Saturday, 28 May 2016 15:50

የጉራጊኛ ዘፈንን ለማዘመን የሚተጋው ድምጻዊ!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

በአንድ ወቅት አንድ ታዋቂ የትግርኛ ዘፋኝ፤“ትግርኛን ከእሽክርክሪት አወጣለሁ” ብሎ መናገሩን
አንድ ወዳጄ አውግቶኝ ነበር፡፡ የትግርኛንባህላዊ አጨፋፈር አዘምነዋለሁ ለማለት ፈልጎ ይመስለኛል፡፡ የዛሬው የአዲስ አድማስ እንግዳ፣የጉራጊኛ ዘፈን ድምጻዊው መላኩ ቢረዳን
ብዙዎች “ትዊስት በጉራጊኛ” በሚለው የበኩር አልበሙ ያውቁታል፡፡ መላኩም እንደ ትግርኛው
ዘፋኝ፣ ጉራጊኛውን የማዘመን ጥልቅፍላጎት አለው፡፡ እስካሁን ሂፕ ሆፕ፣ራፕ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ሙዚቃ ስልቶችን በጉራጊኛ የተጫወተ ሲሆን በተለይ በወጣቶች ዘንድ
ጥሩ ተቀባይነት ማግኘቱን ይናገራል፡፡ ለአድማጭ በደረሱ ሁለት የዘፈን አልበሞቹም ሁለትና ሶስት
በዘመናዊ ስልቶች የተጫወታቸውንየጉራጊኛ ዘፈኖች ማካተቱን ይገልጻል፡፡ “ጉራጊኛ ዘፈን መልዕክቱ ደስታም ይሁን ሃዘን ጭፈራው ዳንኪራ ነው፤ለምንድን ነው እንደ
ሌሎቹ አገርኛ ዘፈኖች፣በትዝታና አንቺ ሆዬ ስልት ቁጭ ተብሎ የሚደመጥ ሙዚቃ የማይሰራው?”
እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር የሚለው
ድምጻዊው፤በ2002 ያወጣው “ትዊስት በጉራጌ” ለራሱ ጥያቄ ምላሽ የሰጠበት የመጀመሪያ አልበሙ
ነው፡፡ሦስተኛ አልበሙን በቅርቡ እንደሚያወጣ የገለጸው አርቲስቱ፤የጉራጊኛ ሙዚቃን በማዘመን ለዓለም
አቀፍ አድማጭ የማድረስ ጥልቅ
ፍላጎት እንዳለው ይናገራል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ከድምጻዊ መላኩ ቢረዳ ጋር
ባደረገችው ቃለምልልስ፣ አስገራሚ
የልጅነት ህይወቱን፣እስከ ዩኒቨርሲቲ የዘለቀበት የትምህርት ትጋቱን፣የሙዚቃ ሙያውን---ወዘተ
በተመለከተ አነጋግራዋለች፡፡
ከትውልድ ቀዬህ ወደ አዲስ አበባ እንዴት መጣህ?
በትውልድ ቦታዬ የተሰባሰበ ቤተሰብ አልነበረኝም፡፡ ግማሹ በሞት፣ ግማሹ በስደት የተበታተነ
ቤተሰብ ውስጥ ስለነበርኩኝ፣ ለመማርም ለመኖርም አልተመቸኝም፡፡ የገጠር ልጅ ስትሆኚ ብዙ ጊዜ
እጣ ፈንታሽ ከብቶች መጠበቅና እንጨት መልቀም እንጂ የመማር እድል የለም፡፡ እኔም የአጐቴን
ከብቶች ስጠብቅ፣ እንጨት ስለቅም ነበር የኖርኩት፡፡ ት/ቤት ያስገቡኛል፤ችግሩ  ለስራ ሲፈልጉኝ
ያስቀሩኛል፡፡ እናም እድለኛ የሆኑ የአካባቢዬ ልጆች ትምህርታቸውን ሲማሩ ስመለከት በጣም
ይከፋኝና አዝን ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ በአጋጣሚ እጄ ላይ በነበረች 10 ብር፣ እንጨት ጭኖ ወደ
አዲስ አበባ በሚመጣ መኪና ተሳፍሬ፣ አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ ዋናው ጉጉቴ የአቅሜን እየሰራሁ
ለመማር ነበር፡፡ ታዲያ አዲስ አበባ እጇን ዘርግታ ተቀበለችህ ወይስ…?
