Tuesday, 24 May 2016 08:20

‹‹ፍቅር - የሚቀራረቡ ሰዎች የጦርነት አውድማ ነው››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(4 votes)

       የዚህ ጽሑፍ ርዕስ ያደረግሁት የአንድ የማላስታውሰው ሰው ቃል፤ ትክክለኛ ሆኖ የታየኝ በኑዌር እና በዲንካ ብሔረሰቦች መካከል የሚታየውን ማህበራዊ ግንኙነት የሚያትት የኢቫንስ ፕሪትቻርድ ጥናትን ባነበብኩ ጊዜ ነው፡፡ ዲንካ እና ኑዌር በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ የኑዌር እና የዲንካ ብሔረሰቦች ኩታ ገጠም በሆነ ግዛት የሚኖሩ ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለት ብሔረሰቦች ያላቸው ግንኙነት ከፍተኛ የባላንጣነት ስሜት የሚንጸባርቅበት ነው፡፡ ይህ የባላንጣነት ግንኘኑነት የሚገለጠውም በጦርነት ነው፡፡ ሆኖም በርካታ ተመሳሳይ ነገሮች አሏቸው፡፡ በጉርብትና የሚኖሩ ሲሆኑ፤ በመሐላቸው ሌላ ‹‹ባዕድ›› እንዲገባም የሚፈቅዱ አይመስሉም፡፡ በጠላትነት የተዛመዱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ፕሪትቻርድ፤ እንዲህ ዓይነት ያልተለመደ ሁኔታ የተፈጠረበትን ምክንያት ይገልጻል፡፡ በሁለቱ ብሔረሰቦች ዘንድ እንዲህ ዓይነት ‹‹ዝምድና›› ሊፈጠር የቻለው፤ ኑዌሩ ያለ ህሊና ወቀሳ ለመዝረፍ የሚችለው የዲንካውን ከብት በመሆኑ ነው ይላል፡፡ በሌላ በኩል፤ ዲንካዎች ከብት እየነዱ የሚመጡ አርብቶ አደሮችን አምርረው ‹‹አትድረሱብኝ›› የሚሉ አለመሆናቸውን እንደ ተጨማሪ ምክንያት  የሚጠቅሰው ይህ አጥኚ፤ በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል በሚደረግ ተደጋጋሚ ጦርነት ሳቢያ በምርኮ የሚወሰዱ ሰዎች መኖራቸው እንደ ወገን የመተያየት ስሜት በመፍጠሩም ሊሆን ይችላል ይላል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ፤ ዲንካዎች ‹‹ሰማይ ከረጋ፤ ምድር ከተዘረጋ›› ጀምሮ የኑዌር ጠላት እንደሆኑ አሉ፡፡ በእርግጥ በባህልና በማህበራዊ ስርዓት ረገድ ሲታዩ፤ አንዱን ከሌላው ለመለየት ያስቸግራሉ፡፡ የአንደኛው ህዝብ አባል የሆነ ሰው፤ ያለ አንዳች ችግር የሌላኛውን ህዝብ ባህልጰ  ማህበራዊ ስርዓት ወርሶ ማንነቱን ቀይሮ ሊኖር ይችላል፡፡
በዲንካ ልማዳዊ የፖለቲካ ቡድንና በኑዌር ልማዳዊ የፖለቲካ ቡድን መካከል ዘወትር ተወጥሮጰ  ሚዛን ይዞ የሚኖር ቅራኔ አለ፡፡ ታዲያ ይህ የተወጠረ ቅራኔ ትንሽ ረገብ ብሎ ወዳጃዊ ግንኙነት ሲፀና፤ በግንኙነቱ ውስጥ የበላይ ሆነው የሚወጡት ኑዌሮች ናቸው፡፡ ታሪክ፣ ትውፊትና አፈ - ታሪክ ወደ ኋላ ሊወስዱን የሚችሉትን ያህል ወደ ኋላ ሄደን የሁለቱን ብሔረሰቦች ግንኙነት ብንመለከት፤ የምናስተውለው በጠላት ዓይን የመተያየትን ድርጊት ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ግጭት ከተፈጠረ፤ ምን ጊዜም ጥቃት ፈፃሚና ግጭት አጫሪ ሆነው የሚገኙት ኑዌሮች ናቸው፡፡ በኑዌሮች ዘንድ የኃይል ጥቃት በመሰንዘር የዲንካን ንብረት ለመዝረፍ መንቀሳቀስ እንደ መደበኛ የህይወት ክስተት የሚታይ ተግባር ነው፡፡ ታዲያ ይህን ድርጊት የሚያጠይቅ ወይም እና ተገቢ አድርጎ የሚያሳይ አፈ ታሪክ አለ፡፡ ይህ እንደ ኤሳው እና ያዕቆብ ያለ አፈ ታሪክ፤ ሁለቱም ወገኖች የሚያደርጉትን ነገር ተገቢ አድርገው በመውሰድ በሙሉ እምነት እንዲያደርጉት የሚያግዛቸው ነው፡፡
