በአንድ የመንግሥት መ/ቤት 10 ተሽከርካሪዎች ሊብሬአቸው ሲገኝ መኪኖቹ የገቡበት አልታወቀም
በፌደራል መንግስት መ/ቤቶች ውስጥ ያለው የተሽከርካሪዎች አያያዝና አጠቃቀም ከፍተኛ ችግሮች እንዳሉበትና አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንደሚያስፈልገው ተገለፀ፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር፤ የመንግስት መ/ቤቶች የ2007 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ሪፖርትን ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት እንደተገለፀው፤ በፌደራል መንግስት ሥር በሚተዳደሩት የመንግስት መ/ቤቶች ላይ በተደረገ ፍተሻና ምርመራ በ32 መ/ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 313 ተሽከርካሪዎች የባለቤትነት ሊብሬ አልቀረበባቸውም፡፡ በ21 መ/ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 218 መኪኖች በብልሽት ምክንያት ቆመዋል፡፡ በአንድ መንግስታዊ ተቋም ውስጥ የሚገኙ 10 ተሽከርካሪዎች ሊብሬአቸው ብቻ ሲገኝ መኪኖቹ የገቡበት አለመታወቁም ተገልጿል፡፡
በስድስት መ/ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 15 ተሽከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸው መሆኑንና በ2 መ/ቤቶች ውስጥ የተገኙ 3 ተሽከርካሪዎች ደግሞ ሞተራቸው ተቀይሮ መገኘታቸው ተጠቁሟል፡፡
በፌደራል መንግስት መ/ቤቶች ላይ ያለውን የተሽከርካሪዎች አያያዝና አጠቃቀም ለማየት በተወሰኑ መንግስታዊ ተቋማት ላይ ፍተሻ ማካሄዱን የገለፀው የጠቅላይ ኦዲት ሪፖርቱ በአያያዝና አጠቃቀማቸው ላይ ጉድለት የተገኘባቸው መ/ቤቶች የእርምት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው፣ በብልሽት ምክንያት የቆሙትም ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የማያገለግሉት በመንግስት መመሪያ መሰረት እንዲወገዱ፣ ሊብሬ ያልቀረበላቸው መኪኖች እንዲመጣላቸው፣ በአካል ያልተገኙት ተሽከርካሪዎች ያሉበት ሁኔታ ተጣርቶ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