Monday, 30 May 2016 09:22

የፍትሕ ኤልኒኖ!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   ከብዙ የሃሳብ መንሸራሸር በኋላ የቢሮ ኃላፊው ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጡ፡፡ ‹‹ታውቃላችሁ? እኛ የምንነጋገረው የቢሮአችንን፣ የአገራችንን እንዲሁም የመንግስታችንን ጥቅም በሚያስከብር ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ይህቺ ሴት ለዚህ ቢሮም ሆነ ለአገራችን  እድገትና ትራንስፎርሜሽን የማታስፈልግ ናት ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ እሷ እኮ ሌላው ቢቀር ለመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንኳን ደንታ የሌላት፣ የአመለካከት ችግር ያለባትና ልማት አደናቃፊ ሴት ነች›› አሉ፡፡
ለዛሬው የጭንቅ አጀንዳቸው መንስኤዋ ኤፍራታ ይመር ናት፡፡ ኤፍራታ ቀውላላ ቁመት፣ ረጂም ጸጉር፣ ንጹህ ልብ፣ ብሩህ አዕምሮ የታደለች የ31 ዓመት ልጅ እግር ናት፡፡ እልኸኛ ከመሆኗ በተጨማሪ መበለጥን አብዝታ ትጠላለች፡፡ ተማሪ እያለች የምትናደደው በመሳሳቷ ሳይሆን በሌላ ተማሪ ከተበለጠች ነበር፡፡ ብዙ ማውራትም ሆነ ከወንዶች ጋር መቀለድ አትፈልግም፡፡ ከባሏም ጋር የተፋታችበት ምክንያት አቋም የሌለውና ልክስክስ መሆኑን በመረጃ ከደረሰችበት በኋላ ነበር፡፡ ትክክል አለመሆኑን ብታውቅም የስልክ ጥሪዎችን በመቅረጽም ሆነ ሰነዶችን ‹‹ኮፒ›› በማድረግ ማንም አይደርስባትም፡፡፡ የዛሬን ፍቅር ሳይሆን የነገን ማሰብ ይበጃል ትላለች፡፡ ሲበዛ ጠንቃቃና ለቃሏ ታማኝ ነች፡፡ ‹‹ክርስቶስን አደርገዋለሁ!›› ብላ የማለችበትን ነገር ሳታደርግ አታፈገፍግም፡፡
የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኤልያስ፤ቦርጩን እያሻሸ  ራሱን ከፍ ዝቅ በማድረግ በአድናቆት ጭምር የሀሳቡን ትክክለኝነት አረጋገጠ፡፡ የቢሮ ኃላፊው የሁሉንም ስሜት ለመረዳት ወደ ሌሎቹ አማተረ፡፡
የፋይናንስ አስተዳደሩም፤‹‹ልክ ነው›› ለማለት ራሱን ነቀነቀ፡፡ የግዢ አስተዳደሩ ጉሮሮውን ጠራርጎ፣ተንኮለኛ ዓይኑን እያጉረጠረጠ፤‹‹ልክ ነው›› አለ፡፡ ‹‹ግን ሴትዮዋ አደገኛ ናት፡፡ የሆነ ነገር ካልተደረገች ሌላ መዘዝ ማምጣቷ አይቀርም፡፡ መቼም ድርቅናዋንና ሐቀኝነቷን ሁላችንም እናውቀዋለን›› ብሎ ማብራራት ከጀመረ በኋላ፣ደጋፊዋ ነህ እንዳይባል ስለሰጋ መልሶ ተወው፡፡
የቢሮ ኃላፊው ቀብረር ብሎ፤‹‹ምንም አታመጣም አትስጉ፡፡ አሁን በተወያየንበት ጉዳይ  ከተስማማን፣ በተነጋገርነው መሰረት ቃለ-ጉባዔውን እንፈራረምበት፡፡ ከዚያም በኋላ በራሷ ወጥመድ ስትታነቅ ሁሉም ነገር ይገባታል፡፡ አይደለም ውሰጂ የተባለችውን ሲሳይ ይቅርና ኪስ ማውለቅ ትጀምራለች፡፡›› አለ የምጸት ሳቅ እየሳቀ፡፡ እነሱም አብረው ሳቁ፡፡
የቢሮ ኃላፊው ሲያወራ  ባያስቅም መሳቅ፣ ሳይገባቸው  የገባቸው ለመምሰል ራሳቸውን መነቅነቅ የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡
      የቢሮ ኃላፊው የፖለቲካ ሹም ከመሆኑም ባሻገር ብዙ ገንዘብ የሰበሰበ በመሆኑ በቅርበት የሚያውቁት ‹‹እጁ ረጂም ነው›› ይሉታል፡፡
 በየትኛውም መንገድ ቢመጡበት መውጫ ቀዳዳ አለማጣቱ ብቻ ሳይሆን ነገር አዋቂና የፈለገውን መጥቀም፣ የፈለገውን መጉዳት የሚችል ሰው በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ሌላው ልዩ የሚያደርገው ነገር በሚሊዮን ብር እያፈሰ በአካውንቱ ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ብር አለመገኘቱ ነው፡፡ በየትኛው አካውንት የትኛው ባንክ ያስገባው ወይም ቆፍሮ ይቅበረው፣ በውጪ ዓለም ባሉ ባንኮች ያሽሸው እስካሁን የሚታወቅ ምስጢር የለም፡፡
     ጉቦ ሲቀበልም በጣም ጠንቃቃ ከመሆኑ የተነሳ፣ የሚቀበለው በጥሬ ብር በሚያምነው ሰው አማካኝነት  ብቻ ነው፡፡ አለዚያም ለሆነ ሰው፣ በሆነ ስም፣ ከሆነ ሰው፣ ወደሆነ ሰው፣ ለሌላ ሰው፣ በሌላ ሰው ስም ይደርሰዋል እንጂ በቼክ ወይም በአካውንቱ ብር ፈጽሞ አይቀበልም፡፡
በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚፈርምበት አጋጣሚ ካለ፣ ስብሰባ ወይም ሌላ ምክንያት ፈጥሮ ወክሎ ይጠፋል፡፡ ሁሉንም ነገር በስልክ በወከለው ሰው አማካኝነት ‹‹ፈርምላቸው፤እንዲህ አድርገው…›› እያለ  በማስፈጸም ራሱን ነጻ ለማድረግ ሁሌም የተዘጋጀ  ክፉ ሰው ነው፡፡ ትልቁ  ብልጠቱ ደግሞ የሚገባውን ነገር ለሚገባው ሰው አለመንፈጉ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው የሚያደንቀው ግን ሁሉንም ቤተሰቦቹን ከድህነት አረንቋ ማውጣት የቻለ ጀግና በመሆኑ ነው፡፡ ዘመድ ቤተሰቡ ይቅርና ሰፈርተኛውም እንደ ዓይናቸው ብሌን ይጠነቀቁለታል፡፡ ተቸገርኩ ብሎ የመጣን ሰው አይመልስም፡፡ ማንን ይዞ ከማን ጋር መሥራት እንዳለበት ጠንቅቆ የሚያውቅ መሰሪ ነው፡፡  አሁን አሁንማ ሰዎች አሰራሩን ከእሱ የበለጠ የተረዱት ይመስላሉ፡፡
   ሁሉም የሥራ ኃላፊዎች ሀሳብ ከመስጠት ይልቅ የእሱን ሀሳብ በማድነቅ እንደ ወትሮው አጸደቁ፡፡ ቃለ ጉባዔውን እየተፈራረሙ ሳለ ምንም ሀሳብ ያልሰነዘረው፣ በዝምታው የሚታወቀው የሰው ኃይል አስተዳደሩ ዳውድ፤ ‹‹እእህ…›› አለ፡፡ የቢሮ ኃላፊው ስለሚረዳው እንጂ የተናገረ ሳይሆን ሽንት ቤት ሆኖ፣ “ሰው አለ” ያለ ነበር የሚመስለው፡፡
‹‹የምትጨምረው ሀሳብ አለህ እንዴ ዳውድ?›› አለው የቢሮ ኃላፊው፡፡ ዳውድም ምንም የገጽታ ለውጥ በፊቱ ሳይታይ፤‹‹ያው አሁን በተነጋገርነው በሁሉም ነገር እስማማለሁ፤ እፈርማለሁም፡፡  ነገር ግን እርሷ ቀድማ የሥራ መልቀቂያ አስገብታለች›› አለ፡፡
