Saturday, 07 May 2016 13:37

ይበለኝ በገዛ እጄ!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

    ያዕቆብ ይባላል፡፡ ሙሉ ቀን መለሰ “ሰንደቅ ያሰቅላል”ን ለሴት ቢያዜመውም ያዕቆብን በሚገባ ይገልፀዋል፡፡ የአርባዎቹን አጋማሽ እየተሻገረ ቢሆንም ግርማ ሞገሱ፣ቅልጥፍናውና ሽንቅጥቅጥ ማለቱ ገና በሰላሳዎቹ ማለዳ ላይ ያለ ያስመስለዋል፡፡ ተምሯል፤የገንዘብም የዲግሪዎችም ሀብታም ነው፡፡ በአንድ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በሚንቀሳቀስ ትልቅ ተቋም ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ ይሰራል፡፡ ዘወትር ሙሉ ልብስ ግዴታው ነው፡፡ እንደሱ የሚያምርበትም አላየሁም፡፡ ታዲያ በዕረፍት ቀኖቹ ቀለል ያለ ልብስ ሲለብስ ሌላ ሰው ይመስላል፡፡ ልውጥ ይላል፡፡ባሌ ነው፤ የምወደው ባሌ፡፡ ምን ዋጋ አለው? ጥሎኝ ሄዷል፡፡ ሁለት ሳምንቱ … በገዛ እጄ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጥሎኝ መሄዱን እንጂ ጠልቶኝ መሄዱን አላምንም፡፡ ጠልቶኝ ካልሆነ ደሞ ክዶኝ ሊሆን አይችልም፡፡ የጋብቻችንን ዘጠነኛ ዓመት ለማክበር የቀረንም ሁለት ሳምንት ብቻ ነበር … ዝግጅታችንን በጋራ አቅደን ጨርሰንም ነበር፡፡
“ካልሆነልን ለምን እንጨነቃለን አቡቲዬ” ውይ ቁልምጫው ሲጥመኝ….አበባ ብሎ ጠርቶኝ  አያውቅም፡፡
“ምንም አይሰማህም?”
“አልዋሽሽም … በቃ ማመን ካለብን ማመን ወይም ተማክረን አማራጭ …”
ቀለል ሲያደርገው ማን አክብጂው አለኝ … በገዛ እጄ!
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ወደ ምሰራበት ግብረሰናይ ድርጅት ቢሮ መጣ፡፡ የኛን ድርጅት የሚረዱ … የውጭ ተቋማት ከነሱም ጋር ይሰራሉ፤ ተመሳሳይ ዓላማዎች ሲገጥሙን አብረን እንሰራለን፡፡ እኔ ደሞ የድርጅታችን ዋና ኃላፊ ነኝ፡፡ ወደ ቢሮዬ ሲገባ ዓይኖቼ ከቁጥጥሬ ወጥተው አጠር ያለች ቁመቴ ረዝማብኝ እየሳብኳት ብድግ ብዬ ተቀበልኩት፡፡ ዘንጣፋ ሰውነቱን እጥፍ አርጎ በአክብሮት ጨብጦኝ ተቀመጠ፡፡ ቢሮዬን እንደሱ የሞላው ሰው አልገጠመኝም፡፡ በግርማው ተጥለቀለቀች፡፡ ለስንትና ስንት ጥላ ቢሶች የሚተርፍ ግርማ፣ የቀልቤን መዝረክረክ ይወቅብኝ አይወቅብኝ እንጃ፡፡ እንደ ምንም የመጣበትን ጉዳይ ተነጋግረን ሄደ፡፡ ለሱ ነው የሄደው፤ ለኔ ቢሮዬ ነበር የዋለው፡፡
