Saturday, 07 May 2016 13:40

ወንዶች ሳያድጉ፣ አርጅተው የሚሞቱ ህፃን ናቸው?

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(2 votes)

“ወንዶች ስትባሉ የህፃንነት ጠባይ ያጠቃችኋል። ሳታድጉ ነው አርጅታችሁ የምትሞቱት” ይሄን የምትለው የበዓሉ ግርማ ገፀ ባህርይ ናት፤ “ደራሲው” ውስጥ የተሳለች፤ ሰብለወርቅ ታፈሰ ብሩ የተባለች፣ የደብተራ ልጅ፣ በመጽሐፍ ቀበኛ፤ በባል ቁራኛ የተያዘች፡፡ ቀበኛው ደራሲው ሲራክ ነው፤ ቁራኛው ደግሞ ዘመነ ዓለሙ የተሰኘ የአብዮት ተጐጂ፡፡ እዚህ ቅርቃር ውስጥ ሰብለወርቅ ተፈጥርቃ ትኖራለች። ዳኝነቷ የብዙ ወንዶች ህመም እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ ወንዶችን ሁሉ እፍኝ የገቡ ቄጠማ አድርጋ በክርክር ስል ማጭድ ታጭዳለች፡፡
እውነት ወንዶች እንደዚህ ነን? የህፃንነት ጠባይ አለን? ሳናድግ አርጅተን እንሞታለን? ተነፃፃሪያችን ህፃን ምን ያደርጋል? እኛስ?
ሰብለወርቅ ይሄን የምትለው ውብ ብትሆንም ባሏ እጅ ከገባች በኋላ “ዋጋዋ” እየቀነሰ በመምጣቱ ነው፡፡ በንግግር ያራክሳታል፣ ከሕሊናዋ አልፎ አካሏን ያጐሣቁልባታል፡፡ ዘመነ ሰብለወርቅን እስኪያገኝ አልቅሷል - እንደ ህፃን፤ ሲያገኛት ስቋል - እንደ ህፃን፤ ውሎ ሲያደር የት እንደተወሸቀች ረስቷል እንደህፃን፤ “አስታውሰኝ” ስትለው “አልፈልግም!” ብሏል - እንደ ህፃን፡፡
ግን ሁላችንም እንዲህ እንደ ዘመነ ነን? ጥያቄው ከበዓሉ ግርማ አንፃር ከተነሣ መልሱ “ነን!” ነው። “ህፃን ነን! ያውም ሳናድግ አርጅተን እንድንሞት የተፈረደብን ህፃን!!”
እንዴት?
እንደዚህ፤ እዚያው “ደራሲው” ውስጥ ዋናው ገፀባህርይ ሲራክ አጥምዶ የያዛትን ሚስቱን ችላ ብሎ ሰብለወርቅን ለመያዝ የሚንጠራራ ሆኖ ተፈጥሯል፡፡ ቃል በቃልም እንዲህ ይላል፡-
“የፍቅር ቅመሙ ታዲያ ከምኑ ላይ መሰለሽ? መለየት መኖሩን ከማወቅ ላይ ነው፡፡ እንደ ህይወት ማለት ነው፡፡ ሞት ባይኖር የህይወት ጣዕም እንዴት አድርጐ እንደሚገባን አላውቅም፡፡ ይገባን እንደሆን ማለቴ ነው” (ገፅ 66)
