Saturday, 14 May 2016 11:56

ዘንድሮ 1.5 ሚ. ኢትዮጵያውያን ለድንገተኛ አደጋዎች ይጋለጣሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

    መነሻውን ከምስራቃዊው የአገሪቴ ክፍል ባደረገውና በቀጣይነት መላውን የአገሪቱን አካባቢዎች ያዳርሳል በተባለው የጎርፍና ሌሎች ቅፅበታዊ የተፈጥሮ አደጋዎች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ተጋላጭ ናቸው ተባለ። በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ እስካን ከ100 በላይ ዜጎች ህይወታቸው አልፏል፡፡
የአማራ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ለአደጋው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የብሔራዊ አደጋ መከላከል ብሔራዊ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ፤ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎችን በዘላቂነት ሰላማዊ ወደሆኑ አካባቢዎች ለማዛወር እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የጎርፍና የመሬት ናዳ አደጋዎች በደረሱባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን በፕላስቲክ መጠለያ ውስጥ ለማስፈር ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች የምግብና ጊዜያዊ የመጠለያ እርዳታዎች እየተደረጉ እንደሆነ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ ዝናቡ ባለማቋረጡ ምክንያት የእርዳታ አሰጣጡ ላይ ችግር መፈጠሩንና ጎርፍ የተረጂዎችን ምግብና አልባሳት ጠራርጎ እንደወሰደው ጠቁመው ተጎጂዎቹ በሚደረግላቸው እርዳታ መጠቀም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ደሴ፣ ወልዲያ፣ ሸዋሮቢት ጣና ዙሪያ፣ በኦሮሚያ ክልል በተለይም ከአዋሽ ተፋሰስ ጋር ያሉ እንደ ዝዋይና መቂ ያሉት አካባቢዎች፣ ከደቡብ ክልል ጎሞጎፋ ዞን፣ ወላይታ ሃዲያ፣ ስልጤ፣ ሲዳማ ዞን፣ ሐዋሳ ዙሪያ፣ ከትግራይ ክልል አላማጣና አካባቢው እንዲሁም ከአፋር ክልል አሚባራ፣ ዱቢቲ፣ አዳይቱና ሚሎ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡
ሰሞኑን በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በተከሰተው የጎርፍና የመሬት ናዳ እስካሁን 39 የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን በናዳው የተቀበሩ ሰዎችን የማፈላለግ ሂደቱ እንደቀጠለ ታውቋል፡፡ በሥፍራው ከሚገኙ ምንጮች ባገኘነው መረጃ መሰረት፤ በወላይታ ዞን ኪንዶዳ ዲዬ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ሰሞኑን እየጣለ በሚገኘው ከባድ ዝናብና በዚሁ ሳቢያ በተከሰተ የመሬት ናዳ ምክንያት የሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን ወላይታን ከዳውሮ ዞን የሚያገናኘው መንገድ በጎርፍ ተሰብሯል፡፡ የወላይታ ዞንን ከሲዳሞ ዞን ጋር የሚያገናኘው ትልቅ ድልድይም በብላቴ ወንዝ ተወስዷል፡፡ በአደጋው ከ135 በላይ ቤቶች በጎርፍ በመወሰዳቸው ምክንያት 1385 አባወራዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ኮይሻ ዋሙራ፣ ሞጊሳ፣ ዋሙራ ቦረከሼ ፋታታና ጎጨ በተባሉት ቀበሌዎች ላይ በደረሰው በዚሁ የጎርፍና የመሬት ናዳ አደጋ፤ በናዳው የተቀበሩ ሰዎችን ህይወት ለማትረፍ የአካባቢው ህብረተሰብና የነፍስ አድን ሰራተኞች ቢጣጣሩም መንገዶቹ በጎፍርና በመሬት ናዳው በመዘጋታቸው የነብስ አድን ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገውና ይህም በናዳውና በጎርፍ አደጋው ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው ዝናቡ አሁንም ያለማቋረጥ እየዘነበ ሲሆን መሬቱ የንቅናቄና ለየት ያለ ድምፅ የሚያሰማ በመሆኑ አካባቢው በስጋት ውስጥ እንደሚገኝም ከስፍራው ያገኘናቸው ምንጮች ገልፀውልናል፡፡
የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ፤ አደጋው የደረሰባቸው ቀበሌዎች በመዘዋወር ተጎጂዎችን ያነጋገሩ ሲሆን በጊዜያዊነት መጠለያ ስለሚያገኙበት ሁኔታና በዘላቂነት ከአካባቢው ርቀው የሚሰፍሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መንግስት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ቃል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በምስራቃዊው የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሥጋት እያንዣበበ ሲሆን ሰሞኑን በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ሳቢያ በተከሰተው ጎርፍ፤ ድሬደዋን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው አስፋልት መንገድ መሰንጠቁን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ ኬላ (ገነት መናፈሻ) እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ላይ በጎርፍ የተሰነጠቀው አስፋልት መንገድ ለተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ሲሆን በ1998 ዓ.ም ከተማዋ ላይ ደርሶ ከነበረው የጎርፍ አደጋ በኋላ የተሰራው የጎርፍ መከላከያም መፍረሱ ታውቋል፡፡ በምሽት ከድሬደዋ የሚመጡና ወደ ድሬደዋ የሚገቡ መኪኖች ልዩ የመብራት ታፔላ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ መመሪያ የወጣ ሲሆን መኪኖቹም በዚሁ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን፤ ስፍራው ድረስ በመሄድ ሁኔታውን የተመለከቱ ሲሆን አካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ በጎርፍ አደጋ ስጋት ውስጥ መውደቁን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከትናንት በስቲያ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ ደራሽ የጎርፍ አደጋ እንደሚከሰት አስቀድሞ መተንበዩን ጠቁመው፤ ዝናቡ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ለአደጋዎች መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እስከ አሁን ድረስ ባለው መረጃ፤ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል፡፡



Read 3691 times Last modified on Saturday, 14 May 2016 12:06