Saturday, 07 May 2016 12:30

የሚዲያ ብዝሃነት ተከብሯል የሚለው እያነጋገረ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(24 votes)

      አለማቀፉ የፕሬስ ቀን ባለፈው ማክሰኞ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት አዘጋጅነት፤ “የሚዲያ ብዝሃነትን  ያከበረች ሀገር-ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን ምሁራንና ጋዜጠኞች የሚዲያ ብዝሃነት አልተከበረም ሲሉ ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል፡፡ መሪ ቃሉ መሬት ያለውን ተጨባጭ እውነታ የሚገልጽ አይደለም ብለዋል - አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ተሾመ በሰጡት አስተያየት፣ ቀኑ የሚከበረው በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ፣ የተሰደዱና ጫና እየደረሰባቸው ያሉ ጋዜጠኞችን ለማሰብ መሆኑን በመጥቀስ መንግስት ሌላ ወንጀል አግኝቼባቸዋለሁ ብሎ ያሰራቸውን ጋዜጠኞች በዚህ አጋጣሚ ከእስር ቢለቅ የሚጎዳው ነገር የለም ብለዋል፡፡ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ የሚዲያ ሞኖፖሊ እየተስፋፋ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ የሀሳብ ብዝሃነትና የሚዲያ ብዝሃነት አለ ለማለት ያስቸግራል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አብርሃም በበኩላቸው፤ ሁሉም ሰው እኩል
የመናገር፤ የመደመጥና ሃሳቡን የማንፀባረቅ እድል ያገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ በመንግስት በኩል ዜጎች ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ክልከላ ባይኖርም የበለጠ እድሎች ሊከፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የ “አዲስ ገፅ” መፅሄት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በሰጠው አስተያየት፤ የሚዲያ ብዝሃነት በሀገሪቱ አለመፈጠሩን ጠቅሶ ያሉት ሚዲያዎችም በርካታ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን ለማስተናገድ የሚፈሩ ናቸው ብሏል፡፡ አለማቀፍ ተቋማት ሀገሪቱ “ፕሬስ አፋኝ ናት” እያሉ የሚያወጡት ሪፖርት፤ በመሬት ላይ ያለውን ሃቅ የሚያንፀባርቅ ነው ሲል ጋዜጠኛ ኤልያስ አክሏል፡፡ “በየቀኑ የሚታተም የግል ጋዜጣ በሌለበትና ያሉትም ራሳቸውን ሳንሱር በማድረግ በተጠመዱበት ሁኔታ የሚዲያ ብዝሃነት ተፈጥሯል የሚባለው ስላቅ ነው” ሲል የተናገረው የ“ውይይት” መፅሄት ዋና አዘጋጅ በፍቃዱ ኃይሉ የሚዲያ ብዝሃነት የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ መንግስት ራሱ በቅጡ የተረዳው አይመስለኝም ብሏል፡፡ አሁን በሀገሪቱ ያለው የሚዲያ ምህዳር አስቸጋሪና እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ የማያሰራ መሆኑንም ጋዜጠኛው አስረድቷል፡፡
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር አቶ እንግዳወርቅ ታደሰ በበኩላቸው፤ በተለይ ኤሌክትሮኒክስ
ሚዲያው ባለፉት ዓመታት በቁጥር መጨመሩን ጠቁመው የሚዲያ ብዝሃነት ስንል የሃሳብ ብዝሃነት ሳይሆን የቁጥር
ማለታችን ከሆነ ተገቢ አይሆንም ብለዋል፡፡ የህትመት ሚዲያው በቁጥርም በይዘትም ብዝሃነት አለው ለማለት አያስደፍርም ያሉት መምህሩ፤ “ለኛ ሀገር የሚያስፈልገው የሀሳብ ብዝሃነት እንጂ የቁጥር ብዛት ብቻ አይደለም” ብለዋል፡፡

Read 3573 times