Saturday, 04 June 2016 12:42

“ጉድና ጅራት …”

Written by  ፍጹም ንጉሴ
Rate this item
(16 votes)

ከ….ከ…ከ…ቂ….ቂ…ቂ ክፉኛ የተለቀቀ የሴት ድምጽ፡፡
የሞት ያህል ወስዶት ከነበረው እንቅልፍ ቀሰቀሰው፡፡ አንድ ክፍል በሆነችው የላጤ ቤቱ ውስጥ አይደለም የነቃው፡፡ ዙሪያውን በደንብ ቃኘው፡፡ ተራ በሚባል የአልቤርጐ ክፍል ውስጥ መሆኑን ተረዳ፡፡ የቀሰቀሰውን የማሜን ድምጽ ዳግም መስማት ፈለገ፡፡ ግን አልሰማም፡፡  
በተፈጥሮው ከባድ የሆነው ጭንቅላቱ የበለጠ ከብዶታል፡፡ ተመልሶ ትራሱ ላይ ጣለው፤ የዞረ ድምር! እንደ አሚር ያጣበቀው እስከሚመስለው ድረስ ማንቀሳቀስ አልቻለም፡፡
“እኔ ራሴ እንዴት ወደዚህ መጣሁ?” ራሱን ጠየቀ፡፡
ትናንትና…
አይኖቹን ከድኖ ያሰላስል ያዘ…ትናንት ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ለወራት ሲጥሉት የነበረ ዕቁብ ዕጣው በሱ ቢሮ ተጣለ፡፡ እናም ለሱ ወጣለት፡፡ በደስታ ሰከረ…ማሜ በዓይኑ ላይ ተንከራተተችበት፡፡
የምትሰራበት ቡና ቤት ከነታዳሚው ታየው…ቅር አላለውም፤ እሷን ብቻዋን ነው የሚወስዳት፡፡
ይችን ቀን ሲጠብቅ ብዙ ቆይቷል…ቢሮ መቆየት ባለመቻሉ ወጣ፡፡ ከላይ ቆንጠር አድርጐ ቀሪውን ባንክ አስገባ… ከዚያም ወደ ማሜ ገሰገሰ፡፡
ቦጋለ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡ በነበር ያስቀረው የሚስቱ ድንገት ልጁን ይዛ መጥፋቷ ነው፡፡ ለምን እንደዛ እንዳደረገች አያውቅም፡፡ ጨቅጫቃ፤ ቅናተኛ አይደለም፡፡ በአንባጓሮ ፈጣሪነትም አይታወቅም፡፡ መጠጥም አይጠጣም ነበር፡፡ ጓደኞቹም ጥቂት ናቸው፡፡ ገንዘብ አያባክንም፤ ሚስቱ ሁን እንዳለችው ነበር ሲሆን የኖረው፡፡ ሆኖም ምንም ሳትለው ጥላው ጠፋች፡፡ ፈለጋት አስፈለጋት፤ ሊያገኛት አልቻለም፡፡ ወራት አለፉ፡፡ ሌላ ሰው ወዳ ነው የሚል ወሬ ደረሰው፡፡ ያኔ ወሬውን ተከትሎ ፈለጋት፡፡ አላገኛትም፡፡ ተስፋ ቆርጦ ተወው፡፡ ራሱን ቀና ለማድረግ ሞከረ፡፡ ፈሪ ነው፤ በተለይ ሴቶችን ይፈራል፡፡ አንድ ቀን እግር ጥሎት አንድ ቡና ቤት ጎራ አለ፡፡ ያን ጊዜ ነው ማሜን ያወቃት፡፡ ትንቡክቡክ ያለች ዕድሜዋን ለመገመት የማትመች፣ ልጅ ልጅ የምትል ሴት ናት፤ ማሜ፡፡ አሁንም አሁንም የምትስቅ፡፡ ሳትስቅም ፊቷ ክፍት ድምቅ ያለላት፡፡ አጠር ሞላ ያለች፡፡
እንደገባ ቂጡ መቀመጫው ላይ ሳይደርስ፣ ዓይኑ እሷ ላይ መውደቁን በመረዳቷ ሆነ ብላ ሳይጠራት አቤት እያለች ስታማልለው አመሸች፡፡ የግዱን ተነስቶ ሄደ፡፡ በቀጣዩ ቀን ተመለሰ፡፡ ብዙ ቀን እንደምታውቀው ሰው ተቀበለችው፡፡ በሷና በመጠጡ ቀስቃሽነት አንደበቱ እየተፈታ ሲመጣ፣ ቅርርባቸው መስመር የያዘ ይመስል ጀመር፡፡
“ማሜ ነው አይደል ስምሽ?”  አጠያየቁና … ነገ ሥራው አስቂኝ ሆኖባት ተንከትክታ ሳቀች፡፡
“አዎ”
ፈራ ተባ እያለ፤“ቦጋለ እባላለሁ፤ተቀመጭ እስኪ”
“አይንህና አፍህ ቦታ ቢቀያየሩ ጥሩ ነበር” አለች፤ እየሳቀች፡፡
የተናገረችው ባይገባውም፤ “ይሻል ነበር አይደል!”