አልተቀበለችኝም፡፡ ለጐዳና ህይወት ነው የተዳረግሁት፡፡ እውነት ለመናገር ስለ ጐዳና ህይወቴና
ስላሳለፍኩት ችግር በዝርዝር ለመናገር ጋዜጣውም ጊዜውም አይበቃም፡፡ ሆኖም በአራት አመታት
የጐዳና ላይ ኑሮ፣ በጣም የሚከብዱ አሳዛኝ ጊዜያትን እንዳሳለፍኩ ገልጬ ባልፍ ነው የሚሻለው፡፡
በዚያ ህይወት ማለፌ ብቻ ሳይሆን እሱን ማስታወስ እራሱ በጣም ከባድ ነው፡፡
በኋላ ግን ከጐዳና ህይወት ወጥተህ ትምህርት ጀመርክ አይደል? እንዴት ነው ከጐዳና ህይወት
የወጣኸው?ከጐዳና ለመውጣት በር የከተፈልኝን አጋጣሚ ልንገርሽ፡፡ አንድ ቀን ጐጃም በረንዳ አካባቢ ቁጭ
ብዬ፣ አንዲት ሴት እቃ ገዝተው በማዳበሪያ ከትተው ታክሲ ይጠብቃሉ፡፡ ኮልፌ ልኳንዳ ለመሄድ
ነው፡፡  ማዳበሪያው ውስጥ ሽንኩርት፣ ድንች፣ የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ ታክሲው ደግሞ ቆየባቸው፡፡
ሄድኩና እኔ ላድርሰው ስላቸው፣ “የምሄደው ሩቅ ቦታ ነው፤ በታክሲ ካልሆነ አትችለውም” ሲሉኝ፤
“ግዴለም አደርሰዋለሁ” አልኳቸው፡፡ ከዚያም በመሳለሚያ በእሳት አደጋው ጀርባ ሻንቅላ ወንዝ
የሚባል አለ፡፡ በዚያ በኩል እያቆራረጥን፣ እቃውን ተሸክሜ አንዳንድ ነገሮችን ከሴትዮዋ ጋር እያወራን ሄድን፡፡
“ጐዳና ላይ መሆን የለብህም፤ ወደ ቤተሰብህ መመለስ አለብህ” አሉኝ፡፡ እኔን በሀላፊነት ወስዶ
የሚያሳድገኝና የሚያስተምረኝ ቤተሰብ ስለሌለኝ ነው ወደ ጐዳና የወጣሁት ብዬ አስረዳኋቸው፡፡
እሳቸውም፤ “እኔ ስምንት ብር እሰጥሀለሁ፤በአራት ብር ስምንት ደብተር ገዝተህ፣እዚህ ኮልፌ ሰላም
በር ት/ቤት ግባ፤ እንደዚህ እየተሸከምክ ያገኘኸውን እየሰራህ ተማር፤እኔም አንዳንድ ነገር
አደርግልሃለሁ፤ ጠይቀኝ” ብለው ብሩን ሰጥተውኝ ተለያየን፡፡
እናም ትምህርቱን ጀመርክ? አዎ፤እዚያው ኮልፌ ኪቢአድ ፊት ለፊት፣ሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ደብተሮቼን ገዝቼ
ትምህርት ጀመርኩኝ፡፡ ት/ቤት የገባኸው ጐዳና እየኖርክ ነው?
ትምህርት ስጀምር ጐዳና ላይ ነበርኩኝ፡፡ ሆኖም ለአንድ ወር ያህል ጐዳና እያደርኩ ከተማርኩ
በኋላ የሌሎቹን ልጆች ንፅህና፣ ሁሉን ነገራቸውን ስመለከትና ከራሴ ጋር ሳወዳድር ትንሽ የስነልቦና
ችግር ውስጥ ገባሁ፡፡ ተማሪዎቹም የሚያሳድሩብኝ ተፅዕኖ ነበር፡፡ ከዚያም እንደምንም ብዬ ቤት
መከራየት አለብኝ ብዬ አሰብኩና፤ ቤት ስፈልግ እዚያው ኮልፌ ልኳንዶ አካባቢ በ30 ብር ትንሽዬ
ቤት አግኝቼ ተከራየሁ፡፡ የ15 ቀን 15 ብር ቅድሚያ ከፍዬ፣ ቀሪውን ለመክፈል ቃል ገብቼ መኖርም
መስራትም መማርም ቀጠልኩኝ፡፡ መስራት ጀመርኩ ስትል----ምን ዓይነት ሥራ?
