Print this page
Saturday, 30 April 2016 11:49

መንግስት ሲፈራ ----- አይደላኝም!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)

(ህዝብ የሚፈራው መንግስት፣ ራሱም ፈሪ ነው!)

  እስቲ የዛሬውን ፖለቲካዊ ወጋችንን በጥያቄ እንጀምረው፡፡ እናንተ መንግስት ሲፈራ የሚሰማችሁ ስሜት ምንድን ነው? እውነቱን ልንገራችሁ  አይደል----እኔ ግን ጨርሶ አይደላኝም፡፡ በፍርሃት ነው የምርደው፡፡ ፍርሃቱ ተጋብቶብኝ እኮ አይደለም፡፡ (መንግስት ሲፈራ ማሰብ ስለሚያቆም ነው!) መንግስት ስላችሁ ደግሞ የግድ ኢህአዴግ ማለቴ አይደለም፡፡ (መንግስት ነኝ የሚልን ሁሉ ይመለከታል!) ለነገሩ አይደለም መንግስት፣ተቃዋሚዎችም ሲፈሩ ደግ አይደለም፡፡ እርስበርስ የሚናቆሩት እኮ በፍርሃት ሲሞሉ ነው፡፡ ፍርሃቱ ሲበረታባቸው  ደግሞ እስከ ቡጢ ሁሉ ይዳረሳሉ፡፡ በአጣና ማንጎራደድም ሊከሰት ይችላል፡፡ (መሳሪያ ቢታጠቁ የሚከሰተውን አስቡት!) ደፋሮች እኮ ዱላን አማራጫቸው አያደርጉም፡፡ ችግራቸውን በሰለጠነ ውይይት ይፈታሉ እንጂ፡፡     በነገራችሁ ላይ ስለ መንግስት ሳስብ ---- የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና!) “መንግስት የመላዕክቶች ስብስብ አይደለም” ያሉት ሁሌም ትዝ ይለኛል፡፡ (እንዴት ሊሆን ይችላል?) ይሄ አባባል የሚሰራው መንግስት አማን በሆነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሲፈራ ግን አባባሉም፤“መንግስት ማሰብ ያቆሙ ሰዎች ስብስብ ነው” ወደሚል ይለወጣል፡፡ (መንግስት እየፈራ ማሰብ አይችልም!)
ሰሞኑን ያየሁት ዶክመንተሪ ፊልም በአራዳ ቋንቋ “ጸዴ” የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ በሶስት የዓለማችን ቁንጮ አምባገነን መሪዎች ላይ የተሰራ ነው፡፡ A Day in The Life of A Dictator ይላል ርዕሱ፡፡ በፊልሙ የተካተቱት መሪዎች፣ የ20ኛው ክ/ዘመን አምባገነኖች በሚል የተገለጹት የሶቭየት ህብረቱ ስታሊን፣የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊና የኡጋንዳው ኢዲ አሚን ናቸው፡፡ ስታሊን በ10 ዓመት የፈላጭ ቆራጭ አገዛዙ፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች ግድያ ተጠያቂ መሆኑን የሚገልጸው ፊልሙ፤ጋዳፊ በ28 ዓመት የስልጣን ዘመኑ 300ሺ ዜጎች፣ኢዲ አሚን ደግሞ በ8 ዓመት የሥልጣን ቆይታው 850ሺ ሰዎች መፍጀቱን ይጠቁማል፡፡ (ጭራቅ ናቸው ሰዎች?!) አያችሁልኝ ---- የፍርሃትን ውጤት! እኒህ አምባገነኖች በፍርሃታቸው በእጅጉ ይመሳሰላሉ፡፡ ሶስቱም ህዝባቸውን ሲፈሩ ለጉድ ነበር! ህዝቡም ይፈራቸዋል!
ለዚህ ነው መንግስት ሲፈራ የማይደላኝ!!
