Print this page
Saturday, 25 February 2012 14:05

“እያንዳንዷ እናት ...ደም ሊፈሳት ይችላል”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

ከወሊድ በሁዋላ ደም መፍሰስ (Postpartum hemorrhage - PPH) የሚባለው ትክክለኛው መጠኑ በ24 ሰአት ጊዜ ውስጥ እስከ 500/ ሚሊ ሊትር ሲሆን ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው የተለመደ ተፈጥሮአዊ ሂደት ሲሆን ከዚህ ባለፈ ግን ከፍተኛ እና የሚያሰጋ ወይንም ደግሞ ብዙም ጉዳት የማያደርስ ተብሎ የሚገመት የፍሰት መጠን አለ፡፡ የደም መፍሰስ እስከ 1000 mls አንድ ሺህ ሚሊ ሊትር ድረስ ብዙም ለጉዳት የማያጋልጥ ሲሆን...የደም መፍሰሱ ከ1000 mls አንድ ሺህ ሚሊ ሊትር በላይ ከሆነ ግን አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈለግለት የሚገባ አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡

ከላይ የተገለጹት መጠኖች በመጀመሪያ ደረጃ ማለትም ልጅ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 24 ሰአት ድረስ ባለው ጊዜ የሚፈጠር የደም መፍሰስ መጠን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ልጅ ከተወለደ ከ24 ሰአት በሁዋላ እስከ ስድስት ሳምንት በሚሆን ጊዜ የሚከሰት አደገኛ የሆነው የደም መፍሰስ ነው፡፡

መረጃውን ያገኘነው ከተለያዩ ሰነዶች ሲሆን በዚህ ርእሰ ጉዳይ ለማብራሪያው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያን ዶ/ር ደሴ እንግዳየሁን ጋብዘናል፡፡ ዶ/ር ደሴ እንግዳየሁ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሽያሊስትና የጽዮን ከፍተኛ ክሊኒክ ባለቤት ናቸው፡፡

ከወሊድ በሁዋላ እናቶች ሕይወታቸውን እስከሚያጡበት ደረጃ የሚያደርሳቸው የደም መፍሰስ በምን ምክንያት ይከሰታል?

ሁኔታው ከተፈጠረስ... ማ ...ምን ...ማድረግ ይጠበቅበታል ?

ከላይ ከተጠቀሱት መሰረታዊ ሀሳቦች በመነሳት ላቀረብንላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ዶ/ር ደሴ መልስ ሰጥተዋል፡፡

ኢሶግ/ እርግዝናና ደም ግንኙነታቸው ምን ይመስላል?

ዶ/ር እርግዝናና ደም በጣም የተቆራኙና የተያያዙ በመሆናቸው እርግዝና ማለት ደም ነው ማለት ይቻላል፡፡፡ በእርግዝና ጊዜ የእናቶች የደም መጠን ከ25-30  ይጨምራል፡፡ ለምሳሌ... እናትየው የደም መጠኑዋ አራት ሊትር ቢሆን በእርግዝና ጊዜ እስከ አምስት ሊትር ድረስ ከፍ ሊል ይችላል፡፡ አንዲት ሴት ስታረግዝ የደም መጠኑዋ ከፍ የሚልበት ምክንያት ልጅ ሲወለድ በተፈጥሮ ደም ስለሚፈስ ያንን ለማካካስ ነው ፡፡ በእርግዝና ጊዜ የደም መጠን ከፍ ይላል ሲባልም ለእርግዝናው በተለይ የሚፈጠር ሳይሆን በአጠቃላይ በሰውነት ውስጥ የሚኖረውን የደም መጠን መጨመር የሚያመለከት ነው፡፡ በወሊድ ወቅት እስከ ግማሽ ሊትርና ከዚያ በላይም ደም ሊፈስ ይችላል፡፡ በእርግዝና ወቅት፣ ከእርግዝና በሁዋላ እንዲሁም በምጥ ሰአት የሚከሰተው የደም መፍሰስ ከትክክለኛው መጠን በላይ ከሆነ ለሕልፈት ስለሚዳርግ ጥንቃቄ ያሻዋል ፡፡

ኢሶግ/ በወሊድ ጊዜ ደም የሚፈሰው...አስፈላጊ ባለመሆኑ ነውን?

