Saturday, 04 June 2016 12:14

“…አንድ በሉልኝ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(20 votes)

እንደምን ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… “ሚስቴ ግራ አጋብታኛለች…” የሚል ሰውዬ ሳይጽፈው ጽፎት ሊሆን የሚችል ማመልከቻ ቢጤ ነገር ነው፡፡
ለሚመለከተው ሁሉ፡፡
(የማይመለከተውም ወደፊት ሊመለከተው ስለሚችል ቢያነበው ጸሀፊው ቅር አይለውም፡፡)
ይህ ማመልከቻ አቤቱታ ወይም ብሶት ተብሎ ቢተረጎምም አልቃወምም፡፡ ምክንያቱም የእኔ ኑሮ “አቤት!” ብቻ ሳይሆን “እግዚኦ!” የሚያሰኝ ሆኗል፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዋ ሚስቴ (ከዚህ በኋላ ‘ሚስት ተብዬዋ’ እየተባለች የምትገለጸዋ) ነች፡፡ በእርግጥ ያገባኋት ደጅ ጠንቼ፣ ስንት ተለማምኜ መሆኑን አልክድም፡ ቢሆንስ…ደጅ ብጠናስ!  ብለማመንስ!…“አሁን አንተም እንደ ወንዶቹ ባል ነኝ ትል ይሆናል…” መባል አለብኝ! ሚስት ተብዬዋ እንዲሁ ነው ያለችኝ፡፡ ጊዜ የሰጠው እኛ ግቢ የሚገኝ አንድ ሰውዬ፤በመኪናው አጠገብ ባለፈች ቁጥር ጡሩምባውን እያስጮኸ ይተነኩሳታል፡፡ ድንገት በእግርም ካገኛት “ጎረቤት አይደለንም እንዴ…ለምን ቤቴ ብቅ ብለሽ ሻይ ቡና አትዪም…” ይላታል፡፡
አንድ ቀን… “ይሄ ሰውዬ አስቸገረኝ…” አለችኝ፡፡ አንበሳ ሆኜ “ምን አባቱ ቆርጦት፣ የቱ ሰውዬ ነው?” ስላት “ይሄ ማዶ ያለው ባለጊዜው ሰውዬ…” ስትለኝ አይደለም አንበሳ ልሆን አንበሳ የሚባል እንሰሳ መኖሩን ረሳሁ፡፡ የአቅም ጉዳይ ነዋ! እኔም ለማረሳሳት “ግዴለም፣ የፈለገውን ቢል አንቺ ምንሽ ይነካል፡ ፊት ስትነሺው ይተውሽ የለ…” ስላት ነው ‘አንተም ባል ትባላለህ’ ያለችኝ፡፡
አሁን ሰውዬው ዘንድ ሄጄ “ለምንድነው ሚስቴን የምታስቸግራት!” ብለው፣ “ደስ ስትለኝስ!” ቢለኝስ? ከፍ ብሎ የተወረወረውን ቅዝምዝም ዝቅ ብለው አላሳልፍ ያሉ የደረሱበትን እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
ሚስት ተብዬዋን አንድ በሉልኝ!
በትንሽ በትልቁ ሞራሌን እየነካችኝ ነው፡፡ መቼም ሰው ነኝና ከሥራ በኋላ ትንሽ ቀማምሼ እገባለሁ፡፡ (እኔ በአሥራ አንድ ሰዓት ቤት ገብቼ ቆጥ ላይ የምሰፍረው ዶሮዎቹ በስምንት ሰዓት እንዲሰፍሩ ነው!) ቀማምሼ ስልም የእውነት ቀማምሼ ነው እንጂ ነገሩን ለማለባበስ አይደለም፡፡ ይሄን ጊዜ ታዲያ መሸት አድርጌ ቤት ስገባ ትንሸ እንደው ደንቀፈቀፍ ያደርገኛል፡፡ ቢያደርገኝስ! ውሀ ስጠጣ አላመሸሁ! ታዲያ ወደ ሶፋውም ወደ አልጋውም ስሄድ ምኑንም ምናምኑንም ገጨትጨት ማድረጌ አይቀርም፡፡ ይሄኔ ሁለት ልጆቻችንን እያካለበች ወደ ጓዳ ታስገባቸዋለች፡፡ ልጆቼም “ምነው እማ፣ ምን ሆነሽ ነው?” ሲሏት “ቤታችን ውስጥ ሲኖትራክ ገብቷል…” ትላቸዋለች፡፡ አሁን አሥራ ሦስት ዓመት አብሮ የኖረ ባሏን ሲኖትራክ ማለት ልክ ነው? ለምን ሞራሌን ትነካዋለች!