መንግስት የለየለት አምባገነን ስለሆነ ብቻ አይደለም የሚፈራው፡፡ ልዩነቱ የፍርሃቱ መጠንና ዕድሜው እንጂ መፍራትማ ትንሽም ብትሆን አትቀርም፡፡ (በፍርሃት የሚርድ መንግስትን  ፍሩልኝ!) እኔ የምለው ግን ----- በተለይ በአንጻራዊነት “ደህና” የተባሉ መንግስታት ለምንድን ነው የሚፈሩት? መንግስት ሆኜ ባላውቅም መገመት አያቅተኝም፡፡ በዋናነት የህዝብን እምነት ወይም ይሁንታ ማጣት ይመስለኛል፡፡ (ከህዝብ ጋር ሆድና ጀርባ መሆን!) ልብ በሉ! የመንግስት ህልውናው እኛ ነን፡፡ (እኛ ስል ህዝብ ማለቴ ነው!) እናላችሁ --- እኛ ፊት የነሳናቸው ጊዜ በፍርሃት ይርዳሉ፡፡ (ድምጻችንን ስንነፍጋቸው ማለት ነው!) የፈራ መንግስት ደግሞ ማሰብ ያቆማል! (#ድሮስ መች ያስባል?” እንዳትሉኝ!) ወዳጆቼ፤መንግስት እንኳን ሳያስብ አስቦም እኮ ብዙ አይፈይድም፡፡   
ለዚህ ነው መንግስት ሲፈራ የማይደላኝ!!
 እንደኔ አመለካከት ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ተቃዋሚዎች እንደሚወነጅሉት የለየለት አምባገነን፣አፍቃሪዎቹ እንደሚያወድሱትም የበቃ ዲሞክራት አይደለም፡፡ (በደፈናው#ልማታዊ” ብንለው ይሻለዋል!) ኢህአዴግ በትግል ላይ ሳለ ከፍርሃት ጋር ጨርሶ እንደማይተዋወቅ የሚመሰክሩ ውስጥ አዋቂ ምንጮች፤ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን እንደ ማንኛውም መንግስት መፍራት መጀመሩን ይጠቁማሉ፡፡ (#Gጅ ያለውና ሥልጣን የያዘ ፈሪ ነው!; እንዲሉ) አንዱም ለልጁ፣ሌላኛውም ለሥልጣኑ --- ሲል ይፈራሉ፡፡ (ድፍረትና ጀብደኝነት ይቀራሉ!)
 በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በሩብ ክፍለ ዘመን የሥልጣን ዘመኑ እንደ 97 የምርጫ ወቅት በፍርሃት የራደበት ጊዜ አለመከሰቱን የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ (አዲስ አበባን ተነጥቆ እንዴት አይርድ!) በቀጣዮቹ 5 ዓመታትም ኢትዮጵያን ያስተዳደራት ቀድሞ የምናውቀው የኢህአዴግ መንግስት ሳይሆን #ፍርሃት የወለደው መንግስት ነው” ሲሉ ይተነትናሉ፡፡ በእነዚያ የፍርሃት ዓመታት ታዲያ የተለያዩ ፍርሃት የወለዳቸው አፋኝ ህጎችና አዋጆች መጽደቃቸውን ታዛቢዎች ያስታውሳሉ፡፡ ያኔ ነው በርካታ የግል ጋዜጦች የተዘጉት፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፡፡  የፖለቲካው ምህዳር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የጠበበው ያኔ ነው፡፡ የተቃውሞ ሰልፍ ለቀጣዮቹ 8 ዓመታት ባልተጻፈ ህግ ታግዶ ቆይቷል፡፡ ተቃዋሚዎች የሚሰበሰቡበት የሆቴል አዳራሽ የሚያከራያቸው አጥተው ነበር፡፡ በአጠቃላይ ---- የዲሞክራሲ ሂደቱ የተቀለበሰበት ወቅት ነው ይላሉ - የፖለቲካ ተንታኞቹ፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ትንሽ ወደ ቀልቡ የተመለሰው፣ በ2002 ምርጫ፣ ተቃዋሚዎችን ከጨዋታ ውጭ አድርጎ (በአስማት ይሁን በዝረራ ባይታወቅም?) ማሸነፉን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ የማታ ማታ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ግስጋሴም፤#አንድ እርምጃ ወደፊት፣ አራት እርምጃ ወደ ኋላ!; በሆነ ሰፊ ልዩነት ተቋጭቷል፡፡ (ያልታደለች አገር!)
 ለዚህ ነው መንግስት ሲፈራ የማይደላኝ!!
