Saturday, 25 February 2012 14:17

3ቱ ወሳኝ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በቀጣይ ሳምንት የአዲስ አበባ ስታድዬም ብሄራዊ ቡድኑና ክለቦች በሚያደርጓቸው 3 የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች ሊደምቅ ነው፡፡ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ማጣሪያ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተፈጠረው የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መደራረብ በተጨዋቾች ምርጫ ችግር ውስጥ ቢገባም በሜዳው ከቤኒን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በአሳማኝ ውጤት ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድድሮች የቅድመ ማጣርያ ተሳትፏቸውን ከሜዳ ውጭ ከሳምንት በፊት የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መጀመርያ ዙር ማጣርያ ለመግባት ወሳኝ ፍልሚያቸውን በአዲስ አበባ ያደርጋሉ፡፡ በተያያዘ በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮናና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክለው የሚጫወቱት ክለቦች ያስመዘገቡት ውጤት አበረታች ነው በሚለው መግለጫው የኢ.እግ.ፌ. ለመልሱ ጨዋታዎች የመላው የስፖርት ቤተሰቡን ድጋፍ ጠይቋል፡፡

ሁለቱም ክለቦች ሀገራችንን በመወከል በአፍሪካ የክለቦች ውድድሮች የሚሳተፉ በመሆኑ መላ የስፖርት ቤተሰቡ በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ክለቦቹ የሚያደርጉትን ጥረት ማበረታታት  እንደሚገባ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ግጥሚያውን ወደ ኮሞሮስ በመጓዝ ከኪዮን ኖርድ የተጋጠመው ኢትዮጵያ ቡና 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፏል፡፡ በሌላ በኩል በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ የጋቦኑን ያንጋ ስፖርት 1-0 አሸንፏል፡፡ለቅዱስ ጊዮርጊስ የአሸናፊነት ጎሉን ያስቆጠረው አዳነ ግርማ ነው፡፡ሁለቱ ቡድኖች በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታቸው ቡና 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት በመሸነፉና ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ 1ለ0 ተጋጣሚውን በመርታቱ በሜዳቸው በሚያደርጓቸው የመልስ ጨዋታዎች አሸንፈው ወደ ቀጣዩ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለማለፍ ሰፊ እድል ይኖራቸዋል፡፡  በሌላ በኩል ቤኒን ከሳምንት በፊት ቀድሞ የፈረንሳይ አጥቂ ተጨዋች የነበሩትን የ50 ዓመቱን ማኑዌል አሞሮስ ለ2 ዓመት ብሄራዊ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ሾሟል፡፡ የ34 ዓመቱ አሰልጣኝ ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር በ1984 እኤአ ላይ የአውሮፓ ዋንጫን ያገኙ ሲሆን በሁለት የዓለም ዋንጫዎች ተሳታፊ የነበሩ ናቸው፡፡

አሞሮስ ከቤኒን ሃላፊነታቸው   2 ዓመት በፊት የኮሞሮስ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠኑ ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታቸውን እዚህ አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረግ ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ አህጉራዊ ፉክከሩን በብሄራዊ ቡድን ከቤኒን ጋር በክለቦች ደግሞ ከአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ጋቦንና ከኮሞሮስ ተወካይ ክለብ ጋር ተፋጥጧል፡፡ ከአራቱ አገራት በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ በ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየችው ጋቦን እጅግ ርቃ ሄዳለች፡፡ ደካማዋ ኮሞሮስ ናት፡፡ ቤኒን ደረጃዋ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ነው፡፡ ይህም ከተጋሚዎች ከባዱ ግጥሚያ ለጊዮርጊስ ያደርገዋል፡፡ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ አሸንፎ የመጣው ክለብ የጋቦም መሆኑ የክለቡ ጥንካሬና ተጨዋቾቹ ምን ያህል ለብሄራዊ ቡድኑ እንደሚያስፈልጉ ያሳያል፡፡

 

በፊፋ መረጃ

ኢትዮጵያና ቤኒን

የተጨዋቾች ብዛት 3,474,245 ፤320600

የተመዘገቡ 56,245   ፤ 7800

ክለቦች 1,004 ፤ 110

ባለሙያዎች 310,600 ፤ 1700

በፊፋ ያለፈው አንድ አመት አማካይና ወቅታዊ ደረጃ

ኢትዮጵያ 132.846፤  137

ቤኒን 100.769 ፤ 136

ጋቦን 65.462፤  45

ኮሞሮስ 183 ፤ 188

 

 

Read 2435 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 14:20