ጉዳዮች አመላለሱት፤ቀጥሎም እኔ ጉዳዩ ሆንኩና … ልቤ ላይ በድብቅ ስትንፈራፈር የነበረችውን የፍቅር ፅንስ ነፍስ ዘራባት፡፡
እኔን ድንገት ላየኝ ሰው፣ ክልስ ልመስለው እችላለሁ፡፡ “ቀይ ሰው መልክ አይፈጅም” ቢባልም ሳይጋነን ፈጅቻለሁ፡፡ ከ27 ወደ 28ኛ ዓመቴ በመሸጋገር ላይ ነበርኩ፡፡ አስጨናቂ የዕድሜ ዳገት ነው ለኛ ለሴቶች፡፡ ብዙ ወንዶች እንዳዩኝ ቢሸነፉም እኔ በቀላሉ አልሸነፍም፡፡ እየፈለግሁ እንኳን አይሆንልኝም፡፡ ዕውቀት፤ ስራ፤ ጥሩ ደሞዝ፤ ጥሩ ኑሮ አለኝ፡፡ ለእህቶቼ ተርፌያለሁ፡፡ በየመንገዳቸው ሄደው ርቀዋል … የእናቴን ድህነት ታሪክ አድርጌ ቀብሬዋለሁ፡፡
 ጎድሎኝ የነበረውን ያቆብ ሞላው … ስንላመድ እንደ ልጅ ያደርገን ጀመር፡፡ ያልኖርነውን እንደ መኖር … በኋላም ምርጫ አጣን፤ ከመጋባት በቀር፡፡ … በቃ አደረግነው፡፡ ተጋባን፡፡  በቅርብ ጓደኞቻችንና ወላጆቻችን ብቻ ታጅበን … በእማዬ “እልልታ” ደምቀን፣ “በወልዳችሁ ሳሙ” ምርቃት እየሰፈፍን ወደ ያቆቤ የሪል ስቴት ቪላ ገባን፡፡ ኑሮ ደመቀ … ጣፈጠ … ግን አልሞላም … ሁሉም ላይሞላ ቢችልም ደርበብ የሚያደርገው የእማዬ ምርቃት ሰሚ አጣ፡፡ በየወሩ ጠባዬን … ሆድ ሆዴን ትከታተላለች፡፡ ያቆቤም ይጠብቃል፡፡ ሁለት ጊዜ እያሳየ ነሳኝ፡፡ ደስታችንን ሳናጣጥም ጨንግፎ አጨነገፈን … ከዚያ በቃ ዝም ሆነ፡፡ እናቴም “ፈጣሪ ያልፈቀደውን እሷን ምን አርጊ እላታለሁ?” ብላ ነው መሰል ዝም …. እምምምም ብላ ቀረች፡፡ ያቆብም አመነ፡፡ ከዕውነቱ ጋር ታረቀ፡፡ እኔ ግን ጭንቀት የውስጥ ልብሴ ሆነ፤ከላይ ድምቅ ፅድት ውስጤ ግን …
ሰሞኑን ሃዘን ላይ ነኝ፤ ከፍራሽ ላይ ሳልወርድ እንባዬን ደብቄ አወርደዋለሁ፡፡ የሰርጋችንን ቪዲዮ ማየት የዘወትር ስራዬ ሆኗል፡፡ ያቺን ብርቅ ቀን፣ ያንን ድንቅ የፍቅር ሰው እያሰብኩ እንባዬ ሊያልቅ ነው፤ ሚዚዬ ሔዋንም የለችም፤ አብሮ አደጌ፣ ከራሴ እኩል ከማያቸው ሰዎች አንዷ ናት፡፡ ያሉኝም እነዚሁ ናቸው፡፡  እናቴ --- ያቆብ --- ሔዋን!!
… እናቴ የያቆቤን መጥፋት ማወቅ የለባትም፤ሌላ ህመም ይሆንባታል፡፡ በገዛ እጄ ራሴን ክፉኛ ቀጣሁት፡፡
“አቡቲ”
“ወዬ..”