መርካቶ ምዕራብ ሆቴል አካባቢ ፌስታል ማዞር ነው የጀመርኩት፡፡ ከዚያም ትንሽ ቀናት ሰራሁና
ቀሪውን 15 ብር የቤት ኪራይ ከፈልኩ፡፡
 የጐዳና ህይወቴ አብቅቶ፣ የቤት ኪራይ ህይወቴ እንዲህ ተጀመረ ማለት ነው፡፡ የዚያን ጊዜ
የምንማረው እንደሚታወቀው ግማሽ ቀን ነው፡፡ ግማሽ ቀን እየተማርኩ፣ ግማሽ ቀን ፌስታል
እያዞርኩ፣ ብቀጥልም ከፌስታል ሽያጭ የማገኘው ገቢ ለቤት ኪራይም ለቀለብም አልበቃ ሲለኝ፣
ከፌስታል ጋር ሎተሪ ማዞር ጨመርኩበት፡፡ ይሄም የተሻለ ገቢ ማምጣት ስላልቻለ፣ ምን አለሽ ተራ
ገብቼ ጫማ መስፋት፣ አሮጌ ጫማ እያጠቡ ማደስ፣ ቀለም መቀባትና የሊስትሮ ስራ ጀመርኩ፡፡
ከዚያ በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርቴን ቀጠልኩኝ፡፡ እስከ ስምንተኛ ክፍልም ደረስኩኝ፡፡ በነገራችን ላይ
ጐበዝ ተማሪም ነበርኩኝ፡፡ እዚያ አካባቢ በወቅቱ ሜሪ ጆይ የተራድኦና የልማት ድርጅት ነበር፡፡ ስለሚያውቁኝ የኮልፌ ቅርንጫፍ አባል ሆኜ፣ የደንብ ልብስና ጫማ መረዳት ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ ደግሞ የቁርስ፣ ምሳና እራት ድጋፍ እዚያው አካባቢ ከሚገኘው አማኑኤል ሆም የህፃናት ማሳደጊያ ከሚባል ድርጅት ማግኘት ጀመርኩኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከ8ኛ ወደ 9ኛ ክፍል ሳልፍ፣የፖሊስ ኦርኬስትራ በድምፃዊነት ቀጠሩኝ፡፡ እንዴት ድንገት ድምፃዊ ሆንክ? በፊት ታንጐራጉር ነበር? እኔ ከምማርበት ሰላም በር ት/ቤት ጀርባ፣ የፌደራል ፖሊስ (ፈጥኖ ደራሽ) የሙዚቃ ባንድ ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ ይህን እየሰማሁ አንጐራጉር ነበር፡፡ ሆኖም ቀጥታ ዘፋኝ አትሆኚም፤ እንደገባሽ መሰረታዊ የፖሊስ ወታደራዊ ስልጠና፣ የዲሲፕሊን ስልጠናና መሰል ግዳጆችን መወጣት ይጠበቅብሻል፡፡ እኔም በእነዚህ ሂደቶች አልፌያለሁ፡፡ መጀመሪያ ሀረር ውስጥ ሁርሶ ማሰልጠኛ ብቼ፣ስልጠናዎቼን ሁሉ ካጠናቀቅኩ በኋላ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገብቼ የተወሰነ ጊዜ ሰራሁኝ፡፡ ከዚያ ነው ወደ ሙዚቃ ክፍል የገባሁት፡፡ በአጠቃላይ በፖሊስ ውስጥ በሙዚቃም ሆነ በሌላው ዘርፍ ስድስት አመት ከሶስት ወር አገልግያለሁ፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ትምህርቴን ቀጥዬ፣
አስረኛ ክፍል በጣም አሪፍ ውጤት አመጣሁና ወደ መሰናዶ ገባሁ፡፡ አየር ጤና የመሰናዶ
ትምህርቴን አጠናቅቄ፣ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ መማር ጀመርኩ እልሻለሁ፡፡
ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ለመማር የመረጥክበት የተለየ ምክንያት ነበረህ? ለምንስ አቋረጥክው?