“አዎ ነበር”
መጠጥ እየጋበዛት የት እንደሚሰራ … ባለትዳር እንደነበር … ሚስቱ ጥላው መጥፋቷን .. በየመንገዱ የ6 እና የ7 ዓመት ልጆችን ባየ ቁጥር፣ ቆሞ ልቅም አድርጎ ሳያይ እንደማያልፍ --- ሁሉንም ነገራት፡፡ ማሜ በተራዋ ዕውነት ይሁን ውሸት ያለየለት ገለፃ አደረገችለት፡፡ ከገጠር በልጅነቷ መምጣቷን፣ ዘመድ ቤት መቆየቷንና ሲሰለቻት ሰው ቤት ተቀጥራ መስራት መጀመሯን፤ ወንድ ቀጣሪዎቿ ጉንተላ ሲያበዙባት ጥላ ወጥታ ወደዚህ ቡና ቤት በአሻሻጭነት መግባቷን ---- እጥር ምጥን አድርጋ … በሳቋ እያጀበች … ነገረችው፡፡ ጎራ እያለ ባያት ቁጥር … በጋለ ፍቅሯ ይነድ ጀመር፡፡
አንድ ቀን ሞቅ እስኪለው ጠብቆ፤ “ላገባሽ እፈልጋሁ” አላት
“ዕውነትክን ነው?” ከሙዚቃው በላይ እየሳቀች … ይሄኔ ሳቋ አስከፋው፡፡
“እሱንማ በደንብ አውቃለሁ”
“እ? ታውቂያለሽ?...
አንድ ሁለት ቀን አደሩ … ቦጋለ የጣቷ ቀለበት ያህል ሆነ … ሲሻት ውልቅ ጣል … ራቅ ታደርገዋለች፤ ሲሻት እዛው ታሽከረክረዋለች …
“እና ምን አሰብሽ?”
“ለባልና ሚስትነቱ? …”
አንድ ያላየው ባላንጣ እንዳለበት ጠርጥሯል፡፡ በሩቅ ያለ ይሆናል፡፡ ወይም እሱ ከሰከረ በኋላ የሚመጣ … አንዳንድ ጊዜ ፊት ትነሳዋለች፡፡ በመጥላት ሳይሆን ምርጫ በማጣት … ጥፍት ትልበታለች፡፡ ያኔ ታዳሚው ሁሉ ምን ያቅበዘብዘዋል እስኪለው ድረስ ይፈልጋታል … ያለችበትን የሚነግረው ደ’ሞ የለም፡፡
“አዎ … ለባልና ሚስትነቱ”
“እጥር ምጥን ያለች ድግስ ያስፈልገናል … አይመስልህም…?”
“ልክ ነሽ”
“ለኔም ጥሎሽ ቢጤ ወርቅ?” እየሳቀች …
ወዷታል፡፡ እንደምንም የጠየቀችውን አሟልቶ፣ የራሱ ማድረግ እንዳለበት ወስኗል፡፡ … አሁን ያሰበው የሆነለት መሰለው፡፡  
እናቱን እንደናፈቀ ልጅ እየበረረ ገባ፡፡
“ቦግዬ--; ተጠመጠመችበት…ቡና ቤቱ ባዶም ባይሆን ሙቀት የለውም፡፡ የተራበው ማሜን ቢሆንም ምግብ አዘዘ፡፡
እየተጐራረሱ፤“ያልኩሽ ሆኗል…”
ትፈነጥዛለች ብሎ ነበር የጠበቀው፤
“ሆነ? ጥሩ!…” አለችው፡፡
“እንዴ ማምዬ፤ ዛሬ አብረን ወደኔ ቤት እንሄዳለን”
“እንሄዳለን፤ መቼ አንሄድም አልኩኝ”
“ደስ ያለሽ አትመስይም”
“አንድ ሰው አለ…እሱ ነው…” መቀጠል አልፈለገችም፡፡
የጠረጠረው እውነት በመሆኑ እየፈራና እየተናደደ… “ማናባቱ ነው?”