እናማ…ሚስት ተብዬዋን አንድ በሉልኝ!
ደግሞም ሚዲያውን አስታግሱልኝ፡፡ ቤቴ ድረስ እየገባ የሚበጠብጠኝ አንዱም ሚዲያው ነው፡፡ እሷ የተነገረውን ሁሉ ያለማጣሪያ ወንፊት እያዳመጠች መከራዬን እያበላችኝ ነው፡፡ ነገሩ የሚጀመረው በተዘዋዋሪ ነው፡፡ “ለምንድነው ይሄንን አሮጌ ሶፋ በአዲስ የማንቀይረው…የሰዉ ባል ስንት ነገር ያደርጋል” ብላ ትተነኩሰኛለች፡፡ እሷ አላወቀች እንጂ አይደለም አዲስ ልቀይር ካለውም ትልቁን አስቀርቼ ሌሎቹን በመሸጥ የበጀት ጉድለት ማሟያ ላደርገው እያሰብኩ ነው፡፡
ትንሽ ቀን ትቆይና ደግሞ…“አሁን እኛም እንደ ሰዉ ቴሌቪዥን አለን ይባላል! በየቤቱ አርባ ሁለት ኢንች ፍላት ስክሪን ገብቷል ይሄ ባጃጅ ዘላለሙን እዚህ ተገሽሮ…” በማለት ትተነኩሰኛለች፡፡ በእርግጥ ሲገዛ ‘ባለቀለም’ የነበረው ቴሌቪዥናችን እንደ አመጽም እየሞከረው እንደሆነ አልክድም፡ አንዳንድ ጊዜ የሚያሳየን ቀለም የቀለም ጠበብት ገና ያልደረሱበት አይነት ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በዓል ላይ የመጀመሪያው ግራጫ ቴሌቪዥን ነገር ያደርገዋል፡፡ ለነገሩ ምን በቀለም የሚታይ ነገር አለና ነው! ኑሯችንና ነገራችን ሁሉ ጥቁርና ነጭ ሆኖ የለም እንዴ! እኔም “ለጥቁርና ነጭ ኑሮ ያለን ይበቃናል…” ስላት “ደግሞ ፖለቲካ እየተናገርክ ጦስ እንዳታመጣብኝ፣ ልጆቼን ላሳድግበት…” ትለኛለች፡፡ አሁን ይሄ ምን ፖለቲካ አለው! እኔ ባሏ ጥሩ ማረጋገጫ አይደለሁ፡፡  እንደዛ ወዜ ይቅለጠለጥ የነበርኩት ሰውዬ የእንትን ቡና ቤት ፎጣ መስዬ የለም እንዴ!
ታዲያ ደግጋማ “ይህን ግዛ፣ ያንን ቀይር…”  የምትለኝ የሚወራውን እየሰማች ስለሆነ ሚዲያውን አስታግሱልኝ፡፡ እኔ “ገንዘቡን ከየት አምጥቼ ነው የምገዛው?” ስላት “ይሄን ሁሉ ዓመት በሁለት ዲጂት ስናድግ ምንም ቤሳ ቤስቲኒ አልደረሰኝም ልትለኝ ነው!” ትለኛለች፡፡ አሁን ይሄንን ለማን እነግረዋለሁ!