ነገሮች አልተመቻቹልኝም ነበር፡፡ በፊት ስማር ጐን ለጐን እሰራ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ጓዝሽን
ጠቅልለሽ ስትገቢ፣ ስራ የለም፤ ትምህርቱም ሙሉ ትኩረት ይጠይቃል፡፡ ሌላው ተማሪ በቤተሰቡ
እየተደገፈ ነው የሚማረው፡፡ እኔ ደግሞ ይህንን የሚያደርግልኝ አልነበረም፡፡ መልበስ አለ፡፡ ብዙ ብዙ ነገሮች ካልተሟሉ፣ ዩኒቨርሲቲው በሚሰጥሽ አልጋና ቀለብ ብቻ ተወስነሽ ለመማር ከባድ ነው፡ በዚህ ምክንያት ነው ያቆምኩት፡፡ አሁን ግን የመቀጠልና ጫፍ የማድረስ ጥልቅ ፍላጐት አለኝ፡፡ ፊልዱን የመረጥኩበት ምክንያት በተለይ በሙዚቃው ዘርፍ ምንም ስትሰሪ የሳውንድ ኢንጂነር እጥረት አለ፡፡ የሳውንድ ችግር አለ፡፡ እኔ ጥሩ ሳውንድ ኢንጂነር የመሆን ከፍተኛ ፍላጐት
ነበረኝ፡፡ ስለዚህ ወድጄው የምማረው ትምህርት ነበር፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እቀጥለዋለሁ፡፡
የመጀመሪያ አልበምህ “ትዊስት በጉራጌ” የተለየ ስልትን ይዞ በመምጣቱ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚያ ስልት ለምን አቀነቀንክ?
ከልጅነቴ ጀምሮ በጉራጊኛ ሙዚቃ ላይ ለውጥ እንዲመጣ አስብና እመኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ በጉራጊኛ ሙዚቃ ስለ እናት ወይም ስለ ችግርና ሀዘን እየተዘፈነ፣ ጭፈራው ግን ሁልጊዜ ዳንኪራ ነው፡፡ የሙዚቃው መልዕክትና የሙዚቃው ምት በፍፁም አይገናኙም፡፡ ይሄንን ነገር ውስጤ አይቀበለውም ነበር፡፡ ለምንድን ነው ጉራጊኛ ሙዚቃን እንደ ሌሎቹ አገርኛ ሙዚቃዎች መስራት የማይቻለው እያልኩ አስባለሁ፡፡ በተለይ የእነ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ የእነ ማዲንጐ አፈወርቅ፣ የእነ ጐሳዬ ተስፋዬ፣ የእነ ጋሽ ማህሙድ አህመድ፣ የእነ ጋሽ ጥላሁንና የእነ ኤሊያስ ተባባልን ስራዎች ሳዳምጥ በጣም
እመሰጣለሁ፡፡ የነዚህን ሰዎች ሙዚቃ በትዝታ መልክ፣ ሞቅ ባለ መልኩ ----- ብቻ በየትኛውም
ሁኔታ ላይ ሆኖ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ ጉራጊኛም እንደነዚህ ሙዚቃዎች ሰው መንገድ ላይ እየሄደ፣
ከስራ በኋላ አረፍ ብሎ ወይም አልጋ ላይ ጋደም ብሎ የሚያዳምጠው እንዲሆን በማሰብ፣ “ትዊስት
በጉራጌ”ን በ2002 ዓ.ም ሰራሁ፡፡   
ጉራጊኛ በትግርኛ ምት፣ በአንቺ ሆዬ፣ በጐንደር፣ በሱዳንኛ አድርጌ ተጫወትኩ፡፡ እንደ ሌሎቹ
ሙዚቃዎች ሰው ጋደም ብሎ፣ እየተራመደ፣ በማንኛውም መልኩ እንዲሰማው ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው የተለመደውን የጉራጊኛ ዘፈን ዎክ እያደረገ ሲያዳምጥ መንገድ ላይ ሊጨፍር
ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ አግባብ አይደለም፡፡ ለዚያ ነው በተለያየ መልኩ ለመስራት ያሰብኩት፡፡
ድምጻ ከተለመደው ውጭ አዲስ ነገርን ይዘው ሲመጡ የተለያዩ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል፡፡ አሳታሚ
ወይም ስፖንሰር ሊያጡ ይችላሉ፡፡ አንተስ ምን ገጠመህ?
