደሆነ እንኳን መለየት አቅቶናል፡፡ በዛ ሰሞን የእሱ ዘመዶች አይደሉም እንዴ ሲበሉ ሲጠጡ ውለው ሊሄዱ ሲሉ… “ይህ ቴሌቪዥን እኮ ራሱን ችሎ የአራት ፎቅ ህንጻ መሰረት ሊሆን ይችላል…” ብለው የተዘባበቱብን!
ከሰፈራችን የሴት እድር ፍላት ስክሪን የሌለኝ እኔ ብቻ ነኝ፣ እንደውም የእድሩ ጸሀፊ አንዳንዴ ስሜ ሲጠፋት… “ያቺ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን የሌላት… ትለኛለች አሉ፡፡
የሶፋው ነገርማ ተዉት፡፡ አንድ አጎቴ… “ቤታችሁን እንደ መጋዘንነት ታከራዩታላችሁ እንዴ!” ብሎ ያሾፈብን ሶፋችንን አይቶ አይደለም እንዴ! እንደውም አቅም የለኝም ካልክ የሳጠራ ወንበሮች እናስገባ ያልኩትን ለምን አልተናገረም!
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
“ይሄን ሁሉ ዓመት በሁለት ዲጂት ስናድግ ምንም ቤሳ ቤስቲኒ አልደረሰኝም ልትለኝ ነው!” አለችኝ ያለው፣ እዛ አምቡላውን ሲግፍ ያወራውን ፖለቲካ ነው እንጂ ከእኔ አፍ እንዲህ አይነት ነገር አልወጣም፡፡ እኔ እንደውም “ይሄንን ፖለቲካህን ቤቴ አታምጣብኝ” ስለው በእኔ እያስመሰለ ሲፎክር ያመሻል፡፡ ቢቸግረኝ “ጎበዝ ከሆንክ ለምን አደባባይ ወጥተህ አትናገርም…” ስለው፤ “ቂሊንጦ ብወርድ በሦስተኛው ቀን ባሌ አይደለም ብለሽ ትክጂኛለሽ…” ይለኛል፡፡ በእርግጥ ልክድው አልችልም አይባልም፡፡ በእኔ አልተጀመረ!
በቀደም ሴቶች እድር ላይ ቲማቲም አሥራ ዘጠኝ ብር ገባ ሲሉኝ…አፌ አላርፍ ብሎ “ገና ቲማቲም በራሽን በሳምንት ሁለት፣ ሁለት ራስ ሳይሰጡን አይቀሩም” አልኩ፡፡ ይሄን ጊዜ አንዷ “ዘላለማችሁን ከማማረር ሄዳችሁ የጓሮ አትክልት አትኮተኩቱም። መንግሥትን ምን አድርግ ነው የምትሉት!” ብላን… በተከታዩ ስብሰባ ከሠላሳ ሰባት ሰው የተገኘው ሰባት ብቻ ነበር አሉ። ምንም ፖለቲካ ባልወድም “ለአንቺ የተሰጠሽ ኮንዶሚኒየም የጓሮ አትክልት ስፍራ አብሮ ተያይዞለታል እንዴ?” ብዬ ባለመጠየቄ ሲቆጨኝ ነው የከረመው፡፡ እንኳን ቲማቲም ልንኮተኩትበት በቂ ቲማቲም ማስቀመጫ እንኳን ሳይኖረን…ብቻ ይቅር… (ያ ባል ተብዬ አጋባብኝ እንዴ!)
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
ሶፋ እንለውጥ ትላለች ላለው፣ እኔ እንግዛ እንጂ እንለውጥ ብዬ አላውቅም፡፡ እንለውጥ የምለው ሶፋ ሲኖረን አይደል እንዴ! ሶፋው የምንለው እኮ በአንድ ወቅት ሶፋ እንደነበረ አንዳንድ ምልክቶች ስለቀሩበት ነው፡፡ ሶፋው እኮ ከአያታቸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፡፡ አያቱ ለአባቱ፣ እሳቸው ለታላቅ ወንድሙ፣ እሱ ለታላቅ እህቱ…እኛ ቤት ሲደርስ እኮ አራተኛ ተራ ወራሾች ነን፡፡
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
“የአንተ እናት ማለት የቻንድራ እንጀራ እናት ማለት ናቸው፣” አለችኝ ያለው አዎ፣ ብየዋለሁ፡፡ እሳቸው ቤታችን በመጡ ቁጥር መሶቤን እየከፈቱ እንጀራ የሚቆጥሩት  ምን የሚሏቸው ኦዲተር ናቸው!  