የሲራክ (የወንድነት) ቅመሙ ከእነዚህ ቃላት የተውጣጣ ነው፡፡ (ቢያንስ በበዓሉ ግርማ ድምዳሜ) መለያየት መኖሩን እስካወቅን ድረስ ፍቅር አለ፡፡ መለያየት የሞተበት ትዳር ውስጥ ግን ፍቅርም በድን ነው፡፡ ሞት የማይታወቅበት ህይወት በዘልዛላነት እንደሚቸከን ሁሉ መለያየት በባህልና በእምነት ግብአተ መሬቱ የተፈፀበት ትዳር ፍቅርን ያፍናል። የሲራክ ህይወት በገቢር ይሄው ነው፡፡ መኖሪያ ቤቱ ሲገባ የሚሞተው ልቡ፣ መስሪያ ቤቱ ሄዶ ሰብለወርቅን ሲያገኝ ከሙታን ይነሳል፡፡ ህፃንም ይሄው ነው፡፡ ዛሬ አልቅሶ ያስገዛውን መጫወቻ ከጥቂት ጊዜ በኋላ (የራሱ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ) ላይፈልገው ይችላል፡፡ ሌላ ሰው ወደያዘው ሌላ ዕቃ ሊያተኩርም ይችላል፡፡ የሰብወርቅ (የበዓሉ ግርማ) ተሐዝቦ ባያስደመድምም ለማግደርደር አይሳነውም።
ከዚህ ጋር ኩታ ገጠምነት ያለው አንድ ተረት ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር አጫውቶኝ ነበር። የጥንት ፈረንሳዮች በትዳር ላይ ያላቸው ወግ ከአሁኖቹ ለየቅል ነበር አሉ፡፡ አንድ መኳንንት ወደ ቤቱ የሚገባው ፍቅረኛው ጋ አምሽቶ፣ አኳሽሞና የፍቅር ወግ ጠርቆ መሆን ይገባዋል ተብሎ ተደምድሟል፡፡ እና የዚያ ዘመን ተሳታፊ አንድ ፈረንሳዊ ከሚስቱ በላይ በፍቅረኛው ቁራኛ ተይዞ ሲሰቃይ አንድ ወዳጁ እንዲህ ሲል ጠየቀው አሉ፡-
“ፍቅር እንዲህ ከፀናብህ ለምን ሚስትህን ፈትተህ እሷን አታገባትም?”
“እሷን አግብቼ የት አባቴ ላመሽ?” አለ አሉ አፍቃሪ፡፡
የወንድ ሁሉ ህይወት ይሄው ነው? የተያዘችውን ወደ ኋላ፤ ያልተያዘችውን ወደፊት አድርጐ፣ በሴት እንደታጠሩ መጓዝ? በመፈለግና ባለመፈለግ መካከል መወዛወዝ? በህፃንነት ምህዋር ላይ ሲሽከረከሩ ኖሮ ነፍስ ሳያውቁ አርጅቶ መሞት? ነው? በማግኘት ታክቶ፣ በማጣት ተብከንክኖ መቅረት?...
…ሴቶችስ? ይሄን ጥያቄ ሲራክም አንስቶታል። ሰብለወርቅ በወንዶች “ህፃንነት” ስትብከነከን “በሴቶች አይብስም?” ብሏታል፡፡ ምን መለሰች?
“ፍፁም! እዚህ ላይ በጣም ተሳስተሃል፡፡ እኛ ሴቶች አንዴ ከወደድን እንወዳለን፡፡ ሌላ ወንድ ያለ አይመስለንም፡፡ የምታራክሱንም ለዚሁ ነው”
ሲራክ በመከራከሪያው አልቀጠለም፤ በሰብለወርቅ ምላሽ የያዘውን ለቅቋል፡፡ ፆታውን አስረትቶ ያለፆታው “አጉራሽ ጠናኝ” ብሏል፡፡ እዚህ ውስጥ ደራሲው በዓሉም ያለ ይመስላል፡፡
እንዴት?