እናማ…ሚስት ተብዬዋን አንድ በሉልኝ!
የመሥሪያ ቤታችንን ሥራ አስኪያጅም አስታግሱልኝ፡፡ እሱ እንጀራውን ሊያበስል በየሚዲያው እየቀረበ “የመሥሪያ ቤታችን ሠራተኞች በሁሉም ረገድ ደስተኞች ናቸው…” እያለ በለፈለፈ ቁጥር የእኔ ቤት ይተራመሳል፡፡ “ጧት ማታ ‘መሥሪያ ቤት አበሳጩኝ፣ መሥሪያ ቤት እድገት አልሰጥ አሉኝ’ እያልክ የምትነጫነጨው ይኸው አለቃህ ሁሉም ደስተኞች ናቸው እያለ አይደል!” ትለኛለች፡፡ አሁን ለዚህ ምን መልስ ነው የምሰጠው! ሚስት ተብዬዋ ከእኔ ከባሏ ይልቅ ‘ባዳው’ን ሚዲያ ነው የምታምነው!
እናማ…ሚስት ተብዬዋን አንድ በሉልኝ!
አሁን በዛ ሰሞን እናቴ ልትጠይቀን ብቅ ብላ ሚስት ተብዬዋ ያሳየቻት ሁኔታ እኔ ሆኜ ነው እንጂ ሰማንያ የሚያስቀድድ ነበር፡፡ ከመንገድ መጥታ ውሀ እንኳን የሚሰጣት ሲጠፋ ጓዳ ገባሁና “ኧረ እንደው ትንሽ እንጀራ በሹሮ እንኳን ስጫት…” ብላት “መች የጋገርከውን እንጀራ!” አለችኝ፡፡
“እሺ እንግዛ…” ብላት “አንገቴ ይቆረጣል እንጂ እዚህ ቤት የግዢ እንጀራ አይገባም!” አለችኝ፡፡ ለነገሩ በዛ ሰሞን ጤፍ ውስጥ ሰጋቱራ እየደባለቁ ሲሸጡ ተገኙ የተባለውን ከሰማች በኋላ ቤታችን ያለው ሁለት የምግብ አይነት ብቻ ነው…ፓስታና ሩዝ፡፡ ታዲያ ሚስት ተብዬዋ፣ እናቴን ለምን እንደሁ እንጃ አትወዳትም፡፡ ቢቸግረኝ በቀደም “አንቺ እማዬን ይሄን ያህል የጠመድሻት ምን አድርጋሻለች!” ብላት… “የአንተ እናት ማለት የቻንድራ እንጀራ እናት ማለት ናቸው፣” አለችኝ፡፡ እኔ ደግሞ ቻንድራ የሚባል ሰው ስለማላውቅ “ቻንድራ ደግሞ ማነው?” ስላት የሳቀችብኝን ሳቅ መቼም አልረሳውም፡፡ “አዲስ አበባ ውስጥ ቁጭ ብለህ ቻንድራን አታውቀውም! አሁን አንተ ሰው ትባላለህ!” አለችኝ፡፡ በኋላ ስጠይቅ ቻንድራ ተንኮለኛ እንጀራ እናት ያለችው በቴሌቪዥን የሚታይ የህንድ ፊልም ላይ የሚሠራ ነው አሉኝ፡፡ እና የእኔ ናት ነች ከእንጀራ እናት ጋር የምትወዳደረው!  
በእርግጥ ለምን ይዋሻል… እማዬ ቤታችን በመጣች ቁጥር ጓዳ ገብታ ሹሮውንም፣ በርበሬውንም መለካካት ትወዳለች፡፡ ከዛም…
“እናንተ በርበሬውን ትቅሙታላችሁ እንዴ!  በቀደም አይደል እንዴ አንድ ፈረሱላ የተፈጨው!” “ይሄ አመድ ነው ሹሮ! አሁን ይሄን ያዘጋጀች ሴት ነኝ ትላለች!” “ይሄ ሁሉ የቆሸሸ ድስት የተከመረው ማን መጥቶ ሊያጥብላችሁ ነው!”