     የቢሮ ኃላፊው መብረቅ የመታው ያክል ደርቆ ቀረ፡፡ ሌሎቹም ንስር እንደወሰዳት ጫጩት ነፍሳቸው ለሰከንዶች ቀጥ አለ፡፡ ሁሉም ክው አሉ፡፡ እንደገና ተያዩ፡፡ እስካሁን ስላልነገራቸው ተናደዱ፡፡ ነገር ግን የእሱን ባህርይ አብጠርጥረው ስለሚያውቁ ለምን እስካሁን አልነገርከንም በማለት ጊዜያቸውን ማጥፋት አልፈለጉም፡፡ ከዚህ በፊት ብዙ  ነገርን ታቅፎ ሳይነግራቸው  በመቅረቱ ተጨቃጭቀዋል፡፡ ብዙ ጥቅማ ጥቅምም ማግኘት እያለበት ትተውታል፡፡ አይታረምም እንጂ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤም በተደጋጋሚ ተጽፎበታል፡፡ የሚገርመው ግን እስካሁን ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎቹ ምን እንደሚሉ አላነበባቸውም፡፡ የሚሰበሰበው ግዴታው ስለሆነ እንጂ ምንም ሳይናገር ስብሰባው የሚዘጋበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
‹‹እንዴት ሆኖ?›› አለ የቢሮ ኃላፊው፤ሁሉንም በአንዴ ለማየት እየሞከረ፤‹‹እኔ መጀመሪያም ያልኩት ይሄን ነው፡፡ ልትቀድመን አስባለች ማለት ነው›› አለ የግዢ አስተዳደሩ፡፡  
ሁሉም ሲደናገጡ ዳውድ ተረጋግቶ የሚሆነውን ይመለከታል፡፡ የሰው ኃይል አስተዳደር በመሆኑ ብዙ ነገሮች ይገጥሙታል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በንቀት ‹‹ከንቱ›› በማለት ያልፈዋል፡፡ በግዴለሽነት ብዙ ነገርን አሳልፏል፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ ማንም ይሁን ማንም፣ ምንም አይመስለውም፡፡ ‹‹አይ አላህ ተው ሰውን ክፉ አታድርገው›› ይላል አንዳንድ ጊዜ ሲመረቅን፡፡ ሥራ ሆኖበት እንጂ ከጫት ውጪ ከማንም ጋር ባያወራ ደስታውን አይችለውም፡፡ ለመማርም ሆነ ራሱን ለማሻሻል እንደ ሌሎቹ አይሯሯጥም፡፡ የቢሮ ኃላፊው ብዙ ስለማይጨቀጭቀው ብቻም ሳይሆን ቢቆፍሩትም ምስጢር ባለማውጣቱ ይደነቅበታል፡፡ የማንንም ቢሆን ለማንም አያወራም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሲያጋንኑለት፤‹‹የሰማውን ወሬ ለሰው ሊያወራ ቀርቶ ለራሱም ደግሞ አይናገርም›› ይሉታል፡፡ በእርግጥም እሱ ካለበት ሳይነቃነቅ ብዙ ኃላፊዎች ተቀያይረዋል፡፡ ስላለፉትም ሆነ አሁን ስላሉት የሚናገረው ስማቸውን ብቻ ነው፡፡
ካልቀጠርከኝ ብለው ከሚጣሉት ሰዎች በተጨማሪ የበላይ ኃላፊዎችና ዳይሬክተሮቹ ዘመዳቸውን እያመጡ ቅጠርልን ስለሚሉት አንጀቱ ብግን፤ድብን ይላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህን ሥራ ለቆ ለመሄድ ቢያስብም ሁሉም ቦታ ያው መሆኑን በመረዳቱ እየተጎዳ ይኖራል፡፡ ‹‹ሰው ክፉ›› ይላል  በዝምታው መሀል፡፡ መርቀን ብሎ ለሚወዳቸው እንደሚናገረው ከሆነ፣ ሁሉም መስሪያ ቤቶች በዚህ ጉዳይ አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንዱ በብሔር፣ አንዳንዱ በሀይማኖት፣ አንዳንዱ በጎሳ፣ አንዳንዱ በገንዘብ አለዚያም ጾታዊ ግንኙነት በማድረግ ቅጥር ይፈጸማል፡፡ ዳውድን የሚያናድደው ነገር ውድድር የሚባለው ከንቱ ልፋት ነው፡፡ ምንም እንኳን እሱም በሕጉ መሰረት ባይሰራም፣ ሁሌም ከራሱ ጋር እንደተካሰሰና እንደተዋቀሰ ይኖራል፡፡ ስንት የድሃ ልጅ እውቀቱን ተማምኖ፣ ስንት አገር አቋርጦ፣ ስንት ፍዳ ቀምሶ፣ ተቸግሮ፣ እየተራበ፣ ያልፍልኛል ብሎ እየተንከራተተ፣ ለይምሰል ማወዳደሩ በጣም ያናድደዋል፡፡ እንደውም ዳውድ በውድድር ጊዜ ከሩቅ አገር ያመለከቱትን አይደውልላቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ ተወዳዳሪዎቹ በዳውድ ላይ አንዳንዴ ቂም ይይዙበታል፡፡ እርሱ ግን ውስጡን ስለሚያውቅ እንዳይንከራተቱ  በማሰብ ነው፡፡  ዳውድ በትክክል ያለፈውን ሰው ትቶ፣ የቢሮ ኃላፊው ቅጠር ያለውን የሚቀጥርበት ጊዜ አለ፡፡ እንደውም ቅጥር ከተፈጸመ በኋላ ‹‹ለፎርማሊቲው ማስታወቂያ አውጣ›› የሚባልበት ጊዜ በጣም ብዙ ነው፡፡ ‹‹አይ አላህ ኧረ ተው ሰውን ክፉ አታድርገው›› ብሎ የታዘዘውን እየተቃጠለ ይፈጽማል፡፡ ማንም ግን ንዴቱን አያውቅበትም፡፡ ከአፉ ክፉ ቃል መናገርም ሆነ  ሰው በእሱ እንዲከፋ አይፈልግም፡፡
‹‹ታድያ ምን እናድርግ?›› አለ የቢሮ ኃላፊው፤ጭንቀቱ እንዳይታወቅበት እየጣረ፡፡
የህዝብ ግንኙነቱ ዳይሬክተሩ ኤልያስም፤‹‹የሆነ ምክንያት ተፈልጎ መታሰር ነው ያለባት፡፡ አለዚያ ሌላ ችግር ውስጥ ታስገባናለች፡፡ በተለይ የባለፈው ጨረታ ከተመረመረ ብዙ ችግሮች ይገኙብናል፡፡ ሁላችንም ሸቤ መግባታችን ነው›› ሸቤ የምትለዋን ቃል ከተናገረ በኋላ ከአፉ ስላመለጠችው ተጸጸተ፡፡ ግን ማናቸውም ቢሆኑ አጽንኦት አልሰጧትም፡፡ አሊያም አልገባቸውም ወይንም ደግሞ ቀድመው ተረድተውት ይሆናል፡፡
‹‹እንዴት? ምን ዓይነት ምክንያት እንፈልግላታለን?›› አለ የፋይናንስ ኃላፊው ከጭንቁ የሚገላገልበት ዘዴ ያገኘ ስለመሰለው አንገቱን አስግጎ፡፡
የግዢ ኃላፊው፤‹‹በእርግጥ ከፈለግን ማስወንጀያ አናጣም፡፡ እርሷ ተወክላ የፈረመቺበት ሰነድ ይኖራል፡፡ በዚያ ልናሳሥራት እንችላለን›› አለ፡፡
የፋይናንስ አስተዳደሩ እንደ መሳቅም እንደ መናደድም ብሎ፤ ‹‹እኔስ? ታዝዤ ነው የፈረምሁት ልበል? ወይስ ተሳስቼ ነው እንድል ትፈልጋለህ? ማንም ይፈርመው አግባብ ከሌለውና ችግር ካለበት እንደ ፋይናንስ አስተዳደርነቴ የማስቆም ኃላፊነት አለብኝ፡፡ እሱ ሌላ መዘዝ ነው፡፡ ሌላ መፍትሔ ካለህ ተናገር›› አለ በማያወላውል አቋም፡፡  
በሆነ ጊዜ የቢሮ ኃላፊው እየወከላት ብዙ ጊዜ ይጠፋ ነበር፡፡ በርከት ያለች ብር ከሆነች ስብሰባ፣ ስልጠና፣ መስክ እያለ በምክንያት  ወክሏት ይሰወር ነበር፡፡ ያኔም በስልክ ፈርሚላቸው ብሏት በስንት ጭቅጭቅ አሳምነዋት የፈረመቺው ሰነድ ስለነበር በዚያ ለመወንጀል ፈልገው ነበር፡፡ ያም ቢሆን እንዳማያዋጣቸው ተረድተዋል፡፡ ኤፍራታ መርዝ ስለሆነች መረጃ ይዛባቸው እንደሆነም ይጠራጠራሉ፡፡                  
የግዢ ኃላፊ፤‹‹ሌላ አማራጭ… አ…ለ! ለምን እንዳትሞት አድርገን በመኪና አናስገጫትም፡፡ ከዚያ እናሳክማታለን፣ እንከባከባታለን›› አለ፡፡
የሰው ኃይል አስተዳደሩ ዳውድ በድንገት፤‹‹ያረሱል አሚን ያለህ! ኧረ በጭራሽ ይህ የማይሆን ነው›› አለ፡፡ እንደ ዳውድ ሌሎቹም አይቃወሙ እንጂ ሁሉም ደግንጠዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ እነሱ በሙስና አልጨማለቅም ማለቷ እንጂ ባህሪይዋን፣ መልካምነቷን፣ በሥራዋ ያላትን ታማኝነትና ጥንካሬ፣ ከሁሉም በላይ ለአመነችበት ነገር ያላትን ጽናትና ክብር የቢሮ ኃላፊው ጭምር ያደንቁላታል፡፡ ይወዱላታልም፡፡ ምን ይደረግ? ወይ አትበላ ወይ አታስበላ!   