እሱን መተው ይቀላል፡፡ ስፖንሰርማ ማንንም አላገኘሁም፡፡ የሚያሳትምልኝም አጥቼ ነበር፡፡ በተለይ
የጉራጊኛ ሙዚቃን በማሳተም የሚታወቁ ሙዚቃ ቤቶች፣“ህዝቡ ስለማይቀበለው አይሸጥልንም”
ብለው መልሰውኛል፡፡ ከረጅም ውጣ ውረድ በኋላ መቼ ተሳካልኝ መሰለሽ? በ2002 ላይ “ስታር”
ሙዚቃ ቤት በስራዬ ተማመነ፤ ወደደውና አሳተመልኝ፡፡ ውጤቱ እንደፈራሁት አልሆነም፡፡ ፈፅሞ
ከተጠበቀው ውጭ በጣም ተወዳጅነትን አገኘ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ አልበሙ ደግሞ
የመድረክ ስራዎችን፣ ኮንሰርቶችን፣ የውጭ ስራዎችን ጭምር ይዞልኝ መጣ፡፡ ብቻ ሁሉም በጊዜው
ጥሩ ሆነ፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን ወጣቱ በሙዚቃው ምን ይፈልጋል? የሚለውን በማየት ሂፕ ሆፕ፣
ራፕ፣ የአፍሪካ ሙዚቃ ስልቶችን በጉራጊኛ በመጫወት ጥሩ ተቀባይነትን አግኝቼበታለሁ፡፡ በቅርቡ
የሰራሁት “አማዶ” የተሰኘው ጉራጊኛ ራፕ አለው፤ ግን በጣም ተወድዷል፡፡
በጉራጊኛ ሙዚቃ ላይ ጥናታዊ ሙከራም (experiment) እያደረግህ ነው ማለት ነው?
ጉራጊኛ ማንነቱን ሳይለቅ፣መልዕክቱን አገርኛ ይዘቱን ሳያጣ፣ በየትኛውም ስልት ሊዘፈን
እንደሚችል ለማሳየት እየሞከርኩ ነው፡፡ እነዚህን ስልቶች የምዘፍነው ከዋናው ጉራጊኛ ዘፈኖቼ ጐን
ለጐን ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ አልበም ውስጥ ከሚካተቱ 13 ወይም 12 ዘፈኖች ስምንቱ ወይ ዘጠኙ
በትክክለኛው የጉራጊኛ ስልት ከተሰሩ፣ ሶስት አራቱን ሌሎች ስልቶችን በመጫወት ዓይነት
እንዲኖረው አደርጋለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ ስራዎቼ ደግሞ በሙሉ ባንድ የተሰሩ ናቸው፡፡
“አምባረኒ” በተሰኘው ሁለተኛ አልበምህ፤የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን፣ኢ-ፍትሀዊነትንና መሰል
ማህበራዊ ችግሮችን እያነሳህ የምትዘፍንበት ዜማ እንደዳሰስክበት ሰምቼአለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ
አጫውተኝ?
በሁለተኛው አልበሜ  የተሻለ ስራ ሰርቻለሁ ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ የህዝቡ ችግር ላይ
የሚያተኩሩ በርካታና ጠንካራ መልዕክቶችን አስተላልፌበታለሁ፤ በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለምሳሌ፣
እታች ያሉት ባለስልጣናት በሚፈጥሯቸው ችግሮች፣ ቢሮክራሲዎች፣ የመልካም አስተዳደር
ጉድለቶች፣ ኢ-ፍትሀዊነት ወዘተ መንግስት ይወቀስባቸዋል፡፡ ቀበሌ፣ ክ/ከተማ ለአንድ ጉዳይ
ስትሄጂ፣ የሚደርስብሽ መጉላላት መንግስትን እንድታማርሪ፣ አገርሽን እንድትጠይ ያደርግሻል፡፡
ይሆኑኛል ብለሽ እጅሽን አውጥተሽ የመረጥሻቸው አመራሮች፤መልሰው ያንቺ ጠላቶች ይሆናሉ፡፡
ይህንን በሙዚቃዎቼ እያነሳሁ ሞግቼበታለሁ፡፡
እነዚህ ችግሮች አንተ ደርሰውብህ አይተሃል?