“ራስሽን እያስጨነቅሽ ነው”
“ደህና ነኝ”
“እያየሁሽ …. ለምን በጉዲፈቻ አናሳድግም” ለስሜቴ እየተጠነቀቀ
“ከስራሽም ጋር ስለሚያያዝ….”
“እስኪ … አንድ የማሰላስለው ነገር አለ … እሱን …”
“ምንድነው አቡቲዬ?”
“ሰሞኑን እነግርሃለሁ”
ቢሮ ገባሁ አልገባሁ ለውጥ አልነበረውም፡፡ የስራ መንፈሴ ሸሽቶኛል፤ የአዕምሮዬም አቅም ተዳክሟል፡፡ ስልኩ ላይ መደወል መደወል … ዝግ ነው፤ ቢዚ ነው፤ ሊገኝ አይችልም …ይለኛል፡፡ አንዴ በመሃል ላይ ድምጹን ሰማሁት፡-
“ሃሎ አቡቲ” ጥሎኝ ሄዶም አቡቲ ማለቱ ገረመኝ፡፡
“ያቆቤ” ሳግ እየተናነቀኝ አወራሁት …
“ኬንያ ነኝ … ስመለስ እደውላለሁ” አጣድፎኝ ሥልኩን ዘጋው፡፡ ስራው ከሀገር ሀገር እንደሚወስደው አውቃለሁ፡፡ ሳይነግረኝ ግን የትም ሄዶ አያውቅም፡፡ ወደ ቢሮው ስሄድ መውጣቱን ይነግሩኛል፡፡ ዝም ብዬ ግራ ስጋባ ሰነበትኩ፡፡
ከጉዲፈቻው አማራጭ በፊት ያሰብኩትን ይዤ ሔዋን ጋ ሄጄ ነበር፡፡ እኩያዬ … ከወዲያኛው ጫፌ እስካለሁበት የምታውቀኝ፡፡ ቆንጆ ነች፤ደስ የምትል ቆንጆ፡፡ ትምህርት ዕጣ ክፍሌ አይደለም ብላ ሁለተኛ ደረጃን ጀምራ ትታዋለች፡፡ በማያዛልቁ ስራዎች ወጣ ገባ ስትል ወንዶች አዩዋት፡፡ ሁሉንም ነገር ቀድማን ነው ያደረገችው፡፡ ቸኩላ አገባች፤ ሁለት ወለደች፤ ሳይቆይ ባሏ በሞት ተለያት፡፡ ብዙም አላዘነችም፤ ኑሮዋንም አለስልሶላት ነበር ያለፈው፡፡ ወጣ ገባዋን ቀጠለች፡፡ የባሏ ዘመዶች በቅርብ ርቀት አዩዋት፤ ገመገሟት፡፡ በመጨረሻ “አንቺ ጥሩ ወላጅ እንጂ ጥሩ እናት አይደለሽም” ብለው ልጆቿን ወሰዱባት፡፡ ጭራሽ ተመቻት አማረባት፤ ተስማማት፤ ያለውን ወንድ የመረቧ ሲሳይ ማድረግ ሆነ ስራዋ፡፡
“ሔዊ ምን ይሻለኛል?” ስላት … እየሳቀች፤ “ወልጄ ልስጥሽ እንዴ?” አለችኝ፡፡ ደንታ የሌላት ናት፡፡ በላች ጠጣች፤ ይዛ ወደቀች .. በቃ ኖረች…
“እኔም ያሰብኩት …”
“አትቀልጅ …”
“ተመሳሳይ ነው ---” ልጅነታችንን … መወለድ ቋንቋ እንደሆነ ያየንባቸውን ዓመታት … ፍቅራችንን እያሰብኩ አማከርኳት …
የዛኑ ቀን … ማታ … መኝታ ክፍላችን ውስጥ … ክንዱን አንተርሶኝ ከሔዋን ጋር የተመካከርነውን ስነግረው … እመር ብሎ ተነሳና አየኝ፡፡ መቆጣት አይችልበትም፡፡ ሄዋንን  እንዳገኛት አይፈልግም ነበር፡፡ “አብሮ ማደግ አብሮ ማርጀት መሆን አለበት” ይለኛል … ሌላ ጊዜ ደሞ “ያኔ እኩል ነበራችሁ … አሁን ግን አይደላችሁም” እያለ ግንኙነታችንን ይቃወም ነበር፡፡
