Print this page
Saturday, 14 May 2016 11:56

በደል እየተፈፀምብን ነው ያሉ አባወራዎች ለአማራ ክልል አቤቱታ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

         “በአማራ ተወላጅነታችን የብሔር ጭቆና ደርሶብናል” ያሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ ከ400 በላይ አባወራዎች ለአማራ ክልል አመራሮች አቤቱታ አቀረቡ፡፡
ለአሶሣ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ በሚል ከ6 አመት በፊት ለተወሰደባቸው 163ሺህ ሄክታር መሬት ካሣ እንዲከፈላቸው አሊያም ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው በፍ/ቤት የጠየቁት አባወራዎቹ፤ ከሰሞኑ “በአማራ ተወላጅነታችን በደል እየተፈፀመብን ነው” ሲሉ የአማራ ክልል መፍትሔ እንዲሰጣቸው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
አባወራዎቹ ለልማት ተብሎ ቦታችን ያለአግባብ ተወስዷል፣ ካሣ አልተከፈለንም፤ ከክልሉ ነባር ተወላጆች እኩል የአስተዳደር አገልግሎት እያገኘን አይደለም” የሚሉ አቤቱታዎችን ለአማራ ክልል አመራሮች በማቅረብ ክልሉ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ጠይቀዋል፡፡
የመኖሪያና በግብርና የሚተዳደሩበት ቦታቸው ያለ ምንም ካሣ እንደተወሰደባቸው የሚገልፁት አባወራዎቹ፤ የመኖሪያ ቦታ ከሌለንና ተሠማርተንበት በነበረው ግብርና ልጆቻችንን ማሳደግ ካልቻልን የኛ በክልሉ መኖር ትርጉም የለውም ብለዋል፡፡
አባወራዎቹ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን አግኝተው ለማነጋገር በማሰብ ከአሶሣ ወደ ባህርዳር ሄደው የነበረ ቢሆንም የክልሉ መንግስት የፕሬዚዳንት ልዩ ረዳት አቶ ሰማ ጥሩነህን ማነጋገራቸውንና ሃላፊውም በፍርድ ቤት የተያዘውን ጉዳይ በሚገባ ተከታተሉ፤ እኛም ይሄን ጉዳይ ሃላፊነት ወስደን በትኩረት እንከታተላለን” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል። “በአማራ ተወላጅነታችን በደል እየተፈፀምብን ነው” ያሉት አባወራዎቹ፤ በቤኒሻንጉል ክልል መኖር የማይችሉ ከሆነ የአማራ ክልል የመስፈሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ጭምር በቀጣይ እንደሚጠይቁ የገለፁ ሲሆን ለክልሉ መንግስት በፃፉት የአቤቱታ ደብዳቤያቸው ላይም ይህ እንደ መፍትሔ ሃሳብ እንዲወሰድላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከ6 ዓመት በፊት ለአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተብሎ ለተወሰደባቸው ቦታ ምትክ እንዲሰጣቸው ወይም ካሣ እንዲከፈላቸው የጠየቁት አባወራዎቹ፤ ለዚህም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትንና ትምህርት ሚኒስቴርን መክሰሳቸው መዝገቡ ይታወሳል፡፡
የክስ ሂደቱም ከነገ በስቲያ በፌደራል ከፍተኛ  ፍ/ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት የሚታይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3670 times