እናላችሁ----ኢህአዴግ ምርጫ 97 የፈጠረበትን ፍርሃት ተከትሎ አዲስ እንደተቆረቆረች አገር ጦቢያን በአዳዲስ አዋጅና ህጎች ስላጥለቀለቃት፣ ሁሌም አዲስ ህግና አዋጅ ሲወጣ እበረግጋለሁ፤ከፍርሃት የተወለደ እንዳይሆን በመስጋት፡፡ አሁን ለምሳሌ በቅርቡ የፌደራል ፖሊስ ተጠሪነቱን ለጠ/ሚኒስትሩ የሚያደርገው አዋጅ መጽደቁን ስሰማ ድንግጥ ነው ያልኩት፡፡ (የሚያስደነግጥ እኮ አይደለም!) ግን በቃ ---- ምን ተፈርቶ ይሆን ፖሊስ ጠ/ሚኒስትሩ ሥር የገባው --- ብዬ ሃሳብ ገባኝ፡፡ ለአራት ወራት ከዘለቀው የኦሮምያ ተቃውሞና ግጭት ጋር የተገናኘ ይሆን?  ካልሆነ ---- ለምን ዛሬ?---እንዴት አሁን? ---- ብዙ ቆዘምኩ፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ ተከታትለው የወጡትን ህጎች ለማስታወስ ሞከርኩ - የሚዲያ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት ፣የጸረ-ሽብር ህግ---ወዘተ --- ለአሁኑ ጥርጣሬዬ ፍንጭ ቢሰጠኝ ብዬ ነበር፡፡ ሆኖም ጭላንጭል ሃሳቤን አዳፈነው፡፡  
የኢትዮ ቴሌኮም ውሳኔም ፍርሃት የወለደው እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ቴሌ ወደፊት ይገሰግሳል ተብሎ ተስፋ እንዳልተጣለበት -- የኋሊት ተንሸራቶ የሞባይል ቀፎ ምዝገባና ሲም ካርድ ቁጥጥር ውስጥ ልገባ ነው ማለቱ አሳዛኝ ነው፡፡ ቢሆንማ ኖሮ-----ድርጅቱ ፕራይቬታይዝድ ተደርጎ፣ ዘርፉ ለውድድር ክፍት ቢሆን ለሁላችንም ሸጋ ነበር፡፡ (በእርግጥ የምትታለብ ላም ታሳሳለች!) ለሱ ወግ አልደረስንም ከተባለ ደግሞ ቢያንስ ቴሌ አገልግሎቱን የሚያሻሽልበትንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚያስተዋውቅበትን መንገድ መቀየስ የአባት ነው፡፡ (ጨዋታችን ፖለቲክስ ነው ቴክኖሎጂ?)
 በነገራችን ላይ አዲሱ የቴሌኮም የቁጥጥር መሳሪያ፣ የደንበኞችን ሞባይል ከሌባ ይታደጋል ቢባልም ብዙዎችን እምብዛም አላስደመመም፡፡ (ቴሌ #ያለ ዕዳው ዘማች” ሆኗል!) በነገራችን ላይ የሞባይል ስርቆት ቀርቷል ማለት አይደለም፡፡ አብዛኛው ሰው ግን ከሞባይል ቀፎው ይልቅ የግል ነጻነቱ (ምስጢርና መረጃው) እንዳይሰረቅበት ክፉኛ መጨነቅ ጀምሯል፡፡ እናም ከሞባይል መንታፊ ይልቅ ሞባይል ቀፎና ሲምካርድ እቆጣጠራለሁ የሚለው ቴሌ በእጅጉ አሳስቦታል፡፡   ከኮምፒዩተር አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የተረቀቀው አዋጅም እስከ 20 ዓመት እስር የሚያስቀጣ አንቀጽ ያለው ነው፡፡ (ኮምፒውተር ራሱ #ሽብር” መሰለኝ!) እናላችሁ--ረቂቅ አዋጁ ከሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስም ማጥፋትና ህዝብን ለአመጽ መቀስቀስ በህግ እንደሚያስቀጣ ይጠቁማል፡፡ አሁን ጥያቄያችን ---- የዚህ ረቂቅ አዋጅ መነሻ ህግና ሥርዓት ማስከበር ነው ወይስ ፍራቻ? (ጥርጣሬያችንን መግለጽ ህገመንግስታዊ መብታችን ነው!)  እናላችሁ--- መነሻው ተቃውሞን ፍራቻ ከሆነ አደጋ አለው፡፡ (መንግስት ሲፈራ ማሰብ ያቆማል ብለናል!) በዚህም የተነሳ ህዝብን ለአመጽ መቀስቀስና ለዲሞክራሲ መቀስቀስ ሊምታታበት ይችላል፡፡ (ከቀልቡ አይደለማ!) እናም ለዲሞክራሲ ቀስቅሰን፣ በአመጽ ቀስቃሽነት ብንጠየቅስ? (የፈራ መንግስት አያደርገውም አይባልም!)
ለዚህ ነው መንግስት ሲፈራ የማይደላኝ!!