ዶ/ር በወሊድ ጊዜ ደም መፍሰሱ ተፈልጎ ሳይሆን ግዴታ ስለሆነ ነው፡፡ የእርግዝናው አወቃቀር ሲታይ እናትየው፣ ማህጸን ፣የእንግዴ ልጅ ፣እትብት፣ ልጅ በሚል ግንኙነት በእንግዴ ልጁ አማካኝነት የተጣራ ደም ከእናትየው ወደ ልጁ ይደርሳል፡፡ ልጁ በሚወለድበት ጊዜ የእንግዴ ልጁ ከማህጸን ግድግዳ ስለሚላቀቅ የተወሰኑ የደም ቧምቧዎች ይበጣጠሳሉ፡፡ በተበጠሰው የደም ቧንቧ አማካኝነት ግዴታ ስለሆነ ደም ይፈሳል፡፡ ነገር ግን ማህጸን ወደቦታው ሲመለስ እነዚያን የተበጠሱ የደም ቡዋንቧዎች ስለሚቋጥራቸው የደም መፍሰሱን ያቆመዋል፡፡ ስለዚህ በወሊድ ጊዜ የሚፈሰው ደም ሆን ተብሎ እንዲወገድ ተፈልጎ ሳይሆን በተፈጥሮአዊ ሂደት የሚከሰት ነው፡፡

ኦሶግ/ ከወሊድ በሁዋላ ለደም መፍሰስ ምክንያቱ ምንድነው?

ዶ/ር ከወሊድ በሁዋላ አላስፈላጊ ለሆነው የደም መፍሰስ ምክንያት ከሚሆኑት ዋናው ልጅ ከተወለደ በሁዋላ ማህጸን ወደቦታው መመለስ ሲያቅተው ነው፡፡ ልጅን ከእንግዴ ልጅና ከፈሳሽ ጋር ተሸክሞ የነበረው ማህጸን መጠኑ እጅግ የተለጠጠ እና ልክ በውሀ እንደተሞላ ፌስታል የሚቆጠር ሲሆን ልጅ በሚወለድበት ጊዜ ወደተፈጥሮአዊው ቦታው ለመመለስ የተወሰነ ጊዜ ሊፈጅበት ይችላል፡፡ ልጅ በሚወለድበት ጊዜ የእንግዴ ልጁ ከማህጸን ሲላቀቅ የደም ቡዋንቡዋዎቹ ስለሚቆራረጡ ደም የሚፈስ ሲሆን ማህጸን ወደቦታው በሚመለስበት ጊዜ ግን እየቋጠራቸው ደም እንዳይፈስ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ማህጸን ወደቦታው ለመመለስ በጣም ጊዜ የሚፈጅበት ከሆነ የደም መፍሰሱ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በማህጸን ወይንም በብልት አካባቢ በወሊድ ጊዜ የመሰንጠቅ ሁኔታዎችም ለደም መፍሰስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

 

ኢሶግ/ የደም መፍሰስ ምን ያህል ለእናቶች ሞት ምክንያት ይሆናል ?

ዶ/ር ከጠቅላላው የእናቶች ሞት መጠን 25 የሚከሰተው በደም መፍሰስ ምክንያት ነው፡፡ በእርግጥ እናቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሊሞቱ የሚችሉ ቢሆንም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የደም መፍሰስ ነው፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ሲታዩ ...በውርጃ ፣በደም ግፊት፣ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ኢንፌክሽንመመረዝ ፣በተራዘመ ምጥ እና በተዘዋዋሪ መንገድ በወባ እና በደም ማነስም ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ዋናው ለእናቶች ሞት ምክንያት ከወሊድ በሁዋላ የሚከሰት የደም መፍሰስ ነው፡፡ ዋናው ምክንያት የተባለበት ምክንያትም ሌሎቹ ሕመሞች በህክምና ሊረዱ የሚችሉበትን እድል ጊዜ የሚሰጡ ሲሆን የደም መፍሰሱ ግን በአጭር ጊዜ በሁለት ሰአት  ውስጥ ለሕልፈት ስለሚዳርግ በሕክም ናውም ዘርፍ እንደ ትልቅ ችግር የሚታይ ነው፡፡

ኢሶግ/ ከወሊድ በሁዋላ የሚፈሰውን ደም መጠን ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ ከጤና ባለሙያው ምን ይጠበቃል?

