Saturday, 04 June 2016 12:57

“ሀሳብም ሒሳብም ቀንሶልናል!”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

    እንደምእተአመቱ የልማት ግብ ሪፖርት ከሆነ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ፣ አምስት ዓመት ሳይሞላቸው የሚሞቱ ሕፃናት ቁጥር በአስገራሚ ሁኔታ ቀንሶአል። ከአንድ ሺ ሕፃናት መካከል፣ 90 ያህሉ የአምስት ዓመት ልደታቸውን ሳያከብሩ ነበር የሚሞቱት - በ1990። የሟቾቹ ሕፃናት ቁጥር፣ በ2015 በግማሽ ቀንሶ ወደ 43 ወርዷል። ከሰሀራ በታች ያሉ አገራትን ሪፖርት ስንመለከትም፣ ከአንድ ሺ ሕፃናት መካከል አምስት አመት ሳይሞላቸው 176 ይሞቱ እንደነበረና አሁን ወደ 86 ዝቅ እንዳለ ይመሰክራል። ቢሆንም ግን በአለም አቀፍ ደረጃ ሲለካ፣ በዚህ የአፍሪካ ክፍል የሕጻናት ሞት አሁንም ከፍተኛ ነው።
በዚህ እትም፣ “ማህበረሰብ አቀፍ የጨቅላ እና የእናቶች ጤና ክብካቤ” ዙሪያ ነው የምናስነብባችሁ። በደቡብ ወሎ፣ በተሁለደሬ ወረዳ የሱሉላ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ፣ ገና የተወለዱ ጨቅላዎችን እና እናቶችን በመንከባከብ ዙሪያ ህብረተሰቡ በምን መልክ ተቀናጅቶ እንደሚሰራ የተመለከትን ሲሆን፣ በመንግስት ደረጃ በጤና ኤክስንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት ለሚከናወኑ ስራዎች፣ ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the children) እገዛዎችን እና ስልጠና በመስጠት ሲተባበር ታዝበናል።
አቶ ሀብታሙ ጥላሁን ከሴቭ ዘ ችልድረን እንደገለጹት፡-
“በኦሮሚያ ስፔሻል ዞን እና በደቡብ ወሎ፣ 844 የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች፣ በጨቅላ ሕጻናት ጤና ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጎአል። ከዚህ ጋር ተያይዞም 485 የጤና ኬላዎች፣ የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና እንዲጀምሩ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ለጤና ክብካቤው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች የተሰጡ በመሆኑም፣ ስራውን በሚመለከት ክትትል በመደረግ ላይ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል። አቶ ሀብታሙ በማያያዝም ባለሙያዎቹ የጨቅላ ሕጻናትን እና የእናቶቻቸውን ጤና በሚመለከት ቤት ለቤት እየሄዱ እና በጤና ተቋሙም አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው” ብለዋል።
የጤና ኤክስንሽን ባለሙያዎቹ ወ/ሮ አስረበብ ይመር እና ወ/ሮ እጅጋየሁም፣ ለነዋሪዎች በሚሰጡት የጨቅላ ሕፃናት የጤና አገልግሎት ዙሪያ አነጋግረናቸዋል።
 “ስልጠናውን ከሴቭ ዘ ችልድረን ካገኘን በሁዋላ የምንሰጠው አገልግሎት በእጅጉ የተለየ ነው። በፊት ተጠቃሚዎች ወደእኛ ይመጣሉ እንጂ እኛ ወደቤታቸው አንሄድም ነበር። አሁን ግን በየቤቱ እየሄድን አገልግሎቱን ስለምንሰጥ እኛ እራሳችን እውቀታችን እየዳበረ ነው። ምክንያቱም ለጨቅላዎችም ይሁን ለእናቶቹ የተሰጠንን የህክምና መርጃ ቻርት እዚሁ እቢሮአችን ቁጭ ብለን እንድናነብ እና እንድንረዳው አስፈላጊ ሆኖአል። ምክንያቱም የህክምና እርዳታውን ለመስጠት በየቤቱ ከሄድን በሁዋላ ተጠቃሚዎች ፊት ቁጭ ብለን ገና ማንበብ ስለማይገባን ነው። መድሀኒት አሰጣጡ ላይም ሆነ ሌሎች ተያያዥ ነገሮችን አስቀድመን በደንብ ማወቅ እንዳለብን በስልጠናው አማካኝነት ስለተረዳን አሁን ከበፊቱየተሸለ እየሰራን እንገኛለን።” ብላለች ወ/ሮ አስረበብ።