እኔ ከጐዳና ልጆችና ከአረጋዊያን ጋር በተገናኘ በብዙ የበጐ አድራጐት ስራዎች ላይ ስለምሳተፍ
ከነዚህ ጋር በተያያዘ ጉዳዮችን ለማስፈፀም ብዙ ጊዜ ቀበሌ እሄዳለሁ፡፡ አንዷን ጉዳይ ለማስፈፀም
ከ15 እና ከ20 ቀን በላይ እመላለሳለሁ፡፡ ጉዳዩ እኮ ግማሽ ቀን የሚበቃው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን
ይህን ስመለከት ነው በሙያዬ እነዚህን ለመታገል የሞከርኩት፡፡ ግን ሁሉንም ሃላፊዎች
አይመለከትም፡፡ በዚህ አልበም የሀይማኖት መቻቻልን፣ ደካሞችንና አካል ጉዳተኞችን እንዲሁም
ወላጅ አልባ ህፃናትን ስለመደገፍም ዘፍኜአለሁ፡፡ በአጠቃላይ “አምባረኒ” ከተወሰኑ የፍቅር ዘፈኖች
በስተቀር በአብዛኛው የማህበረሰቡን ጉዳይ የዳሰስኩበት ነው፡፡
በዚህ አልበምህ ሳቢያ ያኮረፉ ወገኖች ነበሩ?
 እኔ የህብረተሰቡ አንድ አካል እንደመሆኔ የሚሰማኝን - የማስተውላቸውን ችግሮች ነው በሙዚቃ
ያነሳሁት፡፡ ይህን ተከትሎ ኮንሰርቶች ላይ እንዳልሳተፍ፣ የጉራጌ ልማት ማህበር ወይም ደግሞ
“ቤተ - ጉራጌ” በሚባለው ድርጅት ዝግጅቶች ላይ በሙያዬ እንዳልሳተፍ መከልከል ጀመርኩኝ፡፡
የተለየ አጀንዳ ያለኝ ተደርጌ፣ በእነዚህ አይነት ኮንሰርቶች ላይ እንዳልሳተፍ ከህዝብ የራቅኩበትም
ጊዜ ነበር፡፡ ሆኖም እኔ አልበሜን የጉራጌ ህዝብ ብቻ እንዲሰማው ሳይሆን የጉራጌን ሙዚቃ መላው
ዓለም እንዲሰማውና እንዲያውቀው እየጣርኩ ነው፡፡ እነዚያ አካላት ህገወጥ እገዳ ቢጥሉብኝም
ከተደማጭነት አላገደኝም፡፡ በዚህም ቅሬታና ቂም የለኝም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ ማለት
አልፈልግም፡፡ በተረፈ ግን የሚሰማኝን ከመግለጽ ወደ ኋላ የምልበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡
በቅርቡ ገቢው ለበጐ አድራጐት የሚውል አዲስ አልበም ሰርተህ ማጠናቀቅህን ሰምቻለሁ፡፡ ለምን
ዓይነት በጐ አድራጐት ነው ያሰብከው?