ፈረሱላ በርበሬ በሳምንት ይለቅ በዓመት እሳቸው ምን ዶላቸው! በመጡ ቁጥር “በርበሬ አልቆብኛል…” እያሉ በጣሳ እየሰፈሩ የጨረሱት እሳቸው አይደሉም እንዴ!
“አንዳንዴ ነገረ ሥራሽ ሁሉ የዋንዳን ይመስላል…” ሲለኝ ማማሰያ መወርወሬ ልክ ነው። አጠገቤ ሚሳይል  እንኳ ቢኖር እወረውርበት ነበር። እኔ ነኝ ዋንዳ! እኔ ነኝ ተንኮለኛ!
‘እነሆ በረከት’ እንባባል ስላት እምቢ አለች ስላለው…አሁን እንደ እሱ በስሏል የሚባል፣ ዕድሜውን በእንትኑ የቋጠረ ሰው፣ እንዲህ አይነት ነገር በአደባባይ ይናገራል! እምቢ ብለውስ! ቀኑን ሙሉ በሥራ ስደክም ውዬ፣ እሱ ግፎ በመጣ ቁጥር ተጨማሪ የሌሊት ሥራ ምን በወጣኝ!
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
‘ሀብትሽ በሀብቴ’! ተባብለናል ነው ያለው። ለወጉ እንደዛ ተባለ እንጂ እኔም እሱም የነጣን፣ የገረጣን ቺስታዎች አልነበርንም እንዴ፡፡ ያቺን ሶፋ የሚላትንና ሦስት እግር ብቻ ያላትን አልጋችንን ነው እኮ ሀብት የሚለው! እኔ ልኬን ስለማውቅ አፍ አውጥቼ እንዲህ አልልም፡፡
ደግሞ እሪ እላለሁ አለች ላለው… እኔ ምን ብዬ ነው እሪ የምለው! አላርፍም፣ አደብ አልገዛም ካለ በጥፊ አላጠናግረውም እንዴ!
ደግሞ ያለማፈሩ ፕሮግራም እናውጣ አይለኝም! ለአስቤዛ እንኳን ይሄ ነው የሚባል ፕሮግራም የሌለን ለእሱ ፕሮግራም እናውጣ!
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
“ከአንተ ጋር እየተጨቃጨቅሁ ልጅነቴን አላሳጥርም…” አለች ላለው አጣሞታል፡፡ እኔ ልጅነቴን እንዳላሳጥረው ሳይሆን ልጅነቴን አሳጠርከው ነው ያልኩት፡፡ ከፈለገ እንደገና ስዋስው ይማር፡፡ ደግሞስ ብልስ! ልጅ ነኝ ብልስ! እንኳን እኔ ገና ስንት ዓለም አያለሁ የምለው፣ የሀምሳና ስድሳ ዓመት ሴቶች ሁሉ ልጅ ሆነው የለም እንዴ! አላወቀ እንጂ እሱ ምርኩዙን ሲይዝ እኔ ገና ሚኒስከርቴን አልጥልም፡፡
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
“የእኔ ሚስት እንኳን ዘውድ ልትሆንልኝ አናቴ ላይ እንደ ጂብራልታር አለት ተከምራብኛለች…” አይደል ያለው! ዘውዱ ማን እንደሆነ፡ አለቱ ማን እንደሆነ እናያለን፡፡ ላውራ ካልኩ ስንት የማወራው ነበረኝ፣ ግን ጉዳችንን አደባባይ ላለማውጣት ዝም እላለሁ። አላርፍ ካለ ግን አራት ነጥቧና፣ ድርብ ሰረዟ ሳትቀር ሁሏን ነገር እዘከዝካታለሁ፡፡
እናማ ባሌን…ከጅብ የምታስጥል ሁን በሉልኝ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!




Read 4903 times