Saturday, 21 May 2016 16:05

“መሀረቤን ያያችሁ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

“-- ስጋት አለን፡፡ ነገ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሳ በስምንት ኢንች ውፍረት ሊሠራ ታስቦ በምን ያህል ኢንች ውፍረት እንደተሠራ ያልታወቀው አንዱ የከተማ መንገድ ቢሰወርብንስ! ልክ ነዋ…ህንጻ ከጠፋ መንገድስ የማይጠፋበት ምን ምክንያት አለ! ቂ…ቂ..ቂ…”
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“መሀረቤን ያያችሁ…”
“አላ…የንም…”
“ህንጻዎቼን ያያችሁ…”
“አላ…የንም…”
“ሰማንያ ስምንቴን ያያችሁ…”
“አላ…የንም…”
የምር እኮ… አለ አይደል…ቂ…ቂ…ቂ… ለማለት እንኳን ተቸገርን! ሰማንያ ስምንት ህንጻ! “መሀረቤን ያያችሁ…” ነገር ሆነብን እኮ!
እኔ የምጠረጥረው ነገር አለ… የሆነ ፍለጋ ነገር ይካሄድልንማ! ልክ ነዋ…ከማርስ ወይም ከሌላ ፕላኔት የመጡ እነኛ ትናንሽ ‘አረንጓዴ’ ፍጡራን ተመሳስለው ሳይቀላቀሉን አልቀሩም፡፡ እናማ…እነሱ ተገኝተው ይጠየቁልን! እንደውም ‘ከማርስ የመጣን’ የምንመስል ሰዎች እየበዛን ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…  
ኮሚክ እኮ ነው…የቤታችን ግድግዳ ሁሉ ታልፎ ግንባራችን ላይ ያለች ቁንጫ እንኳን ትታያለች በሚባልበት ዘመን…ሰማንያ ስምንት ‘ዕንጣ!’ ይሄን ሰበር ዜና እነቢቢሲ ጭጭ ማለታቸው ያው የድሮ ምቀኝነታቸው መሆን አለበት፡፡
የ‘ሰማንያ ስምንቱ’ ጉዳይ “መሀረቤን ያያችሁ…” ሆነብንሳ!
ስማ አንተ የእንትን ሰፈሩ ወዳጄ… ያቺን ሚጢጢ ሰፈራችሁን ጠብቁ፡፡ ልክ ነዋ…ሰማንያ ስምንት ‘ዕንጣ’ የእናንተ አይነት አምስት ሰፈር ባይወጣቸው ነው!
የምር ግን እዚቹ አገር ብቻ የሚሆኑ…ሌላው ዓለም ላይ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ለ‘ዝንቅ’ የሚሆኑ መአት ነገሮች አሉ፡፡
የምር ኮሚክ እኮ ነው…በዛ ሰሞንም የቆጠራ ነው ምናምኑ ጊዜ ተገነባ የተባለው ይሄን ያህል ነው፣ ይሄን ያህሉ የት እንደገቡ አልታወቀም ምናምን ሲባል ነበር፡፡
የ‘ሰማንያ ስምንቱ’ ጉዳይ “መሀረቤን ያያችሁ…” ሆነብንሳ!
ስሙኝማ…የምር ይቺ አገር… አለ አይደል…የመደነቅ አቅም እስኪያንሰን ድረስ ‘ኢንተረስቲንግ’ እየሆነች ነው፡፡
ፈራንካው ይጠፋል…
ሰነዱ ይጠፋል…
ሰዉ ይጠፋል…
ሙሽራ ትጠፋለች…እንክት!
አሁን ደግሞ ህንጻዎቹ…ያውም ተሰባስበው… ይጥፉ! ጉልበተኛ በዛብንሳ…ህንጻዎችም ‘ያድሙብን’ ጀመር’ ቂ…ቂ…ቂ…
የ‘ሰማንያ ስምንቱ’ ጉዳይ “መሀረቤን ያያችሁ…” ሆነብንሳ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ሰማንያ ስምንት’ በየቤቱ ለሚፈጠረው ጭቅጭቅ አገልግሎት ላይ ስትውል ትታየኛለች፡፡
“ስማኝ እንጂ፣ ዊጌን እዚህ ላፕቶፕህ አጠገብ አድርጌው አልነበረም እንዴ!” ትለዋለች፡፡ እሱዬውም…
“ታዲያ ምን ሆነ ነው የምትዪው?” ይላል፡፡ እሷም…
“የት እንደገባ እንጃ…ጠፋብኝ ትልና ቤቱን ‘ትቀውጠዋለች፡፡ እሱ ደግሞ ዛራና ቻንድራን እያየ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አቦ አትረብሺ፣ እንኳን የአንቺ ዊግ ሰማንያ ስምንት ህንጻ ጠፍቷል!” አሪፍ አይደል!
(ስሙኝማ ‘ዛራና ቻንድራ’ን ካነሳን አይቀር… (የፊልሙ ዋናው ርዕስ ‘ሳራስዋቲቻንድራ’ ነው) ዛራን ሆና የምትጫወተው ጄኒፈር ዊንጌት በቀረጻ ወቅት አስቸጋሪ ነበረች ይባላል፡፡ የምትቀረጸው እሷ በፈለገችው ሰዓት ሲሆን ሌሎቹ የእሷን ፍላጎት መከተል አለባቸው፡፡ ካልመሰላትም ሳታስታውቅ ጭርሱን ትቀራለች አሉ፡፡ እኔ የምለው… አንዳንድ የአገራችንን አርቲስቶች ‘መክራብናለች’ እንዴ!)
እናላችሁ…የሰማንያ ስምንት ‘ዕንጣ’ መጥፋትን አይነት ‘ለሰሚ ግራ’ የሆነ ነገር እዚቹ እኛዋ አገር ካልሆነ የት ሊከሰት ይችላል!
የ‘ሰማንያ ስምንቱ’ ጉዳይ “መሀረቤን ያያችሁ…” ሆነብንሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ‘ሰማንያ ስምንት’ የሚለውን ቁጥር ስንጠቅስ ሆሊዉዶች እንዳይሰሙ ፍሩልንማ! አሀ…የአል ፓቺኖ ‘88 ሚኒትስ’ ፊልምን ርዕስ ወሰዱብን ብለው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቢገትሩንስ!
እነሱ ከሳሾቹ… “ተከሳሾቹ የአእምሮ ንብረት ጥበቃ ህግን በመተላለፍ ሰማንያ ስምንት የሚለውን የ‘88 ሚኒትስ’ ፊልም ርዕሳችንን ስለወሰዱብን ተገቢው ካሳ እንዲከፈለን ለተከበረው ፍርድ ቤት እናመለክታለን…”ዳኛውም የእምነት ክህደት ቃል ይጠይቃሉ፡፡
እኛ ተከሳሾች… “ክቡር ፍርድ ቤት፣ እኛ ሰማንያ ስምንት የሚለውን የተጠቀምነው የ‘88 ሚኒትስ’ ርዕስን ለመውሰድ ሆነ ብለን አስበንና አቅደን ሳይሆን ሰማንያ ስምንት ህንጻዎች በአንድ ጊዜ የገቡበት ስለጠፉብን እነሱን ለመጥቀስ ነው፡፡”
ይሄኔ ዳኛው ‘ፌይንት’ ያደርጉና ለኢመርጀንሲ ቅርብ ወዳለው ሆስፒታል ይወሰዳሉ፡፡
በመንገድ ላይም…ዘመዶቻቸው ምን ብለው ይጸልዩ መሰላችሁ… “ብቻ ሆስፒታሉ ከቦታው ጠፍቶ እንዳይጠብቀን!” ቂ…ቂ…ቂ…
መስሪያ ቤት ነው፡፡  እናላችሁ አንድ ‘ተቆርቋሪ ዜጋ’ ሀሳብ ያቀርባል…
“መስሪያ ቤቱ ጓሩ ሀያ ሁለት መኪኖች ቆመው ነበር፡፡ ከእነዚህ መሀል ሁለቱ ጠፍተዋል፡፡ ስለሆነም በአስቸኳይ ኮሚቴ ተቋቁሞ የት እንደደረሱ ምርመራ ይካሄድ፡፡”
እናላችሁ…የጠቅላላ አግልግሎት ሀላፊው መልስ ይሰጣል…
“ሰማንያ ስምንት ህንጻ በሚጠፋበት አገር ሁለት መኪኖች ጠፉ ተብሎ በዚህ በተከበረ ስብሰባ ላይ ማንሳት የስብሰባውን መንፈስ የሚያውክና ውሃ የማያነሳ ነው፡፡”  ቂ…ቂ…ቂ..
እሷና እሱ ይጣላሉ…
“አንቺ ሴትዮ…ዋ በኋላ ነግሬሻለሁ!”
“ምን እንዳታመጣ ነው!”
“ዋ…እንደ ሰማንያ ስምንቱ ህንጻዎች ድራሽሽን እንዳላጠፋው!” ቂ…ቂ…ቂ…
የ‘ሰማንያ ስምንቱ’ ጉዳይ “መሀረቤን ያያችሁ…” ሆነብንሳ!
ስጋት አለን፡፡ ነገ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሳ በስምንት ኢንች ውፍረት ሊሠራ ታስቦ በምን ያህል ኢንች ውፍረት እንደተሠራ ያልታወቀው አንዱ የከተማ መንገድ ቢሰወርብንስ! ልክ ነዋ…ህንጻ ከጠፋ መንገድስ የማይጠፋበት ምን ምክንያት አለ! ቂ…ቂ..ቂ…
ለ‘ፈረንጆቹ’ ጥቆማ አለን…ህንጻዎችን ማፈራረስ ሲፈልጉ በፈንጂ ምናምን የሚያደርጉት የድምጽና የአየር መበከል ሊያስከትል ስለሚችል የእኛን ድጋፍ ቢጠይቁ አሪፍ ነው፡፡
አሀ…ደማሚት የለ፣ ቡልዶዘር የለ፣ ክሬን ቅብጥርስዮ የለ…በቃ የፈለጉትን ያህል ህንጻ ‘እንሰውርላቸዋለን፡፡’  ቂ…ቂ…ቂ…
ሀሳብ አለን…ሰማንያ ስምንት የሚለው ቁጥር በታሪካዊነት ይመዝገብልን፡፡ እንደ ሰገሌ ዘመቻ ምናምን ---- ማጣቀሻ ሊሆን ይችላላ!
“አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ዙሪያ ባጃጅ የሚባሉ ትናንሽ መኪና የሚመስሉ ማጓጓዣዎች ነበሩ…”
“ስለ መቼ ነው የምታወራው?”
“ያን ጊዜ እንኳን ሰማንያ ስምንቱ ህንጻዎች የተሰወሩ ጊዜ…” አሪፍ ማጣቀሻ አይደል!
የ‘ሰማንያ ስምንቱ’ ጉዳይ “መሀረቤን ያያችሁ…” ሆነብንሳ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7849 times