አፈ ታሪኩ እንደሚተርከው፤ ኑዌር እና ዲንካ የአንድ ፈጣሪ ሁለት ልጆች ናቸው፡፡ ፈጣሪ ያረጀችውን ላም ለዲንካ፤ የዚችን ላም ጥጃ ደግሞ ለኑዌር ለመስጠት ቃል ገባ፡፡ ከዚያ ዲንካ ጨለማን ተገን አድርጎ ወደ ፈጣሪ በረት ሄደ፡፡ እናም የኑዌርን ድምጽ በማስመሰል አታሎ ጥጃዋን ወሰደ፡፡ ታዲያ ፈጣሪ በዲንካ መታለሉን ሲረዳ በጣም ተቆጣ፡፡ ተናድዶም፤ ኑዌር በዲንካ ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ አዘዘ፡፡ ዲንካ በደል ፈጽሟልና እስከ ዘመን ፍፃሜ ድረስ፤ ኑዌር የዲንካን ከብት በመዝረፍ እንዲበቀለው አዘዘ፡፡
 ማንኛውም የኑዌር ህፃን ይህን አፈ - ታሪክ ሳለ ጀምሮ እየሰማው ነው የሚያድገው፡፡ ይህ አፈ - ታሪክ በሁለቱ ጎሳዎች መካክል የሚታየውን የፖለቲካ ግንኙነት የሚያንፀባርቅ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያም ተሻግሮ በሁለቱ ብሔረሰብ አባላት ዘንድ የሚንፀባረቅን ባህርይም መነሻ የሚገልጥም ነው፡፡ ኑዌሮች ጊዜ ጠብቀውና አስልተው ለከብት ዝርፊያ ወደ ዲንካ ግዛት ይዘምታሉ፡፡ ባህላዊ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው (አሁን ጠብመንጃ ሆኗል) ይዘው በግልጽ ለከብት ዘረፋ ይሰማራሉ፡፡ በተቃራኒው ዲንካዎች አድብተውና አዘናግተው ከብት ለመዝረፍ ይዘምታሉ፡፡ ታዋቂው አንትሮፖሎጂስቶች ኢቫንስ ፕሪትቻርድ፤ ‹‹ሁሉም ኑዌሮች ዲንካዎችን እንደ ሌባ ይመለከቷቸዋል፡፡ ዲንካዎችም ይህን የሚቀበሉት ይመስላሉ›› ይላል፡፡ አንድ የዲንካ አዛውንት ከአንድ አንትሮፖሎጂስት ጋር ሲወያዩ ከፍ ሲል የተጠቀሰውን አፈ - ታሪክ ተርከው፤ ‹‹ይኸውልህ እስከ ዛሬ ድረስ ዲንካ በመስረቅ፤ ኑዌር በጦርነት ይኖራል›› ማለታቸውን ፕሪትቻርድ በአንድ በጥናቱ አስፍሯል፡፡ አንድ የኑዌር ተወላጅ እንደ ከብት እርባታ ሥራው ዋነኛ ተግባሩ አድርጎ የሚመለከተው ወይም ስሜቱ ፍጹም የሚገዛለት ነገር ቢኖር ጦርነት ነው፡፡ የዲንካን ከብት ለመዝረፍ የሚደረግ ዘመቻ እንደ የትርፍ ሰዓት ሥራ የሚታይ ነው፡፡ አንድ የኑዌር ልጅ፤ ዲንካን ለመዝረፍ ዘመቻ የሚወጣ አባቱን ተከትሎ ጦርነት ለመሄድ የሚችልበት ጊዜ እስኪመጣ አብዝቶ ይናፍቃል፡፡ ለአቅመ አዳም እንደ ደረሰም፤ በጦርነት ጀግንነቱን አሳይቶ ዝናን ለማትረፍ፤ እንዲሁም ከብት በመዝረፍ ሐብቱን አብዝቶ ባለፀጋ ለመሆን ይመኛል፡፡ በኑዌር ውስጥ የሐብት መጠን ሰውን ትንሽ ወይም ትልቅ የማድረግ ውጤት ባይኖረውም፤ ለአቅመ አዳም የደረሰ ሁሉም ኑዌር፤ ጥቃት ሰንዝሮ ከብት ለመዝረፍ ዕቅድ መንደፍ ይጀምራል፡፡ አንድ ኑዌር ደፋር በመሆኑና በጦርነት ብቃቱ ይመካል፡፡ ዲንካውንም፤ ‹‹ሐሞት የለሽ›› ብሎ ይንቀዋል፡፡ በኑዌሮች ዘንድ የከብት ዝርፊያ የገድል ተግባር ነው፡፡ እያንዳንዱ ኑዌር ቢያንስ በየሁለት ወይም ሦስት ዓመቱ፤ ዘመቻ ወጥቶ የዲንካዎችን ከብት ይዘርፋል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የዲንካ አካባቢዎች በየዓመቱ የከብት ዝርፊያ ያጋጥማቸዋል፡፡ ታዲያ በዘረፋው አማካኝነት የተፈጠረው ጠላትነት ረገብ ሲል ግንኙነታቸው መልካም ገጽታ መያዝ ይጀምራል፡፡ ይህም በባህል መቀራረብና በእሴት