“ተው ቦግዬ፤ ወንድ ለመምሰል አትሞክር”
“ወንድ ሳልሆን እንዴት ሚስት ልፈልግ እችላለሁ?”
“ዘራፉ ላይ ማለቴ ነው” ቢከፋውም ለኔ ብላ ይሆናል ብሎ አስቦ ተወው፡፡ ዋናው ማሜን ቀድሞ የራሱ ማድረጉ ነው፡፡
“ለማንኛውም ጠብቀኝ፤ ያለ ሰዓቴ መውጣት አልችልም ታውቃለህ”
ወደደም ጠላም ይጠብቃል፡፡ እስከዚያም ይጠጣል…
ከእንቅልፉ የቀሰቀሰው ዓይነት ድምፅ ከትውስታው አናጠበው፡፡ በክፍሉ ውስጥ ከሱ በቀር ማንም አልነበረም…‹ታዲያ ድምፁ እንዴት ቅርብ ሆኖ ተሰማኝ?› እያለ ድምፁን በድጋሚ ለመስማት ጠበቀ…የጭፈራ አይነት “ድም…ድም” “እህም…እህም…” የሚል ድምፅ … “ከጐረቤት ክፍል ይሆናል” ብሎ ወደ ትውስታው ተመለሰ…
ትናንትና …ሲገባ ቀዝቃዛ የነበረው ቡና ቤት … እየሞቀ እየወበቀ መጣ፡፡ በአወናባጅ መብራቶች አይኖች ይወናበዱ…ክብሮች ይናዱ ጀመር፡፡ ያቀረቀሩ አንገቶች ሽቅብ ይመዘዙ … ደረቶች ይነፉ…ጥንዶች ይላፉ፤ ትከሻዎች በጭፈራ ይረግፉ ጀመር፡፡ ሞቅ እያለው ነው…ለማንኛውም ብሎ ሂሳብ ከፈለ…ማሜ ስላልነበረች ለባልደረባዋ ሰጣት…ቢራውን ጨልጦ ሲያስቀምጠው … በብስጭት ጠረጴዛውን ደበደበው…ማሜ እየበረረች መጣች፡፡
ወደ ጆሮው ተጠግታ፤ “ትንሽ ቦግዬ…”
“እሺ” ድምፁ እያላዘነ መሆኑ ሲታወቀው፣ በሃፍረት ወበቀው፡፡
“ቆይ ላምጣልህ”
እየበረረች ስትሄድ የተለያዩ እጆች ወደሷ እየተወነጨፉ ጡቷን … ሆዷን … ጭኗን … መቀመጫዋን … ሲነካኩ …ሲቆነጣጥሩ … ብሽቅ አለ፡፡ … ጂን ይዛለት ተመለሰች … አንዴ ጂኑን አንዴ እሷን ሲያይ፤ “ለምን መሰለህ ቦግዬ”
“እ … ለምንድን …ነው?”
“እዛ ላይ … ቦግ እንጂ እልም እንዳትልብኝ” ብላው ሳቀች፡፡ ሳቋን ጥሪ አቋረጠው፡፡ ስትደነግጥ … ደስም ሲላት በብዥታ ውስጥ አይቷታል … ጂኑ ጂኒም ነበረበት .. በሆዱ ውስጥ የተጠራቀመውን ቢራ እንደ ረባሽ ከብት ገብቶ አተረማመሰው፤ ደሙ ፈጠነ፤ ቀጠነ፡፡ ሰውነቱ በሙቀትም በማሜም ናፍቆት ይነድ ጀመር …
ጠበቃት … ጠበቃት … ዥንጉርጉሩ መብራት ቤቱን ብቻ ሳይሆን ሰውን ሁሉ አዥጎረጎረው፡፡ ፀባዮች ተዥጎረጎሩ … ጭምቱ ተገለጠ … ፈሪው ጀገነ፡፡ ቦጋለ .. አይኖቹን መግለጥ እየተሳነው፣ ማሜን የሚያገኛት ለምፅዓት እስኪመስለው ቆየ፡፡ ተስፋው ተዳከመበት … ማሜ እየበረረች ወደሱ መጣች፣ “የ…የ…የ ሄደሽ ነበር?”
“አለሁ …መጣሁ”
“መ…ጣሁ… መጣ…ሁ…ስስ…ንት መ…ጣ..ሁ” እንባው የመጣበት ይመስላል፡፡
“ልብሴን ልቀይር ነው” እያየችው ስትስቅ፣ እሱን ሳይሆን በቲቪ አስቂኝ ቪዲዮ የምትመለከት ነበር የምትመስለው፡፡
ከመሃል ያለው፣ ትዝ አልልህ አለው፡፡ በደንብ ቀና ብሎ … ፈለጋት፡፡
 “ግን እንዴት ወደኔ ቤት ልንሄድ ተነጋግረን ወደዚህ መጣን?”