ዶ/ር የጤና ባለሙያውን በተመለከተ እከሊት ደም ይፈሳታል እከሊት ደም አይፈሳትም ብሎ አስቀድሞ ግምት መስጠት እንደማይቻል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው መሪ ቃል ..እያንዳንዷ እናት ከወለደች በሁዋላ ደም ሊፈሳት ይችላል.. የሚል ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዷ እናት ከወለደች በሁዋላ ደም እንዳይፈሳት የሚደረጉትን ቅድመ ጥንቃቄዎች እያንዳንዱ የጤና ባለሙያ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እናቶች ወዲያውኑ ከወለዱ በሁዋላ ደም እንዳይፈስ የሚረዳ መርፌ መስጠት ...መርፌው ካልተገኘ የሚዋጥ መድሀኒት መስጠት ከጤና ባለሙያው ይጠበቃል፡፡ የእንግዴ ልጅን በሰአቱ ማውጣት እንዲሁም ለሚቀጥሉት ሁለት ሰአታት በየአስራ አምስት ደቂቃው የወለደችውን እናት መጎብኘት እና ምን ችግር አለ ?እያሉ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሁሉ ማድረግ የሚቻለው ግን እናትየው በጤና ተቋም ስትወልድ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም እናት በተቻለ መጠን የሰለጠነ የጤና ባለሙያ ባለበት በጤና ተቋም እንድትወልድ ይመከራል፡፡

ኢሶግ/ ከወሊድ በሁዋላ የሚፈሰውን ደም መጠን ወላድዋ እራስዋ ወይንም ቤተሰብ ሊገምት የሚችልበት መንገድ አለ?

ዶ/ር በእርግጥ የሚፈሰውን የደም መጠን መገመት እንኩዋንስ ለቤተሰብ ለጤና ባለሙያውም አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን አንዲት እናት የሚፈሳት ደም በሰአት እስከ ሁለት ሶስት ሞዴስ የሚያስቀይራት ከሆነ ፣አንሶላው የሚበሰብስ ከሆነ ፣የሚወጣው ደም እየረጋ እየተቆራረጠ ከሆነ እና ለመቆም ስታስብ የእራስ ማዞር ካላት በፍጥነት ወደሐኪም መቅረብ አለባት፡፡ ወደሕክምናው ከደረሰች ግን የተለያዩ እርምጃዎች ስለሚወሰዱ ሕይወቷን ለማትረፍ ይቻላል፡፡

ኢሶግ/ ከወሊድ በሁዋላ የሚከሰተውን የደም መፍሰስ መከላከል ይቻላልን?

ዶ/ር በትክክል... በጣም... መከላከል ይቻላል፡፡ በእርግጥ እናቶች ወደጤና ተቋማት መጥተው መውለድ አለባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው አሰራር አዲስ አይነት ሲሆን እሱም ..በንቃት ደም እንዳይፈስ መጠበቅ.. የሚል ነው፡፡

እናትየው በወለደች በአንድ ደቂቃ ውስጥ ደም የሚያቆም መርፌ መስጠት ፣

እትብት ከተቆረጠ በሁዋላ ከሁለት እስከ ከሶስት ደቂቃ ባለ ጊዜ ውስጥ እንግዴ ልጁን ጎትቶ ማውጣት፣

ማህጸንን አሸት አሸት በማድረግ ወደቦታው እንዲመለስ ማድረግ፣

ከወለደች ጀምሮ እስከ ሁለት ሰአት በየአስራራ አምስት ደቂቃው ወላድዋ ወደተኛችበት እየሄዱ መከታተል እና ስላለችበት ሁኔታ ወላድዋን እራራስ ዋን በመጠየቅ ያለችበትን ሁኔታ መረዳት ...የመሳሰሉት ስራራዎች ከተሰሩ እናቶች እንዳይሞቱ ማድረግ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ የእናቶች ሞት መጠን ከፍ ያለ ነው፡፡ ለምእተ አመቱ የተቀመጠው የእናቶችን ሞት የመቀነስ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የጤና ተቋማቱ ብቻቸውን ሊወጡት የሚችሉት ስላልሆነ ሕብረተሰቡ የራሱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ እናቶች ከቅድመ እርግዝና ጀምሮ በእርግዝና ጊዜ እንዲሁም በወሊድ ወቅት በሰለጠነ የህክምና ባለሙያና በጤና ተቋማት መውለድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕብረተሰቡ ይህን ትብብር ቢያደርግ በሀገራችን እየተከሰተ ያለውን የእናቶች ሞት መቀነስ ይቻላል፡፡

 

 

Read 7208 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 14:07