ተመሳሳይነት የታጀበ ግንኙነት እንዲጠናከር አድርጓል፡፡ በዲንካና በኑዌር መካከል የሚደረግ ጦርነት በጥቅም ግጭት ሳቢያ ብቻ የሚከሰት ጦርነት አይደለም፡፡ ታሪካዊ ወይም ባህላዊ ግፊት ያለው ጦርነትም ነው፡፡ ይሁንና እንዲህ እየተጋጩ አንዱ ሌላውን የመቀበል ዝንባሌ ያሳያሉ፡፡ ይህን መዋቅራዊ ዝምድና በደንብ ያልተረዳ ሰው የግንኙነታቸውን ትርጉም ለመረዳት ይቸገራል፡፡ በኑዌርና በዲንካ መካከል በቀላሉ የመጎዳኘት ዝንባሌ ይታያል፡፡ አንዱ የሌላውን ልማድ የማክበር አዝማሚያም አላቸው፡፡ በመካከላቸው ያለው የባህል አካፋይ መስመር በጣም ጠባብ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹በጣም ስለሚመሳሰሉ፤ በጣም ይጣላሉ›› ለማለት የሚገፋፋ ሁኔታ ይታያል፡፡ ኑዌርና ዲንካ በጣም ስለሚቀራረቡ፤ በጣም ይገፋፋሉ፡፡ በጣም ስለሚናናቁ በጣም ይፈቃቀዳሉ፡፡ታዲያ እንዲህ ያለውን የፈናጅራ ሁኔታ ለመግለጽ የሚሞክሩ አጥኚዎች፤ ‹‹በጣም ከሚመስል ወገን ጋር የመጣላት ዝንባሌ›› በማለት ይደመድሙታል፡፡ እኔም በተውሶ ቃል፤ ‹‹ፍቅር፤ የሚቀራረቡ ሰዎች የጦርነት አውድማ ነው›› ብየዋለሁ፡፡ ይህን ሁኔታ ለማስረዳት የሚጠቅሱት ነገር አለ፡፡ በኑዌርና በዲንካ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን፤ በኑዌርና በሹሉክ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ያለው ልዩነት ሰፋ ይላል፡፡ እንዲሁም በኑዌርና በ‹‹ኮማ››፣ በ‹‹ቡሩን›› እንዲሁም በ‹‹ቦንጎ-ሚቱ›› ህዝቦች መካከል እጅግ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ሆኖም ዘወትር ግጭት የሚፈጠረው በኑዌርና በዲንካ መካከል ነው፡፡ ‹‹በጣም ከሚመስል ወገን ጋር የመጣላት ዝንባሌ›› ይኸ ነው፡፡
ይህ ችግር እየተባባሰ እንጂ እየተሻሸለ ሲመጣ አይታይም፡፡ እንዲያውም ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች እየተዳከሙ በመምጣታቸው፤ እንዲሁም በጦርነት ጊዜ እንኳን ሁለቱም ወገኖች የማይጥሷቸው የነበሩ ባህላዊ ገደቦች የሚጣሱበት ሁኔታ በመፈጠሩ፤ ጠንካራ ባህላዊ እሴቶችም እየተዳከሙ በመምጣታቸው፤ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳታፊ የሆነው ‹‹የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ጦር›› ኃይሎች በየጊዜው አንጃ እየፈጠሩ በመምጣታቸው፤ እንዲሁም ሌሎች የውጭ ኃይሎች ጣልቃ በመግባታቸውና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እንደ ልብ የሚገኝ በመሆኑ፤ በኑዌርና በዲንካ መካከል የሚፈጠረው ግጭት የሚያስከትለው ጉዳት እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ቀደም ሲል ሁለቱም ወገኖች ሴትና ህጻናትን መግደል፤ እንዲሁም የእህል ጎተራን ማቃጠል እርግማን እንደሚያመጣ መጥፎ ተግባር አድርገው ይመለከቱት ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ባህላዊ ድንበር በቦታው የለም፡፡ በዚህ ረገድ የታየው ለውጥ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ሣምንት ላጫውታችሁ፡፡          

Read 2764 times