 እኔ ግን ሔዋንን እንደሱ ላያት አልቻልኩም፡፡ ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ በማግባባት--- በመለመን --- ረታሁት፡፡
“የግድ ካልሽ … ይሁና” አለና ዞሮ ተኛ፡፡ በግድ ሳዞረው የቀይ ዳማ ፊቱ ላይ ጭንቀት፤ ፍርሃት፣ ግርምት … በየተራ እየበሩ ሲጠፉ አየሁ
ዛሬ አስራ ሰባተኛ ቀኑ ከጠፋ፡፡ አቅሜ ተዳክሟል፡፡ ስልኩ አይመልስም፤ ቢሮዬን ትቼ ወጣሁ፡፡ ባልደረቦቼ የሚያደርጉልኝ ጠፍቷቸው እንጂ ጭንቀቴ አስጨንቋቸዋል፡፡ መኪናዬ ራሷ ትምራኝ ደመነፍሴ እንጃ … ብቻ እየበረረች ነው፡፡ ያለ ቀልቤ መኪናዬን ዳር አውጥቼ ሳቆማት፣ ከፊቴ የማውቃትን መኪና ያየሁ መሰለኝ፡፡ ወረድኩ፡፡ አዎ የማውቃት መኪና ናት … ሰውነቴ ባንዳፍታ አልታዘዝ አለኝ፡፡
እግሬ እየመራኝ ጥቂት ተራመድኩ፡፡ የልጅነት ጓደኛዬ፣ሚዜዬ ቤት በራፍ ላይ ደረስኩ፡፡
ሳላንኳኳ በሩን ገፍቼው ገባሁ፡፡ ከደፉ ግን ማለፍ አልቻልኩም፡፡ ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ እውትና ቅዠት ተምታታብኝ፡፡ ቅዠት ቢሆንልኝ ተመኘሁ፡፡ ምኞቴ ግን አልሰመረም፡፡
የማፈቅረው ባሌ ያቆቤ----ከራሴ እኩል የማያት የልጅነት ጓደኛዬ ሔዋን---- አንድ ላይ የተሰፉ መስለዋል፡፡ ጠፍተዋል፡፡ አንጎሌ ለአፍታ ማሰብ ያቆመ መሰለኝ፡፡ ሁሉነገሬ ዝም አለ፤ጭጭ፡፡ “ሔዊ ለአንድ ቀን ከያቆቤ ጋር …” ብላት … የልጅነቴን ፀጋ … በረከቴን ሁሉ ነጠቀችኝ፡፡ በአንዲት ቀን ጦስ ባሌን በሞገደኛዋ ሔዋን ጭን ስር አስቀረሁት፡፡ ጓደኛዬንም ባለቤቴንም አጣኋቸው፡፡ ፊቴን አዙሬ ወደ መኪናዬ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ያየሁት አስክሮኛል፤ አፌም አይኔም ደርቀዋል፡፡ እነሱ ግን ምን አጠፉ? የራሴ ጠላት ራሴ ነኝ፤ ሁሉም የሆነው በገዛ እጄ ነው፡፡ መኪናዬ ውስጥ ከገባሁ በኋላ እንዲህ የሚል ሃሳብ በግድ መጣብኝ፡- “ያንን ሁሉ ዓመት በኔ ደስተኛ አልነበረም ወይስ ከሁሉም ሾራ የምታሾረው ሔዋን ሌላ ተዓምር አሳየችው ?!”
ይበለኝ፤በገዛ እጄ ነው! የራሴ ጠላት ራሴ ነኝ !!







Read 4375 times