Saturday, 07 May 2016 13:06

ገብረመድህን ዋልያዎቹን ለመረከብ ፈቃደኛ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የነበሩትን ዮሃንስ ሳህሌ  ከሃላፊነት ማንሳቱን በይፋ ያስታወቀው በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ሲሆን፤   በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት የመከላከያውን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ መሾሙ እየተነገረ ነው፡፡ በሹመቱ ዙርያ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በይፋ መግለጫ አልሰጠም።  በአሁኑ ወቅት በመከላከያ ክለብ አሰልጣኝነት  ከሚሰራው ገብረመድህን ኃይሌ ጋር በተለያዩ ሁኔታዎች ከሚካሄዱ ውይይቶች በኋላ መግለጫ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በአሰልጣኝነት ከ18 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው፤ ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ አገራዊ ሃላፊነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን ለስፖርት አድማስ ተናግሯል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ዋልያዎቹን ከተረከበ በኋላ በሶስት ሳምንት ውስጥ ስራውን ይጀምራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሜዳው ውጭ ከሌሶቶ እና በሜዳው ከሲሸልስ ጋር ሁለት ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡
ከ2004 ጀምሮ መከላከያን በማሰልጠን ላይ የሚገኘው ገብረመድህን ፣ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋችነት ከፍተኛ እውቅና ያለው ነው፡፡ በተጨዋችነት ዘመኑ በጭንቅላት በሚያገባቸው ጐሎች ይታወቅ የነበረው ገ/መድህን ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነትም መርቷል፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም የምን ማራዶና፣ “የምን ፔሌ ፔሌ እኛም አገር አለ ገ/መድህን ኃይሌ” ተብሎም ተዘምሮለታል፡፡ ከብሔራዊ ቡድን ጋር በዋና አምበልነት እንዲሁም የአሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ረዳት በመሆን ሁለት የሴካፋ ዋንጫን አንስቷል፡፡ በስድስት የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች፤ በሀ 20 እና ወጣት ብሄራዊ ቡድኖች እንዲሁም በዋና ብሄራዊ ቡድን በምክትል አሰልጣኝነት በተለያዩ ጊዜያት በማገልገል ከ18 ዓመታት በላይ ልምድ አካብቷል፡፡ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት በሃንጋሪ ዲፕሎማ ያገኘ ሲሆን  በካፍ የኤ ላይሰንስም አለው፡፡
ትውልዱ በትግራይ የሆነው ገብረመድህን ኃይሌ፤ እግር ኳስንም በጎጃም ክልል ምርጥ በመጫወት ጀምሮ፣ በክለብ ደረጃ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተ ሲሆን፣ ለወጣት ብሄራዊ ቡድን የተመረጠው ከዚሁ ክለብ ነው። በ1977ዓ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበልነት ከማገልገሉም በላይ በ65  ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድን  ተሰልፏል።
ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአሰልጣኝነት መስራት የቀጠለ ሲሆን በመቀሌ ከነማ ካገለገለ በኋላ ቡድኑ ወደ ትራንስ ኢትዮጵያ ክለብነት ሲቀየር ለ9 ዓመታት እያሰለጠነው ቆይቷል፡፡
በኢትዮጰያ ፕሪሚዬር ሊግ  ክለቦች አሰልጣኝ በመሆን ልምድ ያለው ሲሆን  በባንኮች ለ2 ዓመታት፣በመድን ለ1 ዓመት፣ በኢትዮጵያ ቡና ለ1ዓመት  እንዲሁም በደደቢት ለ1 ዓመት ከማገልገሉም በላይ ከኢትዮጰያ ውጭ በየመኑ ክለብ አልሳክር ለ6 ወራት በፕሮፌሽናል አሰልጣኝነት የሰራበት ልምድ አለው፡፡ ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት ደግሞ የመከላከያ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ እያገለገለ ነበር፡፡

Read 2986 times