እንደዚህ፤ በዓሉ ግርማ የፃፋቸው ልቦለዶች ሁሉ ዋና ገፀባህሪው የሚገኘው በሁለት ሴቶች ሰርጥ ውስጥ፤ ነፍሱ የሳንሳ ተይዛ ነው፡፡ በ “ደራሲው” ውስጥ ፅጌ ሃይለማሪያምና ሰብለወርቅ ታፈሰ የሲራክ ህይወት የጀርባና የፊት ችካሎች እንደሆኑት ሁሉ፤ የ “ኦሮማይ”፣ የ “ሀዲስ”፣ የ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” እና የ “ከአድማስ ባሻገር” ዋና ገፀባህሪዎችም ዕጣ ፈንታ በመቂናጣዊ መወዛወዝ ተለጉሟል፡፡ መነሻና መድረሻቸው፣ ትልምና ግባቸው፣ ሳቅና እንባቸው በሁለት ሴቶች ሰርጥ ውስጥ ታቁሯል፡፡ አንዴ ይሁን፣ ሁለቴም ግዴለም፣ እንዴት ተደጋገመ? ያሰኛል፡፡
የ“ኦሮማይ”ው ዋና ገፀ ባህርይ ሮማን ህለተወርቅ እና ፊያሜታ ለተባሉ አንስታይ ሉአላዊነቶች ተባዕታዊ መስዋዕትነት የሚከፍል ባተሌ ነው። እንዲሁ ሀዲስ በስሙ የተሰየሙ ልቦለድ ውስጥ በኃላፊና በመጪው ጊዜው በወከላቸው ሽታዬና አይናለም በተባሉ ሴቶች ዘብጥያ ወርዷል፡፡ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” ውስጥ ያለው ደርቤ ደግሞ እንደ ቀንና ሌሊት እየተፈራረቁ የሚያስተኙትና የሚያነቁት ሁለት ሴቶች በበዓሉ ግርማ ተመድቦበታል፡፡ ሒሩት እንደ ስሟ ሌሊትና ፍትወት ወክላለች፤ ፍኖት ደግሞ የህይወት መዳረሻ መንገድነቷን ትጠቁማለች፡፡ እዚያ ሰርጥ ውስጥ ደርቤ መጨበጥና መልቀቅ ተስኖት ይባትላል፡፡ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥም በራሷ የምኞት ዓለም አበራ ወርቁን የምትቃብዘው ሰናይት እና ለመግራት የምንትገላታው ሉሊት አሉ፡፡
… አንድ ነገር ሲደጋገም “ለምን?” ማሰኘቱ የወግ ነው፡፡ እንደውም አለመጠየቁ ተፈጥሯዊነት ያጣል ማለት ይቻላል፡፡ ከበዓሉ የጥበብ ዓለም እስከ ህይወት ህማም ድረስ የተዘረጋ ፍተሻ የሚያስፈልገው ድግግሞሽ ነው፡፡ የወንድን ዓለም መንታ አንስታይ “ፀሐይ” የሚፏልልበት እንግዳ ተፈጥሮ ማላበስ የአንድ ደራሲ የጥበብ ነጠላ ግብ ከሆነ አጠያያቂነቱ እሙን ነው፡፡ በዓሉ ህይወት ውስጥ ምን ገጠመኝ አለ? በተደራሲያኑ ምን ግንዛቤ እንዲወሰድ ይሻል? በእርግጥ ድግግሞሹ ከድምዳሜው የፈለቀ ነው? ወይስ ልብ ሳይለው ይተገብረዋል? …
በእኛ የአማርኛ ሒስ አግባብ እንዲህ ያለ ጥያቄ ተነስቶ ትንታኔ የተሰጠበት ሥራ አላጋጠመኝም። በውጭው ዓለም ግን አለ፡፡ ለምሳሌ እንደ በዓሉ ግርማ ሁሉም ስራዎቹ አይሁን እንጂ ሩሲያዊው ደራሲ ፊዮዶር ደስተየቭስኪ መንታ ሴቶች የሚያዋክቡት ዋና ገፀ ባህርይ ደጋግሞ ስሏል። “The Brothers Karamazov” ውስጥ ካተሪና ኢቫኖቭና ግሩሼንካ የተባሉ ሴቶች በእኩል ጉልበት የተሳሉ መንትያ ሴት ገፀ ባህርያት ናቸው፡፡ “The Idiot” የተሰኘ ልቦለዱ ውስጥ አግላያ እና ናፃስያ ፍሊፓቭና አሉ፡፡ በተመሳሳይ ቫርያ እና ሶኒያ ደግሞ “Crime and Punishment” ውስጥ ተገዳዳሪ ገፅታ ተላብሰው በዋና ገፀ ባህሪው በራስ ኮሊንኮቭ ህይወት ይፈራረቃሉ፡፡ እንዲሁ በ “The Insulted and Injured” ልቦለድ ውስጥ ታዳጊያዊ ኒሊ እና ኮረዳዋ ኒዛኖቫ ዕድሜያቸውን ያላማከለ ፉክክር ገጥመው ቀርበዋል፡፡
ይሄ የደስተየቭስኪ አዝማሚያ እንደኛው በዓሉ ችላ አልተባለም፡፡ ሁኔታውን ግልፅ ለማድረግና ድምዳሜ ለመስጠት የሚሞክሩ ብዙ ጥናቶች ተሰርተዋል፡፡ እኔን ሊያሳምኑኝ ከዳዱኝ ጥናቶች ውስጥ አንዱ ወደ ደስተየቭስኪ ኃላፊ ጊዜ ተጉዞ ሊያገናኘው የሚጥር ነው፡፡ Konstantin Muchulsky የደራሲውን ህይወትና ሥራ በሚዳስስበት መፅሐፉ ላይ እንደጠቆመው፤ የጥንድ ሴቶች መገዳደር ምንጩ ፎንቪዚና የተባለች ሴት ነች፡፡
እንዴት? …
… እንደዚህ ነው፡፡ ፎንቪዚናን ደስተየቭስኪ የሚያውቃት የሩሲያን ንጉስ በመግደል ሴራ ተከስሶ ሞት በተፈረደበት ማግስት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የሞት ፍርዱ ተሽሮ በአራት አመት የጉልበት ቅጣት ተቀይሮለት ወደ ሳይቤሪያ እየተጓዘ ነበር፡፡ አብረውት ሴረኞች የተባሉ (Desemberist) አሉ፡፡ ከእስረኞቹ የአንዱ ሚስት ከባሏ ላለመነጠል ወደ ላይቤሪያ አብራ እየተጋዘች ነበር፡፡ ያቺ ሴት ናታሊያ ፎንቪዚናን ስትሆን ደስተየቭስኪ በእስር ያሳለፋቸውን አመቶች እያነበበ የተፅናናበትን መፅሐፍ ቅዱስና አሥር ሩብል እንደሰጠችው ማስታወሻው ላይ አስፍሮት ተገኝቷል፡፡
በተጨማሪም የጓደኛው ሚስት ብትሆንም ዕድሜ ልኩን ሲያፈቅራት እንደኖረ፤ ባለቤቷ ከሞተ በኋላ ሳምንትም ሳይቆይ የጋብቻ ጥያቄ እንዳቀረበና እንዳልተቀበለችውም አልሸሸገም። ፎንቪዚና ለፍቅር የተገዛችለት ባሏ ከሞተ በኋላ የጥንቱን መሆን ተስኗት በብዙ ድክመት ተከባ ቀሪ ህይወቷን ገፍታለች፡፡ እንደ ሙቹሉስኪ ድምዳሜ፤ ደስተየቭስኪ በልቦለዱ ውስጥ የሚቀርፃቸው መንታ ሴቶች፤ በጥንካሬና በድክመት የዚችን ሴት መንታ ህይወት የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ደስተየቭስኪ እንደ በዓሉ ግርማ ሁሉ ከህይወት ወደ ልቦለድ በመቅዳት የሚታወቅ ደራሲ ነውና የሙቹሉስኪ ድምዳሜ እውነትነት አያጣም፡፡
… ለመሆኑ ስለ በዓሉ ግርማ እና ስለ መንቶ ሴት ገፀ ባህርይ አሳሳሎቹ ምን ማለት ይቻላል? የሕፃንነት ጠባይ ስለሚያጠቃቸውና ሳያድጉ አርጅተው ስለሚሞቱ ወንዶች ያለው ድምዳሜስ? እንዴት? ለምን እዚህ ድምዳሜ ላይ ደረሰ? ከኑሮውና ከህይወቱ ጋር እንዴት ይተራጎማል? በምን ይገናኛል? … ብዙ ጥያቄ፤ ምናልባትም ምላሻቸው ከእኛ ብዙ የራቀ …፡፡  

Read 3134 times