Saturday, 21 May 2016 14:48

በገርጂ ወረገኑ ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት ግጭት ሰዎች ተጐድተዋል

Written by 
Rate this item
(21 votes)

• ከ2 ሺህ በላይ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑ ታውቋል
• ግጭቱን ተከትሎ ለ3 ቀናት ት/ቤቶች ተዘግተዋል

    በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ገርጂ ወረገኑ በተባለ አካባቢ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ ተገንብተዋል የተባሉ ቤቶችን ለማፍረስ በተሰማራ የደንብ ማስከበር ግብረ ኃይልና በነዋሪዎች መካከል  ውዝግብ ተነስቶ ከፖሊስ ጋር በተከሰተ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በግርግሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ሲናገሩ የፖሊስ ምንጮች በበኩላቸው፤ 3 ፖሊሶችን ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ከመድረሱ በቀር የሞተ ሰው ስለመኖሩ አልተረጋገጠም ብለዋል፡፡ የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታልም ከግርግሩ ጋር በተገናኘ ያስተናገደው አስክሬን አለመኖሩን አስታውቋል፡፡ በቦታው ላይ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተሰሩ ናቸው ያላቸውን ከ2 ሺህ በላይ ቤቶች ለይቶ በማፍረስ ላይ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ኃላፊዎች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ “ከገበሬው ላይ በውድ ዋጋ የገዛነው መሬት ላይ ጥሪታችንን አሟጠን የሰራነው ቤታችን አማራጭ ሳይሰጠን በኃይል በመፍረሱ ሜዳ ላይ ተበትነናል” ሲሉ አማረዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ ኃይሎች ከአፍራሽ ግብረ ኃይሉ ጋር በመሆን ቤቶቹን ማፍረስ መጀመራቸውን የሚገልፁት ተጎጂዎቹ፤ በኃይል እቃችንን እንድናወጣ ከተደረገ በኋላ በ7 የመቆፈሪያ ከባድ ማሽኖች (ስካቬተሮች) ቤቶቹን ማፍረስ ጀመሩ ይላሉ፡፡ እስከ ትናንት ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች መፍረሳቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ የቤቶቹን ፍራሽ፣ ቆርቆሮዎችን ጨምሮ በደንብ ማስከበሮች ተጭኖ ተወስዷል ብለዋል፡፡ በነዋሪዎችና በፖሊስ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎም ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ በሚኖርበት በዚህ አካባቢ ከረቡዕ ጀምሮ መንቀሳቀስና ከቤት መውጣት የሚቻል ባለመሆኑ ለ3 ቀናት ት/ቤቶች መዘጋታቸውንና ትምህርት መቋረጡን ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ውዝግብ ከባድ የመሳሪያ ተኩስ እንደነበር የጠቀሱት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ አምቡላንሶች የተጎዱ ሰዎችን ሲያመላልሱ እንደዋሉ ያስታውሳሉ፡፡ ምንጮቻችን፤ ከቤት መውጣት ባለመቻላችን እስከ 12 ሰው መሞቱን ከመስማታችን በቀር ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉ ሲሆን የከተማዋ ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ም/ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተሰማ ነጋሽ በበኩላቸው፤ “ፖሊስ ላይ መጠነኛ ድንጋይ ከመወርወሩ በቀር የተባለውን ያህል ጉዳት አልደረሰም፣ ጉዳት ደረሰብኝ ያለ አካልም የለም” ብለዋል፡፡
ቤታቸው እየፈረሰባቸው መሆኑን ለአዲስ አድማስ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ አብዛኞቹ በቀን ሰራተኝነት የሚተዳደሩ ሲሆን ከገበሬው ላይ ከ50-100 ካሬ ሜትር ቦታ፣ አንዱን ካሬ ሜትር እስከ 1500 ብር ሂሳብ እየገዙ፣ ከ20-30 ቆርቆሮዎችን የፈጁ ቤቶችን ቀልሰው ሲኖሩ እንደ ነበር ገልፀዋል፡፡ አካባቢው መሰረተ ልማት ያልተሟላለት መሆኑን የሚጠቅሱት ነዋሪዎቹ፤ “ከዛሬ 6 እና 7 አመታት በፊት ቦታውን ገዝተን ቤት ስንሰራ ወረዳውም ሆነ ክ/ከተማው ህገወጥ ናችሁ አላሉንም ነበር” ሲሉ ያማርራሉ፡፡ የቀን ስራ ሠርተን ያጠራቀምነውን ገንዘባችንን በቦታ ግዢና በቤት ግንባታው ላይ ካዋልንና ተረጋግተን መኖር ከጀመርን በኋላ መንግስት ቤታችንን ማፍረሱ ተስፋ-ቢስ አድርጐናል የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ መውደቂያ አጥተን ከነቤተሰባችን ሜዳ ላይ ተበትነናል ብለዋል፡፡
የወረዳው የስራ ኃላፊዎች ባለፈው ሚያዚያ 1 ቀን 2008 ዓ.ም በቦታው ተገኝተው ቤቶቹ ህገ - ወጥ መሆናቸውን ሲነግሩን እንዳያፈርሱብን ብንማፀንም አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡንም ነበር ያሉት ቅሩታ አቅራቢዎቹ፤ እንዳልሰጧቸውና ባለፈው ረቡዕ በድንገት ቤቶቹን ማፍረሣቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ቤቶቹ በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተገነቡ በመሆኑ ህጉን ተከትዬ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል፡፡ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ም/ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተሠማ፤ ከ2ሺህ በላይ ቤቶች በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተሠሩ ሆነው በመገኘታቸው እንደሚፈርሱና በቀጣይም ተጨማሪ ህገ-ወጥ ቤቶችን የመለየት ስራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በህገ መንግስቱ መሬት መሸጥ መለወጥ እንደማይቻል የጠቀሱት ኮማንደሩ፤ ግለሰቦቹ በየትኛውም ህግና ደንብ ህገ-ወጥ ናቸው ይላሉ፡፡ ህጋዊ መሆን የሚችሉበት መንገድም እንደሌለ አክለው ገልፀዋል፡፡  


Read 8392 times