በነገራችን ላይ መንግስት አንዴ ከፍርሃት ጋር ይተዋወቅ እንጂ ከዚያ በኋላ በፍርሃት ለመራድ እንደ ቅንጅት ያለ የምርጫ ተፎካካሪ ወይም ሌላ አስጊ የሥልጣን ተቀናቃኝ አያስፈልገውም፡፡ ራሱ በፍርሃት የሚያርዱ የፖለቲካ ወይም የመንግስት ሃይሎችን ከአገር ውስጥም ከጎረቤትም፣ ከሩቅም ከቅርብም በምናቡ እየሳለ ወይም በዓይነ ህሊናው እየፈጠረ መሸበሩን ይገፋበታል፡፡  አንዳንዴ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ የሚያወጡትን መግለጫዎች አስተውላችሁልኛል? (የጠላት ያለህ የሚሉ ይመስላሉ!) አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡ የአዲስ ዓመት የምኞት መግለጫ ብለው፤#አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት---” በሚል ዓ.ነገር ይጀምራሉ፡፡ (የውግዘት መግለጫ ሳይባሉ?!)
እናላችሁ----መንግስት የፍርሃት በሽታውን ሥር ከመስደዱ በፊት በአፋጣኝ ማከም ካልቻለ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያስከትልበት ቅንጣት አትጠርጥሩ፡፡ በቃ በትንሹም በትልቁም ሲሸበር መክረሙ ነው፡፡ ችግሩ ግን በራሱ ብቻ አያበቃም፡፡ ለሚመራቸው ህዝቦችና በዙሪያው ላሉ ወገኖች ሁሉ ይተርፋል፡፡ እሱ ተሸብሮ ሌላውንም ያሸብራል፡፡ ሳር ቅጠሉ የሥልጣኑ ስጋት መስሎ ይታየዋል፡፡ ለምሳሌ ጥቂት ሰዎች ለታመመ ወዳጃቸው የገንዘብ እርዳታ ለማዋጣት ተሰብስበው ሲመክሩ፣በእሱ ላይ ሴራ የሚዶልቱ ይመስለዋል፡፡ አንድ 10 ሰርገኞች የጓደኛቸው የሰርግ ሥነስርዓት ባመረና በቀለጠፈ መንገድ ይከወን ዘንድ ካፌ ውስጥ ተሰብስበው ሲወያዩ፣የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመንግስት ላይ አመጽ ሊያስነሱ እየተማከሩ ነው በሚል፣በካድሬ ሰራዊት ከማሰለል ወደ ኋላ አይልም፡፡ በቡድን ብቻ ሳይሆን በግላቸውም ቢሆን የሱን ሥልጣን የሚቋምጡ እንዳሉ መንግስት አበክሮ ያምናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጨርሶ ማስረጃም ሆነ መረጃ አይፈልግም፡፡ እናም ምን ያደርጋል ---- ዓይኑ ላይ ያረፈውን ደራሲ፣ሃኪም፣መሃንዲስ፣ኢንቨስተር፣ምሁር፣የሃይማኖት መሪ፣ጋዜጠኛ፣ ወዘተ --- በደህንነት ኃይሉ ጠራርጎ በማስወሰድ ዘብጥያ ያወርዳቸዋል፡፡
እንዲህ ያለው መንግስት ሁሌም ፊቱ ካገኘው ነገር ጋር ይላተማል፡፡ አፈር ድንጋዩ ሳይቀር ጠላቱ ነው፡፡ በነጋ በጠባ ቁጥር አዳዲስ ጠላቶችን ይፈጥራል ወይም ያፈራል፡፡ ክስና ውንጀላ ቀለቡ ናቸው፡፡ በእንዲህ ያለ መንግስት፣ አገር የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ስትዳክር ትኖራለች፡፡  ህዝቦች በመሪር የአፈና ሥርዓት ይሰቃያሉ፡፡ ዓለም የሚያጣጥመው ነጻነት፣ሳቅና ደስታ----እዚያ ቅንጦት ነው፡፡ ነጋ ጠባ ስልጣኑን በስጋት ለሚጠባበቅ ፈሪ መንግስት፣የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ማንሳት ኩዴታ ከመፈጸም ተለይቶ አይታይም፡፡ የአገር ክህደት ወንጀል በሚል አጠር ብሎ ሊቀርብም ይችላል፡፡     
ለዚህ ነው መንግስት ሲፈራ የማይደላኝ!!
(ሥልጣኑ እንቅልፍ የሚነሳው መንግስትን ፍሩልኝ!!!!)
እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ !

Read 4271 times