ትላለች፡፡ ብትልስ! ልጇ አይደለሁ እንዴ! እሷን ከእንጀራ እናት ጋር…ያውም ከህንድ እንጀራ እናት ጋር ማመሳሰል ልክ ነው!
“ሚስት ተብዬዋ እናቴን የቻንድራ እንጀራ እናት ስትልብኝ ምን ልበላት?” ብዬ ምክር ስጠይቅ… “አንዳንዴ ነገረ ሥራሽ ሁሉ የዋንዳን ይመስላል በላት…” አሉኝ፡፡ እኔም አልኳት፡፡ እንደዛ ስላት የወረወረችብኝ ማማሰያ እስካሁን ከአእምሮዬ አልጠፋም፡፡
እናማ…ሚስት ተብዬዋን አንድ በሉልኝ!
ደግሞ መቼም ባልና ሚስት ነንና ‘እነሆ በረከት’ እንባባል ስላት “ቀኑን ሙሉ ስደክም ውዬ ሌሊቱን ደግሞ ላላርፍ ነው!” ትለኛለች፡፡ “አሁን እሱ ከመድከምና ካለመድከም ጋር ምን አገናኘው!” ስላት… “አንተማ ምን ቸገረህ!” ምናምን ትለኛለች፡፡ ቢቸግረኝ “እሺ ፕሮግራም እናውጣለት…” ስላት ከት ብላ ሳቀችብኝና… “አንደኛውን ለምን እቁብ እንጣጣል አትለኝም!” ብላኝ አረፈች፡፡
እንዴ… ስንጋባ ‘ሀብትሽ በሀብቴ’ ተባብለን አይደል እንዴ! የእሷ የሆነው ሁሉ ‘የእኔ’ አይደለም እንዴ! ታዲያ ለምን ትከለክለኛለች!
‘ሀብትሽ በሀብቴ’ የተባባልነው ስምምነታችን ይከበራ! በበፊቱ ዘመን ባል እንኳን እምቢ ቢል “ወደህ ነው፣ በቀበሌ ተገደህ!” ይባል ነበር፡፡ ይኸው እኔ እንኳን በቀበሌ ልገደድ ላባብላት ገና ቀረብ ስላት “ዋ! እምቢ ካልክ እሪ ብዬ መንደሩን ቀውጢ እንዳላደርገው” ትለኛለች፡፡
እናማ…ሚስት ተብዬዋን አንድ በሉልኝ!
ደግሞ አንዳንዴ በሆነ ነገር ላይ ጠበቅ አድርጌ ስከራከራት “ከአንተ ጋር እየተጨቃጨቅሁ ልጅነቴን አላሳጥርም…” ትለኛለች፡፡ አሁን እንዲህ ስትል ሰው ቢሰማን ምን ይላል! ከእኔ ጋር የዛሬ አሥራ አንድ ዓመት ስንጋባ እኮ… አምስት መሥሪያ ቤት ውስጥ የአስራ አራት ዓመት ሥራ ልምድ ነበራት፡፡ ይህ ደግሞ ሥራ ፍለጋ ያሳለፈቻቸው ዓመታት ሳይቆጠሩ ነው፡፡ አሁን ታዲያ “ልጅነቴን አላሳጥርም…” ብሎ ነገር ምንድነው! ደግሞ ሚስት ለባሏ ዘውድ ነች የሚለውን የተናገረውን ሰው ባገኘሁት፣ የምለውን አውቅ ነበር፡፡ እሱ ሰውዬ ወይ ሚስት አላገባም፣ ወይ ዘውድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቅም፡፡ የእኔ ሚስት እንኳን ዘውድ ልትሆንልኝ አናቴ ላይ እንደ ጂብራልታር አለት ተከምራብኛለች፡፡
እናማ…ሚስት ተብዬዋን አንድ በሉልኝ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4848 times