Saturday, 25 February 2012 14:14

የቶሬስ ትራጄዲ ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ፈርንናንዶ ቶሬስ በ12 ወራት የስታምፎርድ ብሪጅ ቆይታው በሁሉም ውድድሮች በ34 ጨዋታዎቸ 5 ጎል ብቻ ማግባቱ ትራጄዲ ተባለ፡፡ በዓመት 10 ሚሊዮን ፓውንድ ደሞዝ በቼልሲ የሚከፈለው ቶሬስ በክፍያ ከሚቀራረባቸው ሜሲ እና ሮናልዶ ጋር በንፅፅር ሲታይ የምንግዘም አክሳሪ ተጨዋች ሆኗል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ የቼልሲው አንድሬስ ቪያስ ቦአስ ቡድናቸው 3ለ1 እየተመራ ቤንች ላይ ከነበሩት ተጨዋቾች ብቸኛው አጥቂ ቶሬስን ሳያስገቡት ቀሩ፡፡ ይህ አጋጣሚ ባንድ ወቅት በዓለም እግር ኳስ ይፈራ የነበረው አጥቂ ዛሬ ከግምት የወጣ መሆኑን አመልክቷል፡፡ቶሬስ ከ15 ዓመቱ ጀምሮ ለተጫወተበት የስፔን ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድ በ200 ጨዋታዎች 83 ጎሎች አግብቷል፡፡ ክለቡን በ19 ዓመቱ በአምበልነት መምራት የቻለ ወሳኝ ልጅም ነበር፡፡

ከ4 ዓመት በፊት ሊቨርፑል ሲገባም በክለቡ ታሪክ 50 ጎሎች ፈጥኖ በማስመስገብ ምርጡ አጥቂ ተባለ፡፡

በ2008 እና በ2009 እኤአ በእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግና በዓለም እግር ኳስ ምርጥ ቡድን ውስጥ የማይቀር ተመራጭ ሆነ፡፡ በ2008 የአውሮፓ ዋንጫ በፍፃሜ ጨዋታ ስፔንን ከ42 ዓመት በ ኋላ ለድል ያበቃችውን ብቸኛ ጎል አስገባ፡፡

ከ2009 የውድድር ዘመን በኋላ ግን የቶሬስ ታላቅነት እየተሸረሸረ መጣ፡፡ በሊቨርፑል በሄጅሰን አሰልጣኝነት በ23 ጨዋታዎች 9 ጎል ብቻ አግብቶ በጎል ድርቅ ሲመታ የአንፊልዱ ክለብ ለቼልሲ ተጨዋቹን በእንግሊዝ እግር ኳስ ሪኮርድ ሆኖ በተመዘገበ የ50 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ለማሰናበት ሳያመነታ ቀረ፡፡

በስታምፎርድ ብሪጅ የመጀመርያውን ጎል  ማግባት የቻለው ከ903 ደቂቃዎች በኋላ ነበር፡፡ በዚህ ድክመቱ ቀጥሎ በዓምናው ፕሪሚዬር ሊግ 14 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሰልፎ በወረደው ዌስትሃም ላይ ብቻ አንድ ጎል አግብቶ የመጀመርያ ውድድር ዘመኑን ጨረሰ፡፡

ዘንድሮም ያው ነው፡፡ በሊጉ ጅማሮ እስከ 5 ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ኳስና መረብን ማገናኘት ተስኖት ሰነበተ፡፡

የመጀመርያ ጎሉን ማን ዩናይትድ ላይ ሲያገባ ደግሞ በአውሮፓ ጋዜጦች የፊትና ጀርባ ገፅ ሰፊ ሽፋን የነበረው በጨዋታው ቶሬስ ባዶ ጎል መሳቱን ያተተ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ በ25 ጨዋታዎች ጎል ያገባው 2 ብቻ ሆነ፡፡ አሁን ጎል ካገባ 20 ጨዋታ ያለፈው ቶሬስ በቼልሲ በቆየባቸው 12 ወራት በሁሉም ውድድሮች ያገባው 5 ብቻ ነው፡፡

ተጨዋቹ አሁንም ሆነ ወደፊት በቼልሲ እቆያለሁ ብሎ ቢናገርም በዚህ የውድድር ዘመን መጨረሻ በኪሳራ ሊሰናበት እንደሚችል መወራት ጀምሯል፡፡ ከሚፈልጉት ክለቦች አንዱ ከሊጉ የወረደው ዌስትሃም ነው፡፡

ፈርናንዶ ጆሴ ቶሬስ ሳንዝ 27 ዓመቱ ነው ከዓመት በፊት ያለው ሃብት 18 ሚሊዮን ፓውንድ ተገምቷል፡፡

ከ2001 2007 በአትሌቲኮ ማድሪድ 214 ጨዋታዎች አድርጎ 82 ጎሎች

ከ2007 2011 በሊቨርፑል 102  ጨዋታዎች አድርጎ 65 ጎሎች

ከ2011 ጀምሮ በቼልሲ 34 ጨዋታዎች 5 ጎሎች

 

 

Read 2474 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 14:16