     ‹‹እና ምን ይሁን? እንደማይመለከትህ እጅህን አጣጥፈህ ዝም ትላለህ እንዴ? አደጋ ውስጥ እንዳለን ታውቃለህ አይደል? ከርቸሌ ከገባን ሁላችንም እንደምንገባ እወቁ፡፡ የምንፈራረማቸው ቃለ-ጉባዔዎች እስካልተፈተሹ ጊዜ ድረስ ነው ህጋዊ ሆነው የሚቀጥሉት፡፡ ከተመረመሩ ግን…›› አለው በእሷ ቦታ የተወከለው ምክትል ቢሮ ኃላፊው ዳውድን በቁጣ፡፡ በእሷ ቦታ የተወከለው አስመሳይና ተሽቆጥቋጭ ስለሆነ ነው እየተባለ ይታማል፡፡ ‹
‹ማንን ታሸንፋለህ ሲባል፣ ወደ ሚስቱ ሮጠ›› እንዲሉ አበው መሆኑ ነው፣ ዳውድ ላይ መጮሁ፡፡ ይህቺ ሹመት ከተሰጠችው በኋላ ተራ ሰራተኞችን ማናገር እያንገሸገሸው ነው፡፡የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኤልያስ፤‹‹ለምን እንዲህ አናደርግም፡፡ ሙስና አልበላም እያለች አይደል የምትመጻደቀው፣ የእኛ መዝገብ ቤቷ ልጅ ብድር አለብኝ ስትል ሰምቻለሁ፡፡ እዳሽን ክፈይ ብለን ልከናት ፎቶ እናነሳታለን፡፡ ከዚያም ፖሊሰ አሰማርተን ሙስና እየተቀበለች ነው ብለን ማሳሰር ነው፡፡ የመዝገብ ቤቷ ልጅ የተወሰነ ብር ከሰጠናት ለፍርድ ቤት ቃሏን እስከ መስጠት ትተባበረናለች፡፡ ምስክር ካስፈለገም ጓደኛዋን በገንዘብም፣በፍቅርም መቅረብ እንችላለን፡፡
ደመወዝ እንደሚጨመርለትና እድገት እንደሚሰጠው ተነግሮት፣በዚህ ኑሮ ውድነት እምቢ የሚል ሰራተኛ አይኖርም›› አለ ከሌሎቹ የተሻለ ብልህ ነኝ ብሎ ስለሚያስብ ዓይነ ዓይናቸውን እያየ፡፡ ሁሉም በየተራ  መፍትሄ የሚሉትን ሀሳብ አቀረቡ፡፡ በጸጥታ ሲከታተል የነበረው የቢሮ ኃላፊው ተናደደ፡፡ የአንዳቸውም ሃሳብ አላረካውም፡፡ ጉዳዩን ላያዳግም መቅበር ነው ፍላጎቱ፡፡ ‹‹ስንት አስቸጋሪና ውስብስብ ነገር እንዳላለፍን አንዲት እንከፍ ታስቸግረን!? በሽጉጥ  ነበር መድፋት፡፡ ብይ! ተጠቀሚ፣ ከሰው እኩል ሁኚ ስትባል እንቢ ትላለች? እሷ ብሎ የአገር ተቆርቋሪ፡፡ እንኳን እሷ ስንቶቹ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣንም ይመዘብራሉ፡፡
አዲስ ነገር ነው እንዴ? ቆይ አሳያታለሁ›› አለ ጠረጴዛውን በመደብደብ፡፡ ሲናደድ ግንባሩ ከመቆጣጠሩና ላቡ ግጥም ከማለቱ በላይ ዓይኑ በክፋት የተሞላች የተኩላ ዓይን ትመስላለች፡፡
     የቢሮ ኃላፊው፤‹‹በቃ ሁሉንም ለኔ ተውት›› ብሎ የስልኩን እጀታ አነሳ፡፡ ‹‹ዳውድ እቤቷ ወስደህ የምታስቀምጥልኝ ነገር አለ፡፡ ኤልያስ የባለፈውን ሰነድ እንድታመጣልኝ፡፡ አንተ ደግሞ ሰሞኑን ከእሷ ጋር ስለሚውለው ሰው ማንነት ሙሉ መረጃ እንድትነግረኝ እፈልጋለሁ፡፡
አንተኛው ፋይሎቹን በሙሉ ‹‹ኮፒ›› አድርግና በተነጋገርነው መሰረት እንደገና ሥራቸው፡፡ ሁላችሁም ተዘጋጁ፤የምነግራችሁንና የማዛችሁን ሰከንድ ሳታባክኑ፣ ሳትጠራጠሩ ማድረግ ነው፡፡ ምንም አታስቡ፤ስልጣኔን በአግባቡ የምጠቀምበት ሰዓት ይህ ነው›› አለ፡፡  ከዚያም በውል ወደሚያውቁት የደህንነት ሰው ጋ ስልክ ደውሎ፤ ስለ አክራሪነት፣ ሽብርተኝነትና ልማት አደናቃፊዎች ጥቂት ካወራ በኋላ በቢሮአቸው ውስጥ ስለተከሰተው ነገር ተገናኝተው ዝርዝሩን ማውራት እንዳለባቸው ተነጋግሮ ስልኩን ዘጋ፡፡ ሁሉም ተደናገጡ፡፡ አብዛኛዎቹ ነገሩ ወደ ሌላ እየተቀየረ መሆኑ ገባቸው፡፡
እውነትም እጀ ረጂም!! ‹‹እኔ የማደርገውን አሳያችኋለሁ፡፡ እድሜ ልኳን ትበሰብሳታለች፡፡
ሁላችሁም ለተልእኮው ተዘጋጁ፡፡ አንተ እንከፍ ደግሞ ስልክህን እንዳታጠፋ›› ብሎ  ምክትል ቢሮ ኃላፊውን ገላምጦት፣ ከእጁ የማትለየውን ጥቁር ቦርሳ አንጠልጥሎ ጥሎአቸው ወጣ፡፡ ሁሉም  ቆሌያቸው ተገፎ በዓይናቸው ሸኙት፡፡ ማንም ምንም ያለ አልነበረም፡፡ ጉዳዩ ከባድና የሁላቸውም እጅ እንደሚኖርበት ተገንዝበዋል፡፡ የቢሮ ኃላፊው ሁሉንም በማነካካት ለዘላለም በደም ተሳስረው እንዲኖሩ ማድረግን ያውቅበታል፡፡
 ማንም ከደሙ ንጹህ ነኝ ማለት አይችልም፡፡ ወደ ኋላ የሚያፈገግፍ ቢኖር የእሷ እጣ ፋንታ እንደሚደርስበትም አላጡትም፡፡ ዳውድ እንደ መሳቅ ብሎ የመጀመሪያው መልእክተኛ በመሆኑ እየተገረመ፤‹‹አሁን ከእኛ በላይ ልማት አደናቃፊ አለ!›› ሲል በምጸት ተናገረ፡፡
ከእርሱ በቀር ሁሉም ደንግጠው ስለነበረ የመለሰለት አልነበረም፡፡ ግዴለሽነቱ ከጭንቀት ቢያድነውም፣ከዚህ መ/ቤት በጊዜ ባለመልቀቁ መቆጨቱ አልቀረም፡፡
ሁሉም በየራሳቸው ዓለም በተቀመጡበት በሀሳብ ሰመጡ፡፡ “ዋ! ለኔ ….. ዋ! ለኔ…” የሚሉ ነፍሶች ተበራከቱ፡፡ ዳውድ ግን አሁን ወንድ መሆን እንዳለበት፤እንደተጫወቱበት የሚጫወትባቸው ጊዜ እንደደረሰ አሰበ፡፡ ‹‹ተጀመረ…!›› አለና በንቀት አይቷቸው፣እሱም ከቢሮው ወጣ፡፡ በድርቅ የተመታው የቢሮአቸው የፍትህ ኤልኒኖ፣ መከላከያው በእጆቹ ውስጥ ባሉት ዶሴዎች እንደሆነ እርግጠኛ ነበር፡፡  





Read 3391 times