መልሱን ፍለጋ ወደ ትውስታው ተመለሰ …
ትናንትና … ምሽት፡፡ ደግፋው ወጡ፡፡
“ታክሲ!”
“እዚህ አይደለማ”
 በሷ መደገፍ ሃፍረት ሆኖበት፤ “ልቀቂኝ መሄድ እችላለሁ” ሲላት፤ ሳታግደረድረው ለቀቀችው … ወደ አንድ ጎን ሲያዘም እጇ ከኮት ኪሱ ሲወጣ፣ ኪሱ ተቀደደ፡፡ ለመውደቅ ሲቸኩል … ፈጥና ስትይዘው፤ ‹እጇ ኪሱ ውስጥ …› ግርም እያለው መላልሶ አሰበው፡፡
ወደ ዋናው ጎዳና እየሄዱ … እየተቃቀፉ … እየተሳሳቁ … ድንገት ወደነሱ አቅጣጫ የመኪና መብራት … ሲበራ --- ማሜ ስትደነግጥ … “መጣሁ እዚህ ጠብቀኝ” ብላው ስትሮጥ … እሷን ተከትሎ ለማየት ቢፈልግም … ስካር አድክሞት … ወደ ግንቡ አጥር … ተወላክፎ ሲደገፍ… አቅቶት እየታከከ … አስፋልቱ ላይ ዝርፍጥ አለ፡፡ ከዚያ … ጆሮዎቹ የማሜን ድምፅ፤ ዓይኖቹ እሷን በየፊናቸው እየፈለጉ … በአዕምሮው የጠፋበትን ትውስታ ለማግኘት ብዙ ጣረ …
ትናንት ምሽት … እዚያ ጥግ ምን ያህል እንደቆየ ባያውቀውም፤ የአስፋልቱ ቅዝቃዜ አነቃው … ልብሱም ረጥቧል፡፡  ሙዚቃ … ዘፈን … የታጀበ … ያልታጀበ … ከሩቅ … ከቅርብ … ድምፅ የሌላት ሴት ስትዘፍን … ስትጨፍር… ስትረግጠው … ስትወድቅበት … ሳቋን ስትለቀው …
“የኔ ቆንጆ መጣሽ?”
“መጣሁ … መጣሁ”
“እወድሻለሁ … ሚስቴ ሁኚ”
“እሺ ባሌ … ባሌ … ባሌ … ነህ በቃ”
“አንሺኝ… ደግፊኝ”
ደግፋው … ሲሄዱ … “እንሂድ … ማ … ማ …”
እንዴት እንደገቡ ትዝ አልልህ አለው፤ ‹እንዴትም ይሁን ገብተናል ማለት ነው፤ታዲያ የታለች?› … የግዱን ተነሳ፡፡
ሰውነቱ የሱ አልመስልህ አለው፤ ከበደው … አቅሙም ክዶታል … ልብሱ ወለሉ ላይ ተበታትኗል … ‹እንዴ እንዴ ኮቴ ..› ኮቱ በምላጭ ይሁን በመቀስ ተተልትሏል ..
“ማሜ … ማሜ”
“ወዬ … ወዬ”
‹ብዙ ጠጥታ ነበር እንዴ? ድምጿን ምን አጎረነነው› እያለ ሲያስብ፤ ከቁም ሳጥን ውስጥ እየሳቀች ወጣች፡፡
“ባሌ … ባሌ .. ውዱ ባሌ” …
ዓይኖቹ በድንጋጤ እንዳፈጠጡ ቀሩ፤ ማሜ አይደለችም፡፡ “ሰርጌ ነው” እየጮኸች፤ “እልል ልል … በሉ ኑ … ሁላችሁም ኑ” የውር ድንብሩን ልብሱን ፈልጎ ለበሰ፡፡
 ጫማውን ሳያስር፣ ሸሚዙን ባግባቡ ሳይቆልፍ፣ በሩን ከፍቶ እግሬ አውጭኝ አለ፡፡ … ‹እንዴት ከዚች እብድ ጋር ላድር ቻልኩ?›
እሷ ‹ባሌ› እያለች እያሳደደችው ወጡ፤ ብዙ ሰዎች ቆመው እንደ ጉድ ሲያዩዋቸው፣ በሀፍረት መደበቂያ እስኪያገኝ ሩጫውን አስነካው፡፡


Read 4137 times