በነገራችን ላይ እንዲህ አደረግሁ፣ እንዲህ ሰራሁ ማለት አስፈላጊ ባይሆንም የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ
አልበሞቼም ሽያጫቸው ለበጐ ስራ ነው የዋለው፡፡ ሶስተኛውም እንግዲህ ለተመሳሳይ ዓላማ ታስቧል፡፡ “ጉርዳ” ወይም “አማዶዬ”፤ከሁለቱ አንዱ ርዕሱ ይሆናል፡፡ “ጉርዳ” ማለት ቃል ኪዳን ማለት ነው፤ከጥንት ጀምሮ የመጣ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህላችን፣ቃል ኪዳናችን ስለሆነ እናስቀጥለው የሚል መልዕክት አለው፡፡ “አማዶዬ” ማለት “ሰላም ነህ ወይ፤ድሮ ትቼህ የመጣሁት ህዝቤ? እንዴት ነህ?” የሚል መልዕክት አለው፡፡ አልበሙ ለፋሲካ እንዲደርስ ጥረት አድርጌ ነበር፤ ግን ዱባይ ለስራ ሄጄ ስለነበረና ስመጣም ከበጐ አድራጐት ጋር በተያያዘ ተደራራቢ ስራዎች ስለወጠሩኝ ለፋሲካ አልደረሰም፡፡ አሁን በዚህ ወር መጨረሻ ወይም በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ይወጣል፡፡ አልበሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታዋቂ አቀናባሪዎች፡- ለምሳሌ ዘሪሁን ሳህለማርያም፣ ማህመድ ኑር ሁሴን ዶክተሬ (መኮንን ለማ)፣ ቢኒ ባና፣ ጊልዶ ካሳ (የካሙዙ ካሳ ወንድም)፣ አስገኘው አሽኮ (ዲንዳሽ)፣ አሌክስ ይለፍና ሌሎችም ተሳትፈውበታል፡፡ 13 ዘፈኖችን ይዟል፡፡ ደስ የሚል፣ በሙሉ ባንድ የተሰራ አልበም ነው፤ በግጥምና በዜማ እኔን ጨምሮ ሌሎችም
ተሳትፈውበታል፡፡ ምን ያህል ወጪ አወጣህ ?
እስካሁን ከ250ሺህ ብር በላይ  ወጥቶበታል፡፡
ህዝቡ አልበሙን በመግዛት የኔንም ስራ ያዳምጣል፤ የተቸገሩትንም ይደግፋል ማለት ነው፡፡
ለየትኞቹ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ነው ገቢው የሚውለው?
ለሶስት ድርጅቶች ነው ያሰብኩት፡፡ አንደኛው አምባሳደር ሆኜ ለተመረጥኩበት “ክብር ለአረጋዊያን”
ምግባረ ሰናይ ድርጅት፣ ሁለተኛው “ሙዳይ” የምትባል የጎዳና ልጆችን ሰብስባ፣ ያለምንም ገቢ
የምታሳድግ፣ እጅግ በጣም ልትደግፍ የሚገባት ሴት አለች፤ ለእሷ በጎ አድራጎት ድርጅትና ሶስተኛ
“ጉርዳ” ነው፡፡ ቅድም እንደነገርኩሽ፤“ጉርዳ” ቃል ኪዳን ነው፤ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ወንድሞቻችን ያመጡት ሀሳብ ነው፡፡ ጉራጌ ውስጥ መስማትና ማየት የተሳናቸው ወገኖቻችን አሉ፡፡
እነዚህ ወገኖች በተለይ በጉራጌ ከፍተኛ መገለል ይደርስባቸዋልና በጉራጌ ዞን እንደብር ከተማ
ውስጥ አዳሪ ት/ቤት ለመገንባት እቅድ ተይዟል፡፡ አልበሙ ሶስተኛውን እርዳታ የሚያደርገው ለዚህ
ት/ቤት ግንባታ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እኔ በአቅሜ ይህን ካደረግሁ ለሌላውም መነሳሳት ይፈጥራል
ብዬ አምናለሁ፡፡  በተመሳሳይ ዓላማ በቅርቡ ኮንሰርት ለማቅረብ ማቀድህን ሰምቻለሁ…
አዎ አስቤያለሁ፡፡ ከሙያ ጓደኞቼ ጋር በመተባበር፣ኮንሰርቱን አቀርባለሁ ብያለሁ፡፡ ሂደቱ ተጀምሯል፡፡ ወጣቱ ለበጎ አድራጎት ስራ ልቡ ክፍት ስለሆነ፣ መጠነኛ መግቢያ አድርገን ገቢውን ለማሰባሰብ አስበናል፡፡ ቦታው የት ይሁን የሚለው ተወስኖ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይፋ ይደረጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በህይወቴ ድርሻ ያላቸውን ግለሰቦች፣ ያሳደገኝን የኮልፌ ልኳንዳ አካባቢ ህዝብ፣ በተለያየ ድጋፍ ለዚህ ያበቁኝን የሚዲያ ተቋማት… የእናንተንም ጭምር በጣም አመሰግናለሁ፡፡  



Read 1782 times