ወ/ሮ እጅጋየሁ በበኩልዋ፡-
 “በቀበሌያችን የሴቶች ልማት ቡድን አደረጃጀት አለ። እንደአደረጃጀቱ 26/የልማት ቡድኖች አሉ፣ 115/የ አንድ ለአምስት መሪዎች፣ 630/ የተደራጁ ጠቅላላ ግለሰቦች አሉ። ስለዚህ ይህንን የጨቅላ እና እናቶችን ጤና አገልግሎት ለመስራት ኮማንድ ፖስት ብቻ ሳይሆን የልማት ቡድኖቹም ያግዛሉ። ልማት ቡድኖቹ በስራቸው ካለው ህብረተሰብ መካከል ማን እርጉዝ እንደሆነ ማን ጤና ጣቢያ ሄዶ እንደወለደ ታሳውቃለች። ልማት ቡድኗ በስርዋ ላሉ ሴቶች የበለጠ ኃላፊነት ስላለባት ከእርግዝና ወሊድ እና ድህረ ወሊድ ድረስ ያለውን ሁኔታ መዝግባ ታሳውቃለች። ለሚመለከተው ክፍልም ሪፖርት ታደር ጋለች። በዚህ ቀበሌ ማንም በቤቱ የሚወልድ የለም። ይህ እንዳይሆንም ለህብረተሰቡ በተለያዩ መድረኮች ተገልጾአል። እንዲማሩም ተደርጎአል። ምናልባት እንኩዋን አንዲት እናት የምትኖርበት ቦታ እሩቅ ቢሆን በጤና ጣቢያ የእናቶች ማቆያ ቤት ስለተዘጋጀ አስቀድማ ከዚያ በማረፍ መውለድ ትችላለች። ህብረተሰቡ በማቆያው ስፍራ የሚደረገውን ዝግጅት በሚመለከት በሙሉ ፈቃደኝነት ከገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ስለሚያዋጣ ካለምንም ችግር እንዲስተናገዱ ይደረጋል” ብላለች።
የሱሉላ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ጌትነት አስረስ እንደገለጹት፡
“በሱሉላ ቀደም ሲል በአመት 60/ወይንም 20/ የሚሆኑ እናቶች ነበሩ የሚወልዱት። አሁን ግን መንግስት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እናቶች በየቤታቸው መውለድ የለባቸውም...በሰለጠነ የሰው ኃይልና በጤና ተቋም መውለድ አለባቸው...የሚል አቋም በሀገር ደረጃ በመያዙ አሁን በተቻለ መጠን ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በተደራጀ መልኩ ስለምንንቀሳቀስ ቁጥራቸው ከፍ ያለ ሆኖአል። እኛ በምንሰራባቸው አካባቢዎች እናቶች በመቆያ ቤት እንዲስተናገዱ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍ ያለ በመሆኑ ከ800/ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር እንሰበስባለን። በእንደዚህ ያለ አካሄድ ማረፊያ ቤታቸውን ሰርተን ለገንፎ እና ለተለያዩ ወጪዎች የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እያሟላን እንገኛለን። ህብረተሰቡም የሚያዋጣው በአንድ መልኩ ሳይሆን እህል አምራች የሆነው ገብስና ስንዴ የመሳሰሉትን ሲሰጥ ጫት አምራች የሆኑት ደግሞ የሚደርስባቸ ውን ገንዘብ እያዋጡ በጣም በጎ ስራ እየተሰራ ነው። እናቶቹ አስቀድመው በእና ቶች ማቆያ ቤት ሲገቡ ከመውለዳቸው በፊት ቤተሰባቸው ተሰብስቦ ፋጡማ ቆሬ ያከብሩ ላቸዋል። ፋጡማ ቆሬ ማለት በባህላችን ሴቶች መውለጃቸው ሲቃረብ አስቀድሞ ገንፎ በማገንፋት እና ቡና፣ ጫት የመሳሰለውን በማዘጋጀት እየተመገቡ እርጉዝዋ ሴት በሰላም እንድትገላገል አምላካቸውን የሚለምኑበት ስነ ስርአት ነው። የገንፎ እና የዱአ ጸሎት ስነስርአቱ ከወለዱም በሁዋላ የሚቀጥል ነው። እንግዲህ ይህ ወጪ በህብረ ተሰቡ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ነው” ብለዋል።
የበጀት አጠቃቀሙን በተመለከተም ሲያብራሩ “አደረጃጀቱ አንድ ለአምስት፣ ኬዝ ቲም፣ ኮማንድ ፖስት አለ። በእነዚህ አማካኝነት በየሳምንቱ ይገመገማል። ስለዚህም ስራውን የተቃና ለማድረግ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በየቀበሌው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የሚከታተለው ስለሆነ ተጠያቂነትን በሚገባ ያገናዘበ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከህብረተሰቡ ለእናቶቹ ሲባል የተሰበሰበው ገንዘብና ንብረት እንዳይባክን የሃይማኖት አባቶችና ከአመራሩ ተወካዮች ሳይኖሩ ምንም የሚነካ ነገር የለም። ”እንደ አቶ ጌትነት አስረስ።
ወ/ሮ አስረበብ ይመር እንደሚሉት፡-
“ኮማንድ ፖስት የሚባለው አካል በንኡስ ለሶስት የተከፈለ ነው። አደረጃጀቱም ከባለሙያዎች ድብልቅ ተደርጎ ነው። ለምሳሌም በእኛ ቀበሌ ከህብረተሰቡ ከተመረጡት ሰዎች በተጨማሪ ፖሊስ፣ ጤና ኤክስንሽን እና ስራ አስኪያጅ የተጨመሩበት አደረጃጀት ነው። ይህ የባለሙያዎች እና የአመራሮች ስብስብ በሶስቱም ቡድኖች እንዲዋቀር ተደርጎአል። ይህ ቡድን በስራቸው ከሚኖሩ ሴቶች ውስጥ አዲስ እርጉዝ ሴት ስትገኝ መዝግበው ይይዙና እርጉዝዋ ሴት በየአስራ አምስት ቀኑ ወደ ጤና ኬላ በመምጣት የነብሰጡር ኮንፍረንስ እንድትካፈል ቅስቀሳ ያደርጋሉ። እንደወ/ሮ አስረበብ “ጨዋታው የሚያልቀው እዚህ ላይ ነው። ” ወደኮንፍረንሱ ሲመጡ ልጅን በተመለከተም ይሁን እርግዝናን ወይንም ወሊድን በተመለከተ ባሉበት አካባቢ የሚነገረውን ወይንም ያለውን ልማድ በሙሉ አውጥተው እንዲነጋገሩ ይደረጋል። በእነሱ ሀሳብ ላይ በመመርኮዝም ከመድረኩ ሰፋ ያለ ትምህርት ይሰጣል። ጊዜው እየጨመረ ሄዶ ወደ መውለጃዋ ስትቃረብ አስቀድሞውኑ ዝግጅት እንድታደርግ ኮማንድ ፖስቱ ያነጋግራታል። በቤት ውስጥ መውለድ አደጋ ሊኖረው እንደሚችል፣ የት መውለድ እንደምትፈልግ፣ በገንዘብ ደረጃ መዘጋጀትን፣ ወደማቆያ ቤት እንደምትሄድና እንደማ ትሄድ በምጥ ሰአት አብሮአት የሚሆነውን ሰው መምረጥን የመሳሰሉትን ሁሉ እንድትወስን ትደረጋለች። እናቶች ብዙውን ጊዜ በቤት ለመውለድ ለምን ፈለጋችሁ ?ተብለው ሲጠየቁ “ሐኪም ቤት በምጥ ሰአት የሚጮኸው ለብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜም ሐኪሞቹ ሊቆጡ ይችላሉ። አይዞሽ የሚል ማንም የለም... የሚል መልስ ነው የሚሰጡት። ስለዚህ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በምጥ ሰአት አይዞሽ ሊላት የሚችል ቤተሰብ እራስዋ የመረጠችውን ይዛ እንድትገባ ይደረጋል። “
በኮማንድ ፖስት አባልነት ከታቀፉት የህብረተሰብ ክፍሎች አንድ አባት የሚከተለውን ብለዋል።
“ስሜ አሊ ሰይድ ይባላል። የንኡስ ሶስት የጨቅላ ሕጻናት ኮማንድ ፖስት አባል ነኝ። በእቅድ ላይ ተመስርተን እናቶችን እና ጨቅላ ሕጻናቱ ጤናቸው እንዳይጎዳ አስፈላጊውን ስራ እንሰራለን። እኔ አሁን የልጆች አባት ነኝ። አንዲቱ የ20/ ቀጥላ 16/ እንዲሁም 14/ አመት የሚሆናቸው ልጆች ያሉኝ ሲሆን አሁን በቅርቡ ደግሞ የ2/ሁለት አመት ልጅ አለኝ። ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ቀደም ያሉት ልጆች ሲወለዱ የነበረው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነበር። እናትየው ከጸነሰች ጀምሮ እንዴት ትገላገል ይሆን ?የሚለውን ጭንቅ ዛሬ ላይ ሳስበው እጅግ ይዘገንናል። በመውለጃ ሰአትዋ ትሙት ትኑርም ማወቅ አይቻልም።
በቃ እግዜር እንደፈቀደ ብሎ መተው ብቻ ነበር። አሁን ግን ሐኪሞቹ በቅርብ እየተከታተሉ፣ እሱዋም ኮንፍረንስ እየተካፈለች እራቀኝ ብትል ማቆያ ቤት አስቀድማ እያረፈች፣ ገንፎው፣ ቡናው፣ ጫቱ፣ ተዘጋጅቶ...ቤተሰቡ አብሮአት እየመጣ ...እንዲያው ልጁን በአለም መጠበቅ ሆኖአል። ጊዜው እጅግ ተለውጦአል። ፋጡማ ቆሬን ሆነ ከወለደች በሁዋላ የማሪያም መሸኛ በዚያው በሐኪም ቤቱ ገንፎ እያገነፉ ቤተሰቡ ተሰብስቦ እልል እያለ...በጣም ደስ ይላል። ጊዜው በጣም ተለውጦአል። ሀሳብም ሒሳብም ቀንሶልናል። አምቡላንስ፣ ሐኪም፣ መድሀኒቱ በነጻ እየተሰጠ ምን ችግር አለ? እናት መሞትዋ ቀርቶአል።”

Read 1460 times