Saturday, 21 May 2016 14:48

በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ረብሻ ተቀሰቀሰ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(17 votes)

   በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ረቡዕ የተቀሰቀሰው ረብሻ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ቬተርናሪ እና IOT ካምፓሶች የተጀመረው ረብሻ ወደ ዋናው ካምፓስ ተሸጋግሮ፣ ተማሪዎች የመማሪያ ክፍሎችንና በግቢው ውስጥ የሚገኙ ህንፃዎችን መስታወቶች በድንጋይ እየሰባበሩ ነው፡፡  ከዩኒቨርሲቲው ምንጮቻችን ባገኘነው መረጃ መሰረት፤ ባለፈው ረቡዕ ተማሪዎች ለጥያቄዎቻችን ምላሽ እንሻለን በሚል ምክንያት የቀሰቀሱት ረብሻ በዩኒቨርሲቲው በሚገኙ ሁሉም ካምፓሶች ተዳርሶ ረብሻው እንደቀጠለ ታውቋል፡፡ በረብሻው ወቅት ከየት እንደመጣ  ያልታወቀ ቦምብ ፈንድቶ ፍንጥርጣሪው በተማሪዎች ላይ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት ተማሪዎቹ በህክምና ተቋማት ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ምንጮቻችን ጠቁመውናል፡፡ በጉዳቱ ህይወቱ ያለፈ ሰው ባይኖርም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች እንዳሉ እነዚሁ ምንጮች ገልፀውልናል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ትግሉ መለሰ እንደገለፁልን፤ በዩኒቨርሲቲው፤ ካለፈው እሮብ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ረብሻ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ጠቁመው የረብሻው መነሻ ምክንያት ግን እስካሁን አለመታወቁን ገልፀዋል፡፡ ተማሪዎቹ ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ በኦሮሚያ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ ለተቀሰቀሰው ረብሻ ጥያቄያቸው በመንግስት ምላሽ በማግኘቱ  ተቋርጦ የነበረ ሲሆን አሁን በድጋሚ ረብሻ ለመቀስቀስ የሚያስችል አንዳችም ምክንያት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች ላይ ምንም አይነት የኃይል እርምጃ አለመውሰዱንም አቶ ትግሉ ገልፀዋል፡፡
በቦንብ ፍንዳታው ሳቢያ በተማሪዎቹ ላይ ደረሰ ስለተባለው ጉዳት ጠይቀናቸው፤ “ይኼ ዩኒቨርሲቲውን የሚመለከት አይደለም፤ የፀጥታ ኃይሎችን ጠይቁ፡፡ በቦንብ ፍንጣሪው ግን አደጋ የደረሰው በአንድ ተማሪ ላይ ብቻ ነው እሱም የከፋ ጉዳት አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ከመምህራንና ከተማሪዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት የፅ/ቤት ኃላፊው፤ ረብሻው የከፋ ችግርና ጉዳት ሳያስከትል እንዲቆም ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀው ይህም